ሉቃስ 4:17-21
ሉቃስ 4:17-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የነቢዩን የኢሳይያስንም መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ እንዲህ የሚል የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። “የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ።” መጽሐፉንም አጥፎ ለተላላኪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራብም የነበሩት ሁሉ ዐይናቸውን አትኲረው ተመለከቱት። እርሱም፥ “የዚህ የመጽሐፍ ነገር ዛሬ በጆሮአችሁ ደረሰ፤ ተፈጸመም” ይላቸው ጀመር።
ሉቃስ 4:17-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም መጽሐፍ በተረተረው ጊዜ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ክፍል አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ከዚያም መጽሐፉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብ የነበሩትም ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፣ “ይህ በጆሯችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ይላቸው ጀመር።
ሉቃስ 4:17-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር።
ሉቃስ 4:17-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሰሩት መፈታትን፥ ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤ እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።” ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤ እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው።
ሉቃስ 4:17-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር።