ሚልክያስ 3:1-14 - Compare All Versions
ሚልክያስ 3:1-14 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“እነሆ፤ በፊቴ መንገድ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ ዐጣቢ ሳሙና ነውና። ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤ በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቍርባን እንዳለፉት ቀናትና እንደ ቀድሞው ዘመን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘የምንመለሰው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ትሰርቁኛላችሁ። “እናንተ ግን፣ ‘እንዴት እንሰርቅሃለን?’ ትላላችሁ። “ዐሥራትና መባ ትሰርቁኛላችሁ፤ እናንተም፣ መላው ሕዝባችሁም ስለምትሰርቁኝ የተረገማችሁ ናችሁ። በቤቴ መብል እንዲኖር፣ እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ። ስለ እናንተ ተባዩን እገሥጻለሁ፤ አዝመራችሁን አይበላም፤ ዕርሻ ላይ ያለ የወይን ተክላችሁም ፍሬ አልባ አይሆንም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ከዚያም በኋላ የተድላ ምድር ስለምትሆኑ፣ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ተናግራችኋል” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን፣ ‘በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድን ነው?’ ትላላችሁ። “እንዲህም ብላችኋል፤ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግና በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ሐዘንተኞች ሆነን በመመላለስ ምን ተጠቀምን?
ሚልክያስ 3:1-14 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ በፊቴ መንገድን ያዘጋጅ ዘንድ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታም በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ በእርሱ የምትደሰቱበት የቃል ኪዳን መልእክተኛም በእርግጥ ይመጣል።” ነገር ግን እርሱ እንደ ብረት ማቅለጫ እሳትና እንደ ልብስ ማጠቢያ ሳሙና ስለ ሆነ በእርሱ የመምጫ ቀን ጸንቶ መቆም የሚችልና እርሱስ ሲገለጥ በፊቱ መቆም የሚችል ማነው? እርሱ እንደ ብረት አቅላጭና እንደ ብር አንጥረኛ ፍርድን ለማጣራት ይቀመጣል፤ የሌዊንም ልጆች የጽድቅ መሥዋዕት ለማቅረብ እስከሚችሉ ድረስ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የሚያቀርቡት መሥዋዕት እንደ ቀድሞ ዘመንና እንዳለፉት ዓመቶች እግዚአብሔርን የሚያስደስት ይሆናል። የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት መስካሪዎች፥ የቀን ሠራተኞችን ደመወዝ አታለው በሚያስቀሩ አሠሪዎች፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ እናትና አባት የሌላቸው ልጆችንና ስደተኞችን በሚጨቊኑና እኔን በማይፈሩ ሰዎች ላይ ፈጣን ፍርዴን አስተላልፋለሁ። “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ገና ፈጽማችሁ አልጠፋችሁም። ከቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሕጌ ርቃችኋል፤ አልጠበቃችሁትምም። ‘ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’፥ እናንተ ግን ‘ወደ አንተ የምንመለሰው በምን ዐይነት ነው?’ ትላላችሁ። ሰው የእግዚአብሔርን ሀብት ይዘርፋልን? ሆኖም እናንተ እኔን ዘርፋችኋል፥ እናንተ ግን እንዴት ከአንተ እንዘርፋለን ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ ከእኔ የዘረፋችሁት ዐሥራትንና መባን ባለመክፈላችሁ ነው። እናንተ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከእኔ ስለምትዘርፉ የተረገማችሁ ሆናችኋል። በቤተ መቅደሴ ሲሳይ ይበዛ ዘንድ ዐሥራቴን በሙሉ ወደ ጐተራ አግቡ፤ እናንተ ይህን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሰማይን መስኮቶች ከፍቼ መልካም የሆነውን በረከት ሁሉ አብዝቼ ባልሰጣችሁ በዚህ ልትፈትኑኝ ትችላላችሁ። እህላችሁን ተባይ እንዳያጠፋው እከለክላለሁ፤ የወይናችሁ ተክል ፍሬ አልባ አይሆንም፤ ከዚህ በኋላ ሕዝቦች ሁሉ እናንተን የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል፤” ይህን የተናገርኩ እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ትናገራላችሁ፤ እንደገና ደግሞ ‘እኛ በአንተ ላይ ምን ክፉ ነገር ተናገርን?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ እናንተ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዞቹን መጠበቅና እንደ ሐዘንተኞች በሠራዊት አምላክ ፊት መመላለስ ምን ይጠቅመናል?
ሚልክያስ 3:1-14 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፣ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፣ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፣ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል። ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፣ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመመዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፣ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም፦ የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፣ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፣ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል። እናንተም፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፣ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል?
ሚልክያስ 3:1-14 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፥ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፥ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፥ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል። ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፥ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመመዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፥ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም፦ የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፥ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፥ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል። እናንተም፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፥ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል?
ሚልክያስ 3:1-14 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትደሰቱበትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና፤ የሚመጣበትን ቀን መቋቋም የሚችል ማን ነው? እርሱስ ሲገለጥ የሚቆም ማን ነው? ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቁርባን እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት በሚምሉ፥ የሠራተኛውን ደመወዝ በሚያስቀሩ፥ መበለቲቱንና የሙት ልጅን በሚያስጨንቁ፥ ስደተኛውን በሚገፉ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እኔ ጌታ አልለወጥምና፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ አልጠፋችሁም። ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዜ ርቃችኋል፥ አልጠበቃችሁትምም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው እንዴት ነው? ብላችኋል። ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ሰርቃችሁኛል። እናንተም፦ እንዴት እንሰርቅሃለን? ብላችኋል። በአሥራትና በቁርባን ነው። እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ ሰርቃችሁኛልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ፤ የሰማያቶችን መስኮቶች ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ስለ እናንተ በላተኛውን እገሥጻለሁ፥ የአፈራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ያለውንም ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። ሕዝቦች ሁሉ የተባረኩ ብለው ይጠሩአችኋል፥ የደስታ ምድር ትሆናላችሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። በእኔ ላይ የድፍረት ቃላትን ተናግራችኋል፥ ይላል ጌታ። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድነው? ትላላችሁ። እናንተም እንዲህ ብላችኋል፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙን መጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ ፊት ኀዘንተኞች ሆነን መሄድ ምን ይጠቅመናል?