ሉቃስ 23:26-49
ሉቃስ 23:26-49 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?” ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ። ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፤ አለቆችም፥ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ይዘብቱበት ነበር፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ አመጡለት። እንዲህም ይሉት ነበር፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህስ ራስህን አድን።” በራስጌውም ደብዳቤ ጻፉ፤ ጽሕፈቱም በሮማይስጥ፥ በጽርዕና በዕብራይስጥ ሆኖ “የአይሁድ ንጉሣቸው ይህ ነው” የሚል ነበር። አብረው ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ወንበዴ፥ “አንተስ ክርስቶስ ከሆንህ ራስህን አድን፤ እኛንም አድነን” ብሎ ተሳደበ። ጓደኛውም መልሶ ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “አንተ በዚህ ፍርድ ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር አምላክህን አትፈራውምን? በእኛስ በሚገባ ተፈርዶብናል፤ እንደ ሥራችንም ፍዳችንን ተቀበልን፤ ይህ ግን ምንም የሠራው ክፉ ሥራ የለም።” ጌታችን ኢየሱስንም፥ “አቤቱ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ ዐስበኝ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።” ቀትር በሆነ ጊዜም በስድስት ሰዓት ፀሐይ ጨለመ፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ። ፀሐዩም በጨለመ ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከመካከሉ ተቀደደ። ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ” ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር አይቶ፥ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ”ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው። ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። የሚያውቁት ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉትም ሴቶች በሩቁ ቆመው ይህን ያዩ ነበር።
ሉቃስ 23:26-49 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስንም ይዘው ሲወስዱት፣ ስምዖን የተባለውን የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው መስቀሉን አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ እንዲሄድ አስገደዱት። ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያ ጊዜ፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?” ከርሱ ጋራ እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር። ከተሰቀሉት ወንጀለኞችም አንዱ እየተሳደበ፣ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? እስኪ፣ ራስህንም እኛንም አድን” ይለው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “ተመሳሳይ ፍርድ እየተቀበልህ ሳለህ፣ ከቶ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።” ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ” አለው። ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤ የፀሓይ ብርሃን ተከልክሏልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀድዶ ለሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር።
ሉቃስ 23:26-49 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፦ መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን፦ በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም፦ ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን? ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ። ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ፦ ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው፦ አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ፦ አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር።
ሉቃስ 23:26-49 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት። ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ። ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ የአይሁድ አለቆችም “ሌሎችንስ አዳነ እንግዲህ እርሱ የተመረጠው የእግዚአብሔር መሲሕ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም እንዲሁ አፌዙበት፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ ሰጡት። እንዲሁም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ እስቲ ራስህን አድን!” ይሉት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍም በኢየሱስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖሩ። ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።” ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው። እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር።
ሉቃስ 23:26-49 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?” ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኰንኖቹም “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን፤” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም ወደ እርሱ ቀርበው፥ ሆምጣጤም አምጥተው “አንተ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን፤” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል በግሪክ፥ በሮማይስጥና በዕብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን፤” ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? እኛ ስለ አደረግነው የሚገባንን እየተቀበልን ነው፤ በእኛ ላይ የተወሰነው ትክክለኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም ክፋት አልሠራም፤” ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ፤” አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፤ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፤ ፀሐይም ጨለመ፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤” አለ። ይህንንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ፤” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ተመለሱ። እርሱን የሚያውቁት ሁሉ ግን ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ጭምር በሩቅ ቆመው ይህን እያዩ ነበር።