ሉቃስ 3:15-21
ሉቃስ 3:15-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡም ሁሉ በልባቸው ዐሰቡ፤ ዮሐንስም ክርስቶስ እንደ ሆነ መሰላቸው። ዮሐንስም መልሶ ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ግን የሚበልጠኝ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ልፈታለት የማይገባኝ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእሳትም ያጠምቃችኋል። መንሹ በእጁ ነው፤ የዐውድማውንም እህል ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይሰበስባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥላል።” ሕዝቡንም ይገስጻቸውና በሌላም በብዙ ነገር የምሥራች ይነግራቸው ነበር። ዮሐንስም የአራተኛው ክፍል ገዢ ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሄሮድስ ያደርገው ስለነበረው ክፉ ነገር ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም ከዚህ ሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አስገባው። ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ጌታችን ኢየሱስም ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ።
ሉቃስ 3:15-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቡ በጕጕት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር። ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታው ይመጣል፤ እኔም የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ዮሐንስም በብዙ ሌሎች የምክር ቃላት ሕዝቡን እያስጠነቀቀ ወንጌልን ሰበከላቸው። ነገር ግን ዮሐንስ፣ የአራተኛውን ክፍል ገዥ ሄሮድስን የወንድሙ ሚስት በነበረችው በሄሮድያዳ ምክንያትና ስለ ሌሎች ሥራዎቹ በገሠጸው ጊዜ፣ ሄሮድስ ይህን በሌላው ሁሉ ላይ በመጨመር፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው። ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤
ሉቃስ 3:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥ ዮሐንስ መልሶ፦ እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው። ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥
ሉቃስ 3:15-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ዘመን ሕዝቡ ሁሉ የመሲሕን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ ስለዚህ ዮሐንስን “ይህ ሰው ምናልባት መሲሕ ይሆንን?” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ዮሐንስ ግን ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ሌላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ የእርሱን ጫማ ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። እርሱ በአውድማ ላይ እህሉን ከገለባ ለመለየት መንሹን በእጁ ይዞአል፤ ካጣራውም በኋላ ጥሩውን እህል በጐተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” እንዲሁም ዮሐንስ በልዩ ልዩ መንገድ ሕዝቡን እየመከረ መልካሙን ዜና ያበሥር ነበር። የገሊላውን ገዢ ሄሮድስን ግን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱና ሌላም ብዙ ክፉ ነገር በማድረጉ ገሠጸው። ሄሮድስ በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወደ ወህኒ ቤት አስገባው። ሰዎች ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እርሱ ሲጸልይ ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤
ሉቃስ 3:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡም ሲጠብቁ ነበርና፥ ሁሉም በልባቸው ዮሐንስን በተመለከተ “እርሱ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አሰቡ፤ ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “እኔስ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ጠፍር መፍታት እንኳ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ አውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውን በጎተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ስለዚህ ለሕዝቡ ሌሎች ብዙ ምክሮችን እየሰጠ መልካም ዜናን ያበሥር ነበር፤ አገረ ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ወንድሙ ሚስት ስለ ሄሮድያዳና ሄሮድስ ስላደረገው ክፋት ሁሉ በዮሐንስ ስለ ተገሠጸ፥ በክፋቶቹ ሁሉ ላይ ይህን ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አስገባው። ሕዝቡም ሁሉ በተጠመቁ ጊዜ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤