ሉቃስ 2:1-24

ሉቃስ 2:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚ​ያም ወራት እን​ዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈ​ጠር ዘንድ ከአ​ው​ግ​ስ​ጦስ ቄሣር ትእ​ዛዝ ወጣ። ቄሬ​ኔ​ዎስ ለሶ​ርያ መስ​ፍን በነ​በረ ጊዜ ይህ የመ​ጀ​መ​ርያ ቈጠራ ሆነ። ሰው ሁሉ ሊቈ​ጠር ወደ​የ​ከ​ተ​ማው ሄደ። ዮሴ​ፍም ከገ​ሊላ አው​ራጃ ከና​ዝ​ሬት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ቤተ ልሔም ወደ​ም​ት​ባ​ለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱ ከዳ​ዊት ሀገ​ርና ከዘ​መ​ዶ​ቹም ወገን ነበ​ርና። ፀንሳ ሳለች ከእ​ጮ​ኛው ከማ​ር​ያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ሄደ። በዚያ ሳሉም የም​ት​ወ​ል​ድ​በት ቀን ደረሰ። የበ​ኵር ልጅ​ዋ​ንም ወለ​ደች፤ አውራ ጣቱ​ንም አሰ​ረ​ችው፤ በጨ​ር​ቅም ጠቀ​ለ​ለ​ችው፤ በበ​ረ​ትም አስ​ተ​ኛ​ችው፤ በማ​ደ​ር​ያ​ቸው ቦታ አል​ነ​በ​ራ​ቸ​ው​ምና። በዚያ ሀገር እረ​ኞች ነበሩ፤ ሌሊ​ቱ​ንም ተግ​ተው መን​ጋ​ቸ​ውን ይጠ​ብቁ ነበር። እነ​ሆም፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ በአ​ጠ​ገ​ባ​ቸው ቆመ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ብር​ሃን በዙ​ሪ​ያ​ቸው አበራ፤ ታላቅ ፍር​ሀ​ት​ንም ፈሩ። መል​አ​ኩም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እነሆ፥ ለእ​ና​ን​ተና ለሕ​ዝቡ ሁሉ ደስታ የሚ​ሆን ታላቅ የም​ሥ​ራች እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለ​ሁና አት​ፍሩ። እነሆ፥ ዛሬ በዳ​ዊት ከተማ መድ​ኅን ተወ​ል​ዶ​ላ​ች​ኋል፤ ይኸ​ውም ቡሩክ ጌታ ክር​ስ​ቶስ ነው። ለእ​ና​ን​ተም ምል​ክቱ እን​ዲህ ነው፦ ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፥ በጨ​ር​ቅም ተጠ​ቅ​ልሎ በበ​ረት ውስጥ ተኝቶ ታገ​ኛ​ላ​ቸሁ።” ድን​ገ​ትም ከዚያ መል​አክ ጋር ብዙ የሰ​ማይ ሠራ​ዊት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እያ​መ​ሰ​ገኑ መጡ። “ክብር ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሰ​ማ​ያት፥ ሰላ​ምም በም​ድር፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” ይሉ ነበር። ከዚ​ህም በኋላ መላ​እ​ክት ከእ​ነ​ርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በዐ​ረጉ ጊዜ እነ​ዚያ እረ​ኞች ሰዎች እርስ በር​ሳ​ቸው፥ “እስከ ቤተ ልሔም እን​ሂድ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የገ​ለ​ጠ​ል​ንን ይህን ነገር እን​ወቅ” አሉ። ፈጥ​ነ​ውም ሄዱ፤ ማር​ያ​ም​ንና ዮሴ​ፍን አገ​ኙ​አ​ቸው፤ ሕፃ​ኑ​ንም በበ​ረት ውስጥ ተኝቶ አገ​ኙት። በአ​ዩም ጊዜ የነ​ገ​ሩ​አ​ቸው ስለ​ዚህ ሕፃን እንደ ሆነ ዐው​ቀው አወሩ። የሰ​ሙ​ትም ሁሉ እረ​ኞቹ የነ​ገ​ሩ​አ​ቸ​ውን አደ​ነቁ። ማር​ያም ግን ይህን ሁሉ ትጠ​ብ​ቀው፥ በል​ብ​ዋም ታኖ​ረው ነበር። እረ​ኞ​ችም እንደ ነገ​ሩ​አ​ቸው ባዩ​ትና በሰ​ሙት ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እያ​ከ​በ​ሩና እያ​መ​ሰ​ገኑ ተመ​ለሱ። ስም​ንት ቀን በተ​ፈ​ጸመ ጊዜም ሕፃ​ኑን ሊገ​ዝ​ሩት ወሰ​ዱት፤ በማ​ኅ​ፀ​ንዋ ሳት​ፀ​ን​ሰው መል​አኩ እን​ዳ​ወ​ጣ​ለ​ትም ስሙን ኢየ​ሱስ አሉት። የመ​ን​ጻ​ታ​ቸ​ውም ወራት በተ​ፈ​ጸመ ጊዜ እንደ ሙሴ ሕግ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያቆ​ሙት ዘንድ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ወሰ​ዱት። “በኵር ሆኖ የሚ​ወ​ለድ ወንድ ልጅ ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ቀ​ደሰ ይባ​ላል” ተብሎ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሕግ እንደ ተጻፈ፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሕግ እንደ ታዘዘ ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የር​ግብ ግል​ገ​ሎች ስለ እርሱ መሥ​ዋ​ዕት አድ​ር​ገው ያቀ​ር​ቡ​ለት ዘንድ።

ሉቃስ 2:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዥ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ። ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከዕጮኛው ከማርያም ጋራ ነበር። በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤ የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው። በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋራ ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወድዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ። በሙሴ ሕግ መሠረት የመንጻታቸው ወቅት በተፈጸመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤ ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።

ሉቃስ 2:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ፦ የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ፦ ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።

ሉቃስ 2:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ በሮማውያን ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ እንዲቈጠሩ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ ታወጀ። ይህም የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ በተደረገ ጊዜ ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስሙን ለማስመዝገብ ወደ ትውልድ አገሩ ይሄድ ነበር። ዮሴፍም በትውልዱ የዳዊት ዘር ስለ ነበረ በገሊላ ምድር ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ወደ ዳዊት ከተማ፥ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ ሊመዘገብ የሄደውም ፀንሳ ከነበረችው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። በቤተልሔም ከተማ ሳሉ ማርያም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። በዚያም የበኲር ልጅዋን ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው። በዚያም አካባቢ፥ በሜዳ ላይ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። እነሆ፥ ለእነርሱ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ የጌታም የክብር ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እነሆ! ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ምልክቱም ይህ ነው፤ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት ውስጥ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኛላችሁ።” በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ጋር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፥ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!” ይሉ ነበር። መላእክቱ ተለይተዋቸው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፤ አሁን የተፈጸመውንና ጌታ የገለጠልንን ነገር እንይ” ተባባሉ። በፍጥነት ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑንም በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት። ሕፃኑንም ካዩ በኋላ መልአኩ ስለ እርሱ የነገራቸውን አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ ባወሩላቸው ነገር ተደነቁ። ማርያም ግን፥ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር። እረኞቹ፥ ሁሉ ነገር መልአኩ እንዳላቸው ሆኖ በማየታቸውና በመስማታቸው፥ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ፥ ወደ ስፍራቸው ተመለሱ። ከስምንት ቀን በኋላ ሕፃኑ በሚገረዝበት ሥነ ሥርዓት ላይ፥ ስሙ “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ። ይህም ገና ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ያወጣለት ስም ነው። በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ።

ሉቃስ 2:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያም ወራት የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲመዘገቡ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ምዝገባ ተከናወነ። ስለዚህ ሁሉም ለመመዝገብ፥ እያንዳንዱም ወደ የራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፥ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ሊመዘገብ ሄደ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።