ሉቃስ 23:39-43
ሉቃስ 23:39-43 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አብረው ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ወንበዴ፥ “አንተስ ክርስቶስ ከሆንህ ራስህን አድን፤ እኛንም አድነን” ብሎ ተሳደበ። ጓደኛውም መልሶ ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “አንተ በዚህ ፍርድ ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር አምላክህን አትፈራውምን? በእኛስ በሚገባ ተፈርዶብናል፤ እንደ ሥራችንም ፍዳችንን ተቀበልን፤ ይህ ግን ምንም የሠራው ክፉ ሥራ የለም።” ጌታችን ኢየሱስንም፥ “አቤቱ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ ዐስበኝ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።”
ሉቃስ 23:39-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ እየተሳደበ፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስኪ፣ ራስህንም እኛንም አድን” ይለው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።” ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ” አለው።
ሉቃስ 23:39-43 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ፦ አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።
ሉቃስ 23:39-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።” ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው።
ሉቃስ 23:39-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን፤” ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? እኛ ስለ አደረግነው የሚገባንን እየተቀበልን ነው፤ በእኛ ላይ የተወሰነው ትክክለኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም ክፋት አልሠራም፤” ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ፤” አለው።