ሉቃስ 6:1-5
ሉቃስ 6:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቈርጠው በእጃቸው እያሹ በሉ። ፈሪሳውያንም፥ “በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩትም በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንደ ገባ፥ ከካህናቱም ብቻ በቀር ሊበሉት የማይገባውን የመሥዋዕቱን ኅብስት ወስዶ እንደ በላ፥ አብረውት ለነበሩትም እንደ ሰጣቸው አላነበባችሁምን? የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።
ሉቃስ 6:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋራ ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።
ሉቃስ 6:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ፦ በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ፦ ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም።
ሉቃስ 6:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ በእጃቸው ማሸትና መብላት ጀመሩ፤ ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርቱን “በሰንበት ቀን ሊደረግ የማይገባውን ነገር ስለምን ታደርጋላችሁ?” አሉአቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እርሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ የመባ ኅብስት አንሥቶ በላ፤ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።” ቀጥሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው፤” አላቸው።
ሉቃስ 6:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ሲያልፍ ሳለ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ስለምን ታደርጋላችሁ?” ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ እንዲህ አለ፦ “ዳዊት በተራበ ጊዜ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን ነገር አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር ለመብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን ኅብስት ወስዶ እንዴት እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንዴት እንደሰጣቸው ይገልጥ የለምን?” እርሱም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤” አላቸው።