ሉቃስ 6:20-26
ሉቃስ 6:20-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዐይኖቹን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ድሆች፥ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና። ዛሬ የምትራቡ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና፤ ዛሬ የምታለቅሱ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ፥ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ። ያንጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ በደስታም ዝለሉ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ብዙ ነውና፤ አባቶቻቸውም ነቢያትን እንዲሁ አድርገዋቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለጠጎች፥ ወዮላችሁ፥ ደስታችሁን ጨርሳችኋልና። ዛሬ ለምትጠግቡ፥ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና፤ ዛሬ ለምትስቁም ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና፤ ታለቅሳላችሁምና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካሙን ነገር ቢናገሩላችሁ ወዮላችሁ፥ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ያደርጉ ነበርና።
ሉቃስ 6:20-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤ ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ። “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና።
ሉቃስ 6:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።
ሉቃስ 6:20-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር። “እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ! “እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ! “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር።
ሉቃስ 6:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና።