ሉቃስ 24:1-12

ሉቃስ 24:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከሳ​ም​ን​ቱም በመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዪቱ ቀን ያዘ​ጋ​ጁ​ትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማል​ደው ወደ መቃ​ብሩ ሄዱ፤ ሌሎች ሴቶ​ችም አብ​ረ​ዋ​ቸው ነበሩ። ያቺ​ንም ድን​ጋይ ከመ​ቃ​ብሩ ላይ ተን​ከ​ባ​ልላ አገ​ኙ​አት። ገብ​ተ​ውም የጌ​ታ​ችን የኢ​የ​ሱ​ስን ሥጋ አላ​ገ​ኙም። ስለ​ዚ​ህም ነገር የሚ​ሉ​ትን አጥ​ተው ሲያ​ደ​ንቁ ሁለት ሰዎች ከፊ​ታ​ቸው ቆመው ታዩ​አ​ቸው፤ ልብ​ሳ​ቸ​ውም ያብ​ረ​ቀ​ርቅ ነበር። ፈር​ተ​ውም ፊታ​ቸ​ውን ወደ ምድር አቀ​ረ​ቀሩ። እነ​ር​ሱም እን​ዲህ አሉ​አ​ቸው፥ “ሕያ​ዉን ከሙ​ታን ጋር ለምን ትሹ​ታ​ላ​ችሁ? በዚህ የለም፤ ተነ​ሥ​ቶ​አል። በገ​ሊላ ሳለ ለእ​ና​ንተ እን​ዲህ ሲል የተ​ና​ገ​ረ​ውን ዐስቡ፦ የሰው ልጅ በኀ​ጢ​ኣ​ተ​ኞች ሰዎች እጅ ተላ​ልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይሰ​ቅ​ሉ​ታል፤ ይገ​ድ​ሉ​ታል፤ በሦ​ስ​ተ​ኛ​ውም ቀን ይነ​ሣል።” 10፥33-34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33። ቃሉ​ንም ዐሰቡ። ከመ​ቃ​ብ​ርም ተመ​ል​ሰው ለዐ​ሥራ አን​ዱና ለቀ​ሩት ባል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ቸው ሁሉ ይህን ነገር ነገ​ሩ​አ​ቸው። እነ​ዚ​ያም መግ​ደ​ላ​ዊት ማር​ያም፥ ዮሐና፥ የያ​ዕ​ቆብ እናት ማር​ያም፥ አብ​ረ​ዋ​ቸው የነ​በ​ሩት ባል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ቸ​ውም ይህን ለሐ​ዋ​ር​ያት ነገ​ሩ​አ​ቸው። ይህም ነገር በፊ​ታ​ቸው እንደ ተረት መሰ​ላ​ቸ​ውና አላ​መ​ኑ​አ​ቸ​ውም። ጴጥ​ሮ​ስም ተነሣ፤ ወደ መቃ​ብ​ርም ፈጥኖ ሄደ፤ ዝቅ ብሎም በተ​መ​ለ​ከተ ጊዜ በፍ​ታ​ውን ለብ​ቻው ተቀ​ምጦ አየ፤ የሆ​ነ​ው​ንም እያ​ደ​ነቀ ተመ​ለሰ።

ሉቃስ 24:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው እጅግ ማለዳ ሳለ ወደ መቃብሩ ሄዱ። ድንጋዩም ከመቃብሩ ደጃፍ ተንከባልሎ አገኙት፤ ወደ ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ እነሆ፤ እጅግ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ። ሴቶቹም ከመፍራታቸው የተነሣ በምድር ተደፍተው ሳሉ፣ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቷል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና።” ሴቶቹም በዚህ ጊዜ ቃሉን አስታወሱ። ሴቶቹ ከመቃብሩ ስፍራ ተመልሰው ይህን ሁሉ ነገር ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩት ሁሉ ነገሯቸው። ይህን ለሐዋርያት የነገሯቸውም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ከእነርሱ ጋራ የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። እነርሱ ግን ሴቶቹ የተናገሩት ቃል መቀባዠር ስለ መሰላቸው አላመኗቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያ ደርሶም ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታውን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተገረመ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ሉቃስ 24:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው፦ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ። ቃሎቹንም አሰቡ፥ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ።

ሉቃስ 24:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት። ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። ስለዚህም ነገር በመገረም ላይ ሳሉ እነሆ፥ የሚያንጸባርቅ ብሩህ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች መጥተው በአጠገባቸው ቆሙ። ሴቶቹም እጅግ ፈርተው ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ ሰዎቹ፦ “ስለምን ሕያውን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? አሉአቸው። እርሱ እዚህ የለም፤ ተነሥቶአል፤ በገሊላ በነበረበት ጊዜ የነገራችሁን አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች ተላልፎ መሰጠት፥ መሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ከሞት መነሣት ይገባዋል’ ብሎአችሁ ነበር።” ሴቶቹም የኢየሱስን ቃል አስታወሱ፤ ከመቃብርም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለቀሩትም ነገሩአቸው። ይህን ለሐዋርያት የተናገሩት መግደላዊት ማርያም፥ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም፥ እንዲሁም ሌሎች ሴቶች ነበሩ። እነርሱ ግን ይህ ነገር ቅዠት ስለ መሰላቸው አላመኑአቸውም። ነገር ግን ጴጥሮስ ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያም ሲደርስ ጐንበስ ብሎ በተመለከተ ጊዜ አስከሬኑ የተከፈነበትን ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀመጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤት ተመለሰ።

ሉቃስ 24:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፥ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት፤ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲገረሙ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው “ሕያዉን ለምን በሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ እዚህ የለም፤ ይልቁንም ተነሥቶአል። ገና በገሊላ እያለ የነገራችሁን አስታውሱ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው።” እነርሱም ቃሎቹንም አስታወሱ፤ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና፥ የያዕቆብም እናት ማርያም፥ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሌሎች ሴቶች ነበሩበት። ነገር ግን ይህ ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ።