ሉቃስ 21:1-19
ሉቃስ 21:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሙዳየ ምጽዋቱ መባቸውን የሚያገቡ ባለጠጎችን አየ። አንዲት ድሃ መበለትም ሁለት መሐለቅ ስታስገባ አየ። እንዲህም አላቸው፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህቺ ድሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብዝታ ለእግዚአብሔር መባ አገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፋቸው ለእግዚአብሔር መባ አግብተዋልና፤ ይህቺ ግን ከድህነቷ ያላትን ጥሪቷን ሁሉ አገባች።” ስለ ቤተ መቅደስም ድንጋዩ ያማረ ነው፥ አሠራሩም ያጌጠ ነው የሚሉት ነበሩ። እንዲህም አላቸው፥ “ይህን ታያላችሁን? በእዚህ ቦታ ድንጋይ በድንጋይ ላይ የማይተውበትና ሳይፈርስ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል።” እነርሱም፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ መቼ ይደረጋል? ይህስ የሚሆንበት ጊዜው፥ ምልክቱስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ፤ ጊዜውም ደርሶአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና እንዳያስቱአችሁ ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርነትንና ጠብን፥ ክርክርንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን ወዲያው የሚፈጸም አይደለም።” እንዲህም አላቸው፥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ ይነሣሉ። በየሀገሩ ታላቅ የምድር መነዋወጥና ራብ፥ በሰውም ላይ በሽታና ፍርሀት ይመጣል፤ በሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ አስቀድሞ ይይዙአችኋል፤ ወደ አደባባዮችም ይወስዱአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ያስሩአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ መሳፍንት ይወስዱአችኋል። ይህም በእነርሱ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። ዕወቁ፤ የምትናገሩትንም በልባችሁ አታስቡ። በእናንተ ላይ የሚነሡ ሊመልሱላችሁና ሊከራከሯችሁ እንዳይችሉ እኔ አፍንና ጥበብን እሰጣችኋለሁ። ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ወዳጆቻችሁና ባልንጀሮቻችሁ አሳልፈው ይሰጡአችኋል። ሁሉም ስለ ስሜ ይጠሉአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም። ነገር ግን ከራስ ጠጕራችሁ አንዲቱ እንኳ አትጠፋም። በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ።
ሉቃስ 21:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ መባቸውን ሲጨምሩ አየ። ደግሞም አንዲት ድኻ መበለት ሁለት ትንንሽ የናስ ሳንቲሞች በዚያ ስትጨምር ተመለከተ። እንዲህም አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉም የበለጠ ጨመረች። እነዚህ ሰዎች የሰጡት ከትርፋቸው ላይ ሲሆን፣ እርሷ ግን የሰጠችው ከጕድለቷ ያላትን መተዳደሪያዋን በሙሉ ነው።” ከደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ በውብ ድንጋዮችና በስእለት ስጦታዎች እንዳማረ ሲነጋገሩ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ይህ የምታዩት ሁሉ ሳይፈርስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደ ተካበ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል።” እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? ደግሞም ይህ እንደሚሆን ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ በማለት፣ ደግሞም፣ ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እናንተ ግን እነርሱን አትከተሏቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሕዝብ ዐመፅ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ መሆን የሚገባው ነውና፤ መጨረሻው ግን ወዲያውኑ አይሆንም።” ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል። “ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሰዎች ያስሯችኋል፤ ያሳድዷችኋል፤ ወደ ምኵራቦችና ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧችኋል፤ በነገሥታትና በገዦች ፊት ለፍርድ ያቀርቧችኋል፤ ይህም ሁሉ በስሜ ምክንያት ይደርስባችኋል። ይህም ለመመስከር ጥሩ ዕድል ይሆንላችኋል። ስለዚህ ምን መልስ እንሰጣለን በማለት አስቀድማችሁ እንዳትጨነቁ ይህን ልብ በሉ፤ ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ ሊቋቋሙትና ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጕር አንዷ እንኳ አትጠፋም፤ ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።
ሉቃስ 21:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ። አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ። አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ፦ ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ። እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እንዲህም አለ፦ እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፦ እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
ሉቃስ 21:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች መባቸውን በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ውስጥ ሲጨምሩ አየ። እንዲሁም አንዲት ድኻ መበለት፥ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ስትጨምር አየ። እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት፥ ከሁሉም አብልጣ ሰጥታለች። እነርሱ የሰጡት ከሀብታቸው የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።” አንዳንድ ሰዎች፥ “ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት ውብ ነው? በከበሩ ድንጋዮችና ለእግዚአብሔር በቀረቡ ስጦታዎች አጊጦአል” እያሉ ይነጋገሩ ነበር። ኢየሱስ ግን “ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ አንድ ቀን ይፈራርሳሉ።” እነርሱም “መምህር ሆይ! ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን የምናውቅበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ! እነሆ፥ ጊዜው ቀርቦአል!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እነርሱን አትከተሉአቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሁከት በምትሰሙበት ጊዜም አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ይሁን እንጂ ፍጻሜው ወዲያውኑ አይሆንም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል። በየቦታውም ብርቱ የምድር መናወጥ፥ ራብና ወረርሽኝ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሰዎች እናንተን ይይዙአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ወደ ምኲራብና ወደ ወህኒ ቤትም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ይወስዱአችኋል። ይህም ስለ ስሜ ለመመስከር መልካም አጋጣሚ ይሆንላችኋል። ስለዚህ በሚቀርብባችሁ ክስ ስለምትሰጡት መልስ መጨነቅ እንደማይገባችሁ አስቀድማችሁ ልብ አድርጉ። ከጠላቶቻችሁ ማንም ሊቋቋመው ወይም ሊቃወመው የማይችለውን አንደበትና ጥበብ እኔ እሰጣችኋለሁ። ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ዘመዶቻችሁና ወዳጆቻችሁም ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተ አንዳንዶቹ ይገደላሉ። ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዲት እንኳ አትጠፋም። በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” አለ።
ሉቃስ 21:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዐይኑንም አንሥቶ በምጽዋት መቀበያ መባቸውን የሚያስቀምጡ ሀብታሞችን አየ። አንዲትም ድኻ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስታስቀምጥ አየና “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉ አብልጣ አስቀምጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ መዝገቡ አስቀምጠዋልና፤ እርሷ ግን እየጐደላት የነበራትን ንብረት ሁሉ ሰጠች፤” አለ። አንዳንዶቹም ስለ ቤተ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ “ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል፤” አለ። እነርሱም “መምህር ሆይ! እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሊሆን መቃረቡን የሚያሳየው ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እንዲህም አለ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤ ዘመኑም ቀርቦአል፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።” በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይታያል። ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ጭነው ይይዟችኋል፤ ያሳድዱአችኋ፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። ሰለዚህም የመከላከያ መልስ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ። ተቃዋሚዎቻችሁ በሙሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። ወላጆችና ወንድሞች፥ ዘመዶችና ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ በሁሉም ከስሜ የተነሣ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።