ሉቃስ 6:39-49

ሉቃስ 6:39-49 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ምሳ​ሌም መሰ​ለ​ላ​ቸ​ውና እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ዕውር ዕው​ርን ሊመራ ይች​ላ​ልን? ሁለ​ቱስ በጕ​ድ​ጓድ ውስጥ ይወ​ድቁ የለ​ምን? ከመ​ም​ህሩ የሚ​በ​ልጥ ደቀ መዝ​ሙር የለም፤ ለሁ​ሉም መጠኑ እንደ መም​ህሩ ይሆ​ናል። በወ​ን​ድ​ምህ ዐይን ውስጥ ያለ​ውን ጕድፍ ለምን ታያ​ለህ? በዐ​ይ​ንህ ውስጥ ያለ​ውን ምሰሶ አታ​ይ​ምን? ወን​ድ​ም​ህ​ንም፦ ወን​ድሜ ሆይ፥ ታገሥ፤ በዐ​ይ​ንህ ያለ​ውን ጕድፍ ላው​ጣ​ልህ ልት​ለው እን​ደ​ምን ትች​ላ​ለህ? አንተ ግን በዐ​ይ​ንህ ውስጥ ያለ​ውን ምሰሶ አታ​ይም፤ አንተ ግብዝ፥ አስ​ቀ​ድሞ ከዐ​ይ​ንህ ምሰ​ሶ​ውን አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በባ​ል​ን​ጀ​ራህ ዐይን ውስጥ ያለ​ውን ጕድፍ ታወጣ ዘንድ አጥ​ር​ተህ ታያ​ለህ። ክፉ ፍሬን የሚ​ያ​ፈራ መል​ካም ዛፍ የለም፤ መል​ካም ፍሬ የሚ​ያ​ፈራ ክፉ ዛፍም የለም። ዛፍ ሁሉ ከፍ​ሬው ይታ​ወ​ቃል፤ ከእ​ሾህ በለ​ስን አይ​ለ​ቅ​ሙም፤ ከደ​ን​ደ​ርም ወይ​ንን አይ​ለ​ቅ​ሙም። መል​ካም ሰው ከልቡ መል​ካም መዝ​ገብ መል​ካ​ምን ያወ​ጣል፤ ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝ​ገብ ክፉ ነገ​ርን ያወ​ጣል፤ ከልብ የተ​ረ​ፈ​ውን አፍ ይና​ገ​ራ​ልና። “ለምን አቤቱ፥ አቤቱ፥ ትሉ​ኛ​ላ​ችሁ? የም​ላ​ች​ሁ​ንም አታ​ደ​ር​ጉም። ወደ እኔ የሚ​መ​ጣና ቃሌን ሰምቶ የሚ​ያ​ደ​ር​ገ​ውም ሁሉ የሚ​መ​ስ​ለ​ውን አሳ​ያ​ች​ኋ​ለሁ። መሠ​ረ​ቱን አጥ​ልቆ ቈፍሮ የመ​ሠ​ረ​ተና ቤቱን በዐ​ለት ላይ የሠራ ሰውን ይመ​ስ​ላል፤ ብዙ ፈሳ​ሾች በመጡ ጊዜ ጎር​ፎች ያን ቤት ገፉት፤ ሊያ​ነ​ዋ​ው​ጡ​ትም አል​ቻ​ሉም፤ በዐ​ለት ተሠ​ር​ቶ​አ​ልና። ቃሌን ሰምቶ የማ​ያ​ደ​ር​ገው ሰው ግን ቤቱን ያለ መሠ​ረት በአ​ፈር ላይ የሠራ ሰውን ይመ​ስ​ላል፤ ጎር​ፎች ገፉት፤ ወዲ​ያ​ው​ኑም ወደቀ፤ የዚ​ያም ቤት አወ​ዳ​ደቁ ታላቅ ሆነ።”

ሉቃስ 6:39-49 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጕድጓድ አይገቡምን? ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል። “በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም። ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ ከቀጋ ቍጥቋጦ የወይን ፍሬ አይቈረጥም። መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና። “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ? ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤ ቤት ለመሥራት አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም። ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ቤቱን ያለ መሠረት በዐፈር ላይ የሠራን ሰው ይመስላል፤ የወንዝ ሙላትም ቤቱን በመታው ጊዜ ወዲያው ወደቀ፤ ክፉኛም ፈራረሰ።”

ሉቃስ 6:39-49 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ምሳሌም አላቸው፦ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን? ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፦ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል። ስለ ምን፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም? ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።

ሉቃስ 6:39-49 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? እንዲህማ ቢያደርግ ሁለቱም ተያይዘው በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ ይሁን እንጂ ተማሪ ትምህርቱን በደንብ ከተማረ እንደ አስተማሪው ይሆናል። “በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ስለምን በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? ደግሞስ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ወንድሜ ሆይ፥ እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ፤’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ። “መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ አያፈራም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ እንዲሁም ከእሾኻማ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ አይለቀምም። ስለዚህ ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካምን ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከመጥፎ ልቡ ክፉውን ነገር ያወጣል። ሰው በአፉ የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “እኔ የምነግራችሁን አትፈጽሙም፤ ታዲያ፥ ስለምን ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እያላችሁ ትጠሩኛላችሁ? ወደ እኔ የሚመጣና ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ማንን እንደሚመስል ልንገራችሁ፤ እርሱ በጥልቅ ቆፍሮ ቤቱን በጽኑ አለት ላይ የመሠረተውን ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በጽኑ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ ሊያነቃንቀው አልቻለም። ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ያለ መሠረት ቤቱን በዐፈር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍ መጥቶ ያንን ቤት በገፋው ጊዜ ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም እጅግ ታላቅ ሆነ።”

ሉቃስ 6:39-49 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እርሱም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዐይነ ስውር ዐይነ ስውርን መምራት ይችላልን? ሁለቱም በጉድጓድ አይወድቁምን? ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም? አንተ ራስህ በዐይንህ ያለውን ምሰሶ ሳታይ እንዴት ወንድምህን፦ ‘ወንድሜ ሆይ! በዐይንህ ያለውን ጉድፍ እዳወጣ ፍቀድልኝ፤’ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” መልካም ዛፍ የተበላሸ ፍሬ አያፈራምና፤ እንዲሁም የተበላሸ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ከአጣጥ ቁጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። መልካም ሰው በልቡ ከሚገኘው መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሚገኘው ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና። ስለምን “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ትሉኛላችሁ? የምለውን ግን አታደርጉም? ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ፥ ቃሎቼንም ሰምቶ የሚያደርጋቸው ሰው ማንን እንደሚመስል አሳያችኋለሁ፤ እርሱም፦ ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ፥ በዐለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፤ ደኅና ተደርጎም ስለ ታነጸ ሊያናውጠው አልቻለም። ነገር ግን ሰምቶ የማያደርገው ቤቱን ያለ መሠረት በምድር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው፤ ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።”