ሉቃስ 8:22-26
ሉቃስ 8:22-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዕለታት በአንዲት ቀንም እንዲህ ሆነ፤ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ወጣና፥ “ኑ ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው እነርሱም ሄዱ። ሲሄዱም አንቀላፋ፤ በባሕሩም ላይ ዐውሎ ነፋስ መጣ፤ ውኃዉም ታንኳቸውን ሞላው፤ እነርሱም ተጨነቁ። ቀርበውም፥ “መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ልንጠፋ ነው” ብለው ቀሰቀሱት፤ ተነሥቶም ነፋሱንና የውኃዉን ማዕበል ገሠጻቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እርሱም “እምነታችሁ ወዴት አለ?” አላቸው፤ እነርሱም ፈርተው ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “ውኃም ነፋስም የሚታዘዙለት ይህ ማነው?” አሉ። ከዚህ በኋላ በገሊላ ወደብ አቅጣጫ ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን ሀገር በታንኳ ሄዱ።
ሉቃስ 8:22-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዕለታቱ በአንድ ቀን፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጕዞ ቀጠሉ። እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ መጥፋታችን እኮ ነው!” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ። እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነርሱም በፍርሀትና በመደነቅ፣ “ይህ ነፋስንና ውሃን የሚያዝዝ፣ እነርሱም የሚታዘዙለት እርሱ ማን ነው?” ተባባሉ። ከዚህ በኋላ ከገሊላ ባሻገር ወዳለው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በጀልባ ተሻገሩ።
ሉቃስ 8:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም። ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር። ቀርበውም፦ አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጽጥታም ሆነ። እርሱም፦ እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፦ እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ። በገሊላም አንጻር ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በታንኳ ደረሱ።
ሉቃስ 8:22-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፈረና “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር፤” አላቸው፤ እነርሱም ለመሄድ ተነሡ። በባሕሩ ላይ እየቀዘፉ ሲሄዱ ሳሉ ኢየሱስ አንቀላፋ፤ በዚያን ጊዜ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ በባሕሩ ላይ ተነሣ፤ ውሃውም በጀልባው ውስጥ መሙላት ስለ ጀመረ አደጋው አስግቶአቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ! ልናልቅ ነው!” ሲሉ ኢየሱስን ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የሚያናውጠውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ነፋሱና የሚያናውጠው ማዕበል ወዲያውኑ ቆሙ፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነርሱ ግን እጅግ ተደንቀውና ፈርተው እርስ በርሳቸው፥ “ነፋስንና ማዕበልን ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ለመሆኑ ይህ ማን ነው?” ተባባሉ። ባሕሩንም ተሻግረው በገሊላ ማዶ ወደምትገኘው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ፤
ሉቃስ 8:22-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዕለታቱም በአንዱ ቀንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ “ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር፤” አላቸው፤ እነርሱም ለመሄድ ተነሡ። እየሄዱም ሳሉ ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደው። ዓውሎ ነፋስም በሐይቁ ላይ ተነሣ፤ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበር፤ እነርሱም በአደጋ ላይ ስለ ነበሩ ተጨንቀው ነበር። ቀርበውም፦ “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ! እየጠፋን ነው፤” እያሉ ቀሰቀሱት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የሚናውጠውን የውኃ ሞገድ ገሠጻቸው፤ እነርሱም አቆሙ፤ ጸጥታም ሆነ። እርሱም፦ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። በፍርሃትና በመደነቅ ተውጠውም፤ እርስ በርሳቸው፦ “እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን ሳይቀር የሚያዝ፥ እነርሱም የሚታዘዙለት ይህ ለመሆኑ ማን ነው?” ተባባሉ። በገሊላም ማዶ ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ተሻገሩ።