ሉቃስ 24:44-53
ሉቃስ 24:44-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም፥ “በሙሴ ኦሪት፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ እንዳለው፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የነገርኋችሁ ነገሬ ይህ ነው” አላቸው። ከዚህም በኋላ መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፥ “ክርስቶስ እንዲሞት በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንዲነሣ፥ ንስሓና የኀጢኣት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንዲሰበክ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ነገር ምስክሮች ናችሁ። እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ።” እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው። እየባረካቸውም ራቃቸው፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በቤተ መቅደስም ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያገለገሉ ኖሩ። ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ወንጌላዊ ሉቃስ የጻፈው ወንጌል ተፈጸመ። የጻፈውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በዐረገ በሃያ አንድ ዓመት ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አራት ዓመት በጽርዕ ቋንቋ ለመቄዶንያ ሰዎች ነው። ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። አሜን።
ሉቃስ 24:44-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱም፣ “ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።” ከዚህ በኋላ እስከ ቢታንያ ይዟቸው ወጣ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። እየባረካቸውም ሳለ፣ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለት፤ በታላቅ ደስታም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር በቤተ መቅደስ ነበሩ።
ሉቃስ 24:44-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ። እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።
ሉቃስ 24:44-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው። ከዚህ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተዋል እንዲችሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። እንዲህም አላቸው፤ “መሲሕ መከራ እንደሚቀበልና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደሚነሣ አስቀድሞ ተጽፎአል፤ እንዲሁም በስሙ የንስሓና የኃጢአት ይቅርታ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በየአገሩ ለሕዝብ ሁሉ እንደሚሰበክ ተነግሮአል። እናንተም የዚህ ሁሉ ነገር ምስክሮች ናችሁ፤ እነሆ! እኔ አባቴ የሰጣችሁን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተም ከላይ ኀይል እንደ ልብስ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከኢየሩሳሌም ከተማ አውጥቶ እስከ ቢታንያ ወሰዳቸው፤ በዚያም እጆቹን ዘርግቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ሳለ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር ከቤተ መቅደስ አይለዩም ነበር።
ሉቃስ 24:44-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።” እስከ ቢታንያም ወሰዳቸው፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። እየባረካቸውም ከእነርሱ ተለየ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በመቅደስ ኖሩ።