ሉቃስ 21:29-36
ሉቃስ 21:29-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ምሳሌም መስሎ እንዲህ አላቸው፥ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ። ለምልመውም ያያችኋቸው እንደ ሆነ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተም ይህ እንደ ሆነ ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ደረሰች ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪደረግ ድረስ ይህቺ ትውልድ አታልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፥ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች። በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ተዘረጋች ወጥመድ ትደርሳለችና። እንግዲህ ከዚህ ከሚመጣው ሁሉ በጸሎታችሁ ማምለጥ እንድትችሉ፥ በሰው ልጅ ፊትም እንድትቆሙ ሁልጊዜ ትጉ።”
ሉቃስ 21:29-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቀጥሎም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ፤ ቅጠሎቻቸው አቈጥቍጠው ስታዩ፣ በዚያ ጊዜ በጋ መቃረቡን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ዕወቁ። “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “እንግዲህ በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።”
ሉቃስ 21:29-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።
ሉቃስ 21:29-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስን ዛፍና የሌሎችንም ዛፎች ሁኔታ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ ቅጠሎቻቸው ሲያቈጠቊጡ ባያችሁ ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። በዚህ ዐይነት ይህ ሁሉ ነገር መሆን ሲጀምር ባያችሁ ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ መቃረብዋን ዕወቁ። “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይይዛችኋል። ያ ቀን በምድር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ በድንገት ያጠምዳቸዋል። ስለዚህ ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ለማምለጥ ኀይል እንድታገኙና በሰው ልጅ ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ዘወትር ትጉ።”
ሉቃስ 21:29-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህ ሲልም ምሳሌ ነገራቸው “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቁጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር፥ ስለ ኑሮም ማሰብ እንዳይዝል፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ሁልጊዜ ትጉ።”