ሉቃስ 24:18-27
ሉቃስ 24:18-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእነርሱም ቀለዮጳ የሚባለው አንዱ መልሶ፥ “አንተ ብቻ ለኢየሩሳሌም እንግዳ ነህን? በእነዚህ ቀኖችስ በውስጥዋ የተደረገውን አታውቅምን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ይህ ምንድነው?” አላቸው፤ እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “በእግዚአብሔር ፊትና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በቃሉና በሥራው ብርቱ ነቢይና እውነተኛ ሰው ስለነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፥ የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን አሳልፈው እንደ ሰጡት፥ ሞትም እንደ ፈረዱበትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ እናደርግ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ይህ ነገር ከሆነ ዛሬ ሦስተኛ ቀን ነው። ደግሞም ሴቶች ከእኛ ዘንድ ወደ መቃብር ገስግሠው ሄደው ነበርና አስደንቀው ነገሩን። ሥጋውንም በአላገኙ ጊዜ ተመልሰው፦ ተነሥቶአል ያሉአቸውን የመላእክትን መልክ እንደ አዩ ነገሩን። ከእኛም ዘንድ ወደ መቃብር ሄደው እንዲሁ ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ ያገኙት አሉ፤ እርሱን ግን አላዩትም።” ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰነፎች፥ ነቢያትም የተናገሩትን ነገር ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ፥ ክርስቶስ እንዲህ ይሞት ዘንድ ወደ ክብሩም ይመለስ ዘንድ ያለው አይደለምን?” እርሱም ከሙሴና ከነቢያት፥ ከመጻሕፍትም ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን ይተረጕምላቸው ጀመር።
ሉቃስ 24:18-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት። እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።
ሉቃስ 24:18-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።
ሉቃስ 24:18-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው።
ሉቃስ 24:18-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ቀለዮጳ የሚባለውም አንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም የተከሠተውን ነገር የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” እርሱም “ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነው፤ የካህናት አለቆቻችንና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን የሚታደገው እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ይህ ነገር ከሆነ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ‘ሕያው ነው’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛ ጋር ከነበሩት አንዳንዶች ወደ መቃብር ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉ፤ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን አብራራላቸው።