ሉቃስ 21:10-15
ሉቃስ 21:10-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አላቸው፥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ ይነሣሉ። በየሀገሩ ታላቅ የምድር መነዋወጥና ራብ፥ በሰውም ላይ በሽታና ፍርሀት ይመጣል፤ በሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ አስቀድሞ ይይዙአችኋል፤ ወደ አደባባዮችም ይወስዱአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ያስሩአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ መሳፍንት ይወስዱአችኋል። ይህም በእነርሱ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። ዕወቁ፤ የምትናገሩትንም በልባችሁ አታስቡ። በእናንተ ላይ የሚነሡ ሊመልሱላችሁና ሊከራከሯችሁ እንዳይችሉ እኔ አፍንና ጥበብን እሰጣችኋለሁ።
ሉቃስ 21:10-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል። “ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሰዎች ያስሯችኋል፤ ያሳድዷችኋል፤ ወደ ምኵራቦችና ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧችኋል፤ በነገሥታትና በገዦች ፊት ለፍርድ ያቀርቧችኋል፤ ይህም ሁሉ በስሜ ምክንያት ይደርስባችኋል። ይህም ለመመስከር ጥሩ ዕድል ይሆንላችኋል። ስለዚህ ምን መልስ እንሰጣለን በማለት አስቀድማችሁ እንዳትጨነቁ ይህን ልብ በሉ፤ ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ ሊቋቋሙትና ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
ሉቃስ 21:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
ሉቃስ 21:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል። በየቦታውም ብርቱ የምድር መናወጥ፥ ራብና ወረርሽኝ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሰዎች እናንተን ይይዙአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ወደ ምኲራብና ወደ ወህኒ ቤትም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ይወስዱአችኋል። ይህም ስለ ስሜ ለመመስከር መልካም አጋጣሚ ይሆንላችኋል። ስለዚህ በሚቀርብባችሁ ክስ ስለምትሰጡት መልስ መጨነቅ እንደማይገባችሁ አስቀድማችሁ ልብ አድርጉ። ከጠላቶቻችሁ ማንም ሊቋቋመው ወይም ሊቃወመው የማይችለውን አንደበትና ጥበብ እኔ እሰጣችኋለሁ።
ሉቃስ 21:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይታያል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ጭነው ይይዟችኋል፤ ያሳድዱአችኋ፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህም የመከላከያ መልስ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ። ተቃዋሚዎቻችሁ በሙሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።