ሉቃስ 23:27-38
ሉቃስ 23:27-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?” ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ። ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፤ አለቆችም፥ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ይዘብቱበት ነበር፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ አመጡለት። እንዲህም ይሉት ነበር፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህስ ራስህን አድን።” በራስጌውም ደብዳቤ ጻፉ፤ ጽሕፈቱም በሮማይስጥ፥ በጽርዕና በዕብራይስጥ ሆኖ “የአይሁድ ንጉሣቸው ይህ ነው” የሚል ነበር።
ሉቃስ 23:27-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያ ጊዜ፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?” ከርሱ ጋራ እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።
ሉቃስ 23:27-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን፦ በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም፦ ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን? ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ። ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ፦ ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው፦ አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ።
ሉቃስ 23:27-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ። ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ የአይሁድ አለቆችም “ሌሎችንስ አዳነ እንግዲህ እርሱ የተመረጠው የእግዚአብሔር መሲሕ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም እንዲሁ አፌዙበት፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ ሰጡት። እንዲሁም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ እስቲ ራስህን አድን!” ይሉት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍም በኢየሱስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖሩ።
ሉቃስ 23:27-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?” ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኰንኖቹም “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን፤” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም ወደ እርሱ ቀርበው፥ ሆምጣጤም አምጥተው “አንተ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን፤” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል በግሪክ፥ በሮማይስጥና በዕብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ።