ሉቃስ 20:20-26
ሉቃስ 20:20-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእነርሱም ተለይተው ከሄዱ በኋላ፥ የሚጠባበቁትን አዘጋጁለት፤ በአነጋገሩም ያስቱት ዘንድ ወደ መኳንንትና ወደ መሳፍንት አሳልፈው ሊሰጡት ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰላዮችን ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት፥ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነት እንደምትናገርና እንደምታስተምር፥ ፊት አይተህም እንደማታዳላ፥ የእግዚአብሔርንም መንገድ በቀጥታ እንደምታስተምር እናውቃለን። ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል? ወይስ አይገባም?” ተንኰላቸውንም ዐውቆ፥ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ገንዘቡን አሳዩኝ” አላቸው። አምጥተውም አሳዩት፤ “መልኩ፥ ጽሕፈቱስ የማነው?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የቄሣር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፥ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። በሕዝቡም ሁሉ ፊት በአነጋገሩ ማሳሳት ተሳናቸው፤ መልሱንም አድንቀው ዝም አሉ።
ሉቃስ 20:20-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።
ሉቃስ 20:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። ጠይቀውም፦ መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ፦ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም፦ የቄሣር ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።
ሉቃስ 20:20-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ኢየሱስን ለመያዝ ምቹ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ለገዥው ሥልጣንና ፍርድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸውን የወንጀል ቃል ከእርሱ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ስለዚህ ቅን ሰዎች መስለው፥ በንግግሩ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። ሰላዮቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! አንተ የምትናገረውና የምታስተምረው እውነት መሆኑን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት ታስተምራለህ እንጂ ለማንም አታዳላም። እስቲ ንገረን! በሕጋችን መሠረት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ገንዘቡን አሳዩኝ፤ በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ስለዚህ በመልሱ ተደንቀው ዝም አሉ።
ሉቃስ 20:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በቅርብ እየተከታተሉትም ለገዢው ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። እነርሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “መምህር ሆይ! እውነትን እንደምትናገርና እንደምታስተምር በሰው ፊትም እንደማታደላ እናውቃለን፤ ይልቁንም በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ፤ ለቄሣር ግብር እንድንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። ሲመልሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በሕዝቡም ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።