ሉቃስ 20:1-26

ሉቃስ 20:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ህም በኋላ በአ​ንድ ቀን ሕዝ​ቡን በመ​ቅ​ደስ ሲያ​ስ​ተ​ም​ራ​ቸው፥ ወን​ጌ​ል​ንም ሲነ​ግ​ራ​ቸው፥ የካ​ህ​ናት አለ​ቆች፥ ጻፎ​ችና ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ተነ​ሡ​በት። “ይህን በማን ሥል​ጣን ታደ​ር​ጋ​ለህ? ይህ​ንስ እን​ድ​ታ​ደ​ርግ ማን ፈቀ​ደ​ልህ? እስኪ ንገ​ረን” አሉት። እር​ሱም መልሶ፥ “እኔም አን​ዲት ነገ​ርን እጠ​ይ​ቃ​ች​ኋ​ለሁ፤ ንገ​ሩኝ፤ የዮ​ሐ​ንስ ጥም​ቀት ከወ​ዴት ናት? ከሰ​ማይ ናትን? ወይስ ከሰው?” አላ​ቸው። እርስ በር​ሳ​ቸ​ውም እን​ዲህ ተባ​ባሉ፤ “ከሰ​ማይ ነው ብን​ለው ለምን አላ​መ​ና​ች​ሁ​ትም? ይለ​ናል። ከሰው ነው ብን​ለ​ውም ሕዝቡ ሁሉ በድ​ን​ጋይ ይወ​ግ​ሩ​ናል፤ ሁሉም ዮሐ​ንስ ነቢይ እንደ ሆነ አም​ነ​ው​በ​ታ​ልና። ከወ​ዴት እንደ ሆነች አና​ው​ቅም” ብለው መለ​ሱ​ለት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እኔም ይህን በማን ሥል​ጣን እን​ደ​ማ​ደ​ርግ አል​ነ​ግ​ራ​ች​ሁም” አላ​ቸው። ለሕ​ዝ​ቡም ይህን ምሳሌ ይመ​ስ​ል​ላ​ቸው ጀመረ፤ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ መጭ​መ​ቂ​ያም አስ​ቈ​ፈረ፤ ግን​ብም ሠራ​ለት፤ ለገ​ባ​ሮ​ችም ሰጥቶ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ ሳይ​መ​ለ​ስም ዘገየ። የመ​ከሩ ወራት በሆነ ጊዜም ወደ ገባ​ሮቹ፥ ከወ​ይኑ ፍሬ ይል​ኩ​ለት ዘንድ አገ​ል​ጋ​ዩን ላከ፤ ገባ​ሮቹ ግን አገ​ል​ጋ​ዩን ደብ​ድ​በው ባዶ እጁን ሰደ​ዱት። ዳግ​መ​ኛም ሌላ​ውን አገ​ል​ጋ​ዩን ላከ፤ እር​ሱ​ንም ደብ​ድ​በ​ውና አዋ​ር​ደው ባዶ እጁን ሰደ​ዱት። ደግሞ ሦስ​ተ​ኛ​ውን አገ​ል​ጋ​ዩን ላከ፤ እር​ሱ​ንም አቍ​ስ​ለው ሰደ​ዱት። የወ​ይኑ ባለ​ቤ​ትም፦ እን​ግ​ዲህ ምን ላድ​ርግ? ምና​ል​ባት እር​ሱን እንኳ አይ​ተው ያፍሩ እንደ ሆነ የም​ወ​ደ​ውን ልጄን ልላክ ብሎ ላከው። ገባ​ሮ​ቹም ባዩት ጊዜ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እን​ግ​ደ​ለ​ውና ርስ​ቱን እን​ው​ሰድ ብለው ተማ​ከሩ። ከወ​ይኑ ቦታም ወደ ውጭ አው​ጥ​ተው ገደ​ሉት። የወ​ይኑ ባለ​ቤት በመጣ ጊዜ እን​ግ​ዲህ ምን ያደ​ር​ጋ​ቸ​ዋል? ይመ​ጣል፤ እነ​ዚ​ያ​ንም ገባ​ሮች ይገ​ድ​ላ​ቸ​ዋል፤ ወይ​ኑ​ንም ለሌ​ሎች ገባ​ሮች ይሰ​ጣል፤” ቃሉ​ንም ሰም​ተው፥ “አይ​ሆ​ንም፤ እን​ዲህ አይ​ደ​ረ​ግም” አሉ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ተመ​ለ​ከ​ተና እን​ዲህ አላ​ቸው፤ “ግን​በ​ኞች የና​ቁ​አት ድን​ጋይ እር​ስዋ የማ​ዕ​ዘን ራስ ሆነች፥ የሚ​ለው ጽሑፍ ምን​ድ​ነው? በዚ​ያች ድን​ጋይ ላይ የወ​ደቀ ሁሉ ይቀ​ጠ​ቀ​ጣል፤ እር​ስ​ዋም የወ​ደ​ቀ​ች​በ​ትን ታደ​ቅ​ቀ​ዋ​ለች።” ያን ጊዜም የካ​ህ​ናት አለ​ቆ​ችና ጻፎች ሊይ​ዙት ወደዱ፤ ይህን ስለ እነ​ርሱ እንደ መሰለ ዐው​ቀ​ዋ​ልና፤ ነገር ግን ሕዝ​ቡን ፈሩ​አ​ቸው። ከእ​ነ​ር​ሱም ተለ​ይ​ተው ከሄዱ በኋላ፥ የሚ​ጠ​ባ​በ​ቁ​ትን አዘ​ጋ​ጁ​ለት፤ በአ​ነ​ጋ​ገ​ሩም ያስ​ቱት ዘንድ ወደ መኳ​ን​ን​ትና ወደ መሳ​ፍ​ንት አሳ​ል​ፈው ሊሰ​ጡት ራሳ​ቸ​ውን የሚ​ያ​መ​ጻ​ድቁ ሰላ​ዮ​ችን ወደ እርሱ ላኩ። እነ​ር​ሱም እን​ዲህ ብለው ጠየ​ቁት፥ “መም​ህር ሆይ፥ አንተ እው​ነት እን​ደ​ም​ት​ና​ገ​ርና እን​ደ​ም​ታ​ስ​ተ​ምር፥ ፊት አይ​ተ​ህም እን​ደ​ማ​ታ​ዳላ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም መን​ገድ በቀ​ጥታ እን​ደ​ም​ታ​ስ​ተ​ምር እና​ው​ቃ​ለን። ለቄ​ሣር ግብር መስ​ጠት ይገ​ባል? ወይስ አይ​ገ​ባም?” ተን​ኰ​ላ​ቸ​ው​ንም ዐውቆ፥ “ለምን ትፈ​ት​ኑ​ኛ​ላ​ችሁ? ገን​ዘ​ቡን አሳ​ዩኝ” አላ​ቸው። አም​ጥ​ተ​ውም አሳ​ዩት፤ “መልኩ፥ ጽሕ​ፈ​ቱስ የማ​ነው?” አላ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም፥ “የቄ​ሣር ነው” ብለው መለ​ሱ​ለት። እር​ሱም፥ “እን​ኪ​ያስ የቄ​ሣ​ርን ለቄ​ሣር፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስጡ” አላ​ቸው። በሕ​ዝ​ቡም ሁሉ ፊት በአ​ነ​ጋ​ገሩ ማሳ​ሳት ተሳ​ና​ቸው፤ መል​ሱ​ንም አድ​ን​ቀው ዝም አሉ።

ሉቃስ 20:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደ ሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስኪ መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?” እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” ስለዚህ፣ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ። በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት ባሪያውን ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ባሪያውን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት። ቀጥሎም ሌላ ባሪያውን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት። አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቍስለው ወደ ውጭ ጣሉት። “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስኪ ደግሞ የምወድደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ። “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤ ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል? መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ። ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጕሙ ምንድን ነው? በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቅቃል።” ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።

ሉቃስ 20:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና፦ እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት። መልሶም፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ብንል፦ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ። መልሰውም፦ ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። ኢየሱስም፦ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ። በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት። የወይኑም አትክልት ጌታ፦ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ። ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ፦ ይህስ አይሁን አሉ። እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ፦ እንግዲህ፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው? በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። ጠይቀውም፦ መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ፦ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም፦ የቄሣር ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።

ሉቃስ 20:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንድ ቀን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ሕዝቡን ያስተምርና ወንጌልንም ያበሥር በነበረበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጡ፤ እነርሱም “በል እስቲ ንገረን እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ በሉ እስቲ መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረን ወይስ ከሰው?” እነርሱም እንዲህ እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል፥ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ ሕዝቡ ሁሉም በዮሐንስ ነቢይነት ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” ስለዚህ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎች አከራየውና ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ ሳይመለስም ብዙ ጊዜ ቈየ። ወይኑ ባፈራ ጊዜ የወይኑ ተክል ባለቤት ከፍሬው ድርሻውን እንዲቀበልለት አንድ አገልጋይ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው፥ ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት፤ እንደገናም ሦስተኛ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደብድበው አቈሰሉትና አውጥተው ጣሉት። ከዚህም በኋላ የወይኑ ተክል ባለቤት፦ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልከዋለሁ፤ እርሱን ምናልባት ያከብሩት ይሆናል!’ አለ። ነገር ግን ገበሬዎቹ ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ ‘ይህ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል!’ ስለዚህ ልጁን ከወይኑ ተክል ቦታ ወደ ውጪ አውጥተው ገደሉት። ታዲያ፥ እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? የወይኑ ተክል ባለቤት ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጣል።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ታዲያ፥ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ምንን ያመለክታል? በዚያ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።” የሕግ መምህራንና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ ዐውቀው በዚያን ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ስለዚህ ኢየሱስን ለመያዝ ምቹ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ለገዥው ሥልጣንና ፍርድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸውን የወንጀል ቃል ከእርሱ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ስለዚህ ቅን ሰዎች መስለው፥ በንግግሩ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። ሰላዮቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! አንተ የምትናገረውና የምታስተምረው እውነት መሆኑን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት ታስተምራለህ እንጂ ለማንም አታዳላም። እስቲ ንገረን! በሕጋችን መሠረት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ገንዘቡን አሳዩኝ፤ በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ስለዚህ በመልሱ ተደንቀው ዝም አሉ።

ሉቃስ 20:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አንድ ቀንም ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና “እስኪ ንገረን፤ እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ነው የምታደርገው? ወይንስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ተናገሩት። ሲመልስም “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እስቲ ንገሩኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረች ወይስ ከሰዎች?” አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ በድንጋይ ይወግሩናል፤ ምክንያቱም ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉም ያምኑ ነበርና” አሉ። መልሰውም “ከየት እንደሆነ አናውቅም፤” አሉት። ኢየሱስም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው። ይህንንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ለወይን ጠባቂዎች አከራይቶ ለረጅም ጊዜ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ጊዜውም ሲደርስ ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ አገልጋይ ወደ ተከራዮቹ ላከ፤ ጠባቂዎቹ ግን ደበደቡትና ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት፥ አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። እንደገናም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይኸኛውን ደግሞ አቁሰለው አስወጡት። የወይኑ አትክልት ጌታም ‘ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል፤’ አለ። ተከራዮቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው፤’ አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? ይመጣል እነዚህንም ተከራዮች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።” ይህንንም በሰሙ ጊዜ “ይህስ በጭራሽ አይሁን፤” አሉ። እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ “እንግዲህ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ ነው የማዕዘን ራስ የሆነው፤’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት ነው? በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰባበራል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይጨፈልቀዋል፤” አለ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። በቅርብ እየተከታተሉትም ለገዢው ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። እነርሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “መምህር ሆይ! እውነትን እንደምትናገርና እንደምታስተምር በሰው ፊትም እንደማታደላ እናውቃለን፤ ይልቁንም በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ፤ ለቄሣር ግብር እንድንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። ሲመልሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በሕዝቡም ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።