ሉቃስ 3:1-20

ሉቃስ 3:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጢባ​ር​ዮስ ቄሣር በነ​ገሠ በዐ​ሥራ አም​ስት ዓመት ጴን​ጤ​ና​ዊው ጲላ​ጦስ የይ​ሁዳ ገዢ ሆኖ ሳለ፥ ሄሮ​ድ​ስም በገ​ሊላ የአ​ራ​ተ​ኛው ክፍል ገዢ ሳለ፥ ወን​ድሙ ፊል​ጶ​ስም የኢ​ጡ​ር​ያ​ስና የጥ​ራ​ኮ​ኒ​ዶስ አራ​ተኛ ክፍል ገዢ፥ ሊሳ​ን​ዮ​ስም የሳ​ብ​ላ​ኒስ አራ​ተኛ ክፍል ገዢ ሆነው ሳሉ፥ ሐናና ቀያ​ፋም ሊቃነ ካህ​ናት በነ​በ​ሩ​በት ወራት የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል በም​ድረ በዳ ወደ ዘካ​ር​ያስ ልጅ ወደ ዮሐ​ንስ መጣ። ስለ ኀጢ​አት ስር​የት ለን​ስሓ የሚ​ያ​በቃ ጥም​ቀ​ትን እየ​ሰ​በከ በዮ​ር​ዳ​ኖስ አው​ራጃ ዞረ። በም​ድረ በዳ የሚ​ጮኽ የአ​ዋጅ ነጋሪ ድምፅ በነ​ቢዩ በኢ​ሳ​ይ​ያስ መጽ​ሐፍ ቃል እንደ ተጻፈ፥ እን​ዲህ ሲል፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ገድ ጥረጉ፤ ጥር​ጊ​ያ​ው​ንም አስ​ተ​ካ​ክሉ። ጐድ​ጓ​ዳው ሁሉ ይምላ፤ ተራ​ራ​ውም፥ ኮረ​ብ​ታ​ውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ሰን​ከ​ል​ካ​ላ​ውም የቀና ጥር​ጊያ ይሁን፤ ወጣ ገባው መን​ገ​ድም ይስ​ተ​ካ​ከል። ሰውም ሁሉ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ትድ​ግና ይይ።” ዮሐ​ን​ስም ሊያ​ጠ​ም​ቃ​ቸው የመ​ጡ​ትን ሰዎች እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንት የእ​ፉ​ኝት ልጆች፥ ከሚ​መ​ጣው መቅ​ሠ​ፍት ታመ​ልጡ ዘንድ ማን ነገ​ራ​ችሁ? እን​ግ​ዲህ ለን​ስሓ የሚ​ያ​በ​ቃ​ች​ሁን ሥራ ሥሩ፤ አብ​ር​ሃም አባ​ታ​ችን አለን በማ​ለት የም​ታ​መ​ልጡ አይ​ም​ሰ​ላ​ችሁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእ​ነ​ዚህ ድን​ጋ​ዮች ለአ​ብ​ር​ሃም ልጆ​ችን ማስ​ነ​ሣት እን​ደ​ሚ​ችል እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ። እነሆ፥ ምሳር በዛ​ፎች ላይ ተቃ​ጥ​ቶ​አል፤ መል​ካም ፍሬ የማ​ያ​ፈ​ራ​ው​ንም ዛፍ ሁሉ ይቈ​ር​ጡ​ታል፤ ወደ እሳ​ትም ይጥ​ሉ​ታል።” ሕዝ​ቡም፥ “እን​ግ​ዲህ ምን እና​ድ​ርግ?” ብለው ጠየ​ቁት። እር​ሱም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ሁለት ልብስ ያለው አን​ዱን ለሌ​ለው ይስጥ፤ ምግብ ያለ​ውም እን​ዲሁ ያድ​ርግ።” ቀራ​ጮ​ችም ሊያ​ጠ​ም​ቃ​ቸው መጡና፥ “መም​ህር፥ ምን እና​ድ​ርግ?” ብለው ጠየ​ቁት። እር​ሱም፥ “ከታ​ዘ​ዛ​ች​ሁት አት​ር​ፋ​ችሁ አት​ው​ሰዱ” አላ​ቸው። ጭፍ​ሮ​ችም መጥ​ተው፥ “እኛሳ ምን እና​ድ​ርግ?” አሉት፤ “በደ​መ​ወ​ዛ​ችሁ ኑሩ እንጂ በማ​ንም ግፍ አት​ሥሩ፤ ማን​ንም አት​ቀሙ፤ አት​በ​ድ​ሉም” አላ​ቸው። ሕዝ​ቡም ሁሉ በል​ባ​ቸው ዐሰቡ፤ ዮሐ​ን​ስም ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆነ መሰ​ላ​ቸው። ዮሐ​ን​ስም መልሶ ሁሉ​ንም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እኔ በውኃ አጠ​ም​ቃ​ች​ኋ​ለሁ፤ ግን የሚ​በ​ል​ጠኝ የጫ​ማ​ውን ማሰ​ሪያ እንኳ ልፈ​ታ​ለት የማ​ይ​ገ​ባኝ ይመ​ጣል፤ እርሱ በመ​ን​ፈስ ቅዱስ፥ በእ​ሳ​ትም ያጠ​ም​ቃ​ች​ኋል። መንሹ በእጁ ነው፤ የዐ​ው​ድ​ማ​ው​ንም እህል ያጠ​ራል፤ ስን​ዴ​ው​ንም በጎ​ተ​ራው ይሰ​በ​ስ​ባል፤ ገለ​ባ​ውን ግን በማ​ይ​ጠፋ እሳት ያቃ​ጥ​ላል።” ሕዝ​ቡ​ንም ይገ​ስ​ጻ​ቸ​ውና በሌ​ላም በብዙ ነገር የም​ሥ​ራች ይነ​ግ​ራ​ቸው ነበር። ዮሐ​ን​ስም የአ​ራ​ተ​ኛው ክፍል ገዢ ሄሮ​ድ​ስን የወ​ን​ድ​ሙን የፊ​ል​ጶ​ስን ሚስት ሄሮ​ድ​ያ​ዳን ስለ​ማ​ግ​ባ​ቱና ሄሮ​ድስ ያደ​ር​ገው ስለ​ነ​በ​ረው ክፉ ነገር ሁሉ ይገ​ሥ​ጸው ነበር። ደግ​ሞም ከዚህ ሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐ​ን​ስን ተቀ​የ​መ​ውና በግ​ዞት ቤት አስ​ገ​ባው።

ሉቃስ 3:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤ ይኸውም፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤ “በምድረ በዳ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አቅኑ፤ ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው መንገድ ቀና፣ ወጣ ገባውም ጐዳና ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል፤ የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ” ዮሐንስም በርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባት አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና። እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው። ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት። እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው። ወታደሮች ደግሞ፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” አላቸው። ሕዝቡ በጕጕት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር። ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታው ይመጣል፤ እኔም የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ዮሐንስም በብዙ ሌሎች የምክር ቃላት ሕዝቡን እያስጠነቀቀ ወንጌልን ሰበከላቸው። ነገር ግን ዮሐንስ፣ የአራተኛውን ክፍል ገዥ ሄሮድስን የወንድሙ ሚስት በነበረችው በሄሮድያዳ ምክንያትና ስለ ሌሎች ሥራዎቹ በገሠጸው ጊዜ፣ ሄሮድስ ይህን በሌላው ሁሉ ላይ በመጨመር፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው።

ሉቃስ 3:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፥ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና። አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ሕዝቡም፦ እንግዲህ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። መልሶም፦ ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ ይል ነበር። ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። ጭፍሮችም ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው። ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥ ዮሐንስ መልሶ፦ እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው።

ሉቃስ 3:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የሮም ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጰንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ምድር አስተዳዳሪ ነበር፤ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዢ ነበር፤ እንዲሁም ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሌኔ ገዢ ነበሩ፤ ሐናና ቀያፋም የካህናት አለቆች ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ በበረሓ ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ስለዚህ ዮሐንስ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ እየተዘዋወረ፦ “ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ፤” እያለ ያስተምር ነበር። ይህም የሆነው፦ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ አስቀድሞ እንዲህ ሲል በጻፈው መሠረት ነው፦ “እነሆ! ይህ በበረሓ እንዲህ እያለ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነው፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ! ጥርጊያውንም አቅኑ! ጐድጓዳው ቦታ ሁሉ ይደልደል! ተራራና ኰረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል! ጠማማው መንገድ ይቅና! ሻካራውም መንገድ ይስተካከል! ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ!’ ” ሊጠመቁ ወደ እርሱ የመጡትን ብዙ ሕዝብ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የመርዘኛ እባብ ልጆች! ከሚመጣው ከእግዚአብሔር ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ? ይልቁንስ ንስሓ መግባታችሁን የሚያመለክት ሥራ ሥሩ እንጂ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን እያላችሁ በልባችሁ አትመኩ። እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እንደሚችል እነግራችኋለሁ። አሁን መጥረቢያ በዛፎቹ ሥር ተቀምጦአል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም “ታዲያ፥ ምን እናድርግ?” ሲሉ ዮሐንስን ጠየቁት። እርሱም፦ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ፤ ምግብ ያለውም ለሌለው ያካፍል፤” አላቸው። ቀራጮችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው “መምህር ሆይ! እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ “በሕግ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትጠይቁ፤” አላቸው። ወታደሮችም መጥተው፥ “እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት፤ እርሱም፦ “የሰው ገንዘብ በግፍ ነጥቃችሁ አትውሰዱ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ የራሳችሁ ደመወዝ ይብቃችሁ፤” አላቸው። በዚያን ዘመን ሕዝቡ ሁሉ የመሲሕን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ ስለዚህ ዮሐንስን “ይህ ሰው ምናልባት መሲሕ ይሆንን?” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ዮሐንስ ግን ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ሌላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ የእርሱን ጫማ ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። እርሱ በአውድማ ላይ እህሉን ከገለባ ለመለየት መንሹን በእጁ ይዞአል፤ ካጣራውም በኋላ ጥሩውን እህል በጐተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” እንዲሁም ዮሐንስ በልዩ ልዩ መንገድ ሕዝቡን እየመከረ መልካሙን ዜና ያበሥር ነበር። የገሊላውን ገዢ ሄሮድስን ግን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱና ሌላም ብዙ ክፉ ነገር በማድረጉ ገሠጸው። ሄሮድስ በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወደ ወህኒ ቤት አስገባው።

ሉቃስ 3:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም የይሁዳ ገዥ ነበር፥ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስ ደግሞ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አገረ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሊኒ አገረ ገዢ ሳሉ፥ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ዘመን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። በዮርዳኖስም ዙርያ ወዳለው አገር ሁሉ መጥቶ ለኃጢአት ስርየት የንስሓን ጥምቀት ሰበከ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በሚገኘበት መጽሐፍ እንደተጻፈው፦ “በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ ጐድጓዳው ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም መንገድ ቀና ይሁን፤ ሸካራውም መንገድ የተስተካከለ ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤” ስለዚህ በእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚገቡ ፍሬዎች አፍሩ፤ በልባችሁም ‘አብርሃም አባት አለን፤’ አትበሉ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንደሚችል እነግራችኋለሁና። ቀድሞውንም እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።” ሕዝቡም፦ “ታድያ፥ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ።” ግብር ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ “መምህር ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉት። እርሱም፦ “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ ምንም አትሰብስቡ፤” አላቸው። ወታደሮችም እንዲሁ፦ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ “ማንንም በግፍ ወይም በሐሰት ክስ አትበዝብዙ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሲጠብቁ ነበርና፥ ሁሉም በልባቸው ዮሐንስን በተመለከተ “እርሱ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አሰቡ፤ ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “እኔስ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ጠፍር መፍታት እንኳ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ አውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውን በጎተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” ስለዚህ ለሕዝቡ ሌሎች ብዙ ምክሮችን እየሰጠ መልካም ዜናን ያበሥር ነበር፤ አገረ ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ወንድሙ ሚስት ስለ ሄሮድያዳና ሄሮድስ ስላደረገው ክፋት ሁሉ በዮሐንስ ስለ ተገሠጸ፥ በክፋቶቹ ሁሉ ላይ ይህን ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አስገባው።