ሉቃስ 15:11-19

ሉቃስ 15:11-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዳግ​መ​ኛም እን​ዲህ አለ፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበ​ሩት። ታናሹ ልጁም አባ​ቱን፦ ‘አባቴ ሆይ፥ ከገ​ን​ዘ​ብህ የሚ​ደ​ር​ሰ​ኝን ከፍ​ለህ ስጠኝ’ አለው፤ ገን​ዘ​ቡ​ንም ከፍሎ ሰጠው። ከጥ​ቂት ቀን በኋ​ላም ያ ትንሹ ልጁ ገን​ዘ​ቡን ሁሉ ሰብ​ስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚ​ያም በመ​ዳ​ራት እየ​ኖረ ገን​ዘ​ቡን ሁሉ በተነ፤ አጠ​ፋም። ገን​ዘ​ቡ​ንም ሁሉ በጨ​ረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እር​ሱም ተቸ​ገረ። ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአ​ንዱ ተቀ​ጠረ፤ እሪ​ያ​ዎ​ች​ንም ይጠ​ብቅ ዘንድ ወደ እር​ሻው ቦታ ሰደ​ደው። እሪ​ያ​ዎች ከሚ​መ​ገ​ቡት ተረ​ን​ቃ​ሞም ይጠ​ግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚ​ሰ​ጠው አል​ነ​በ​ረም። በል​ቡም እን​ዲህ ብሎ ዐሰበ፦ እህል የሚ​ተ​ር​ፋ​ቸው የአ​ባቴ ሠራ​ተ​ኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረ​ኃብ ልሞት ነው። ተነ​ሥቼ ወደ አባቴ ልሂ​ድና እን​ዲህ ልበ​ለው፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰ​ማ​ይም፥ በፊ​ት​ህም በደ​ልሁ። እን​ግ​ዲህ ወዲ​ህስ ልጅህ ልባል አይ​ገ​ባ​ኝም፤ ከአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ችህ እንደ አንዱ አድ​ር​ገኝ።’

ሉቃስ 15:11-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው። “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ። እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር። ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው። ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም። “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’

ሉቃስ 15:11-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ታናሽዮው አባቱን ‘አባባ፥ ከሀብትህ ከፍለህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። ስለዚህ አባትየው ሀብቱን ለሁለት ልጆቹ አካፈለ። ከጥቂት ቀን በኋላ ታናሽዮው ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም አገር ገንዘቡን ሁሉ በከንቱ አባከነ። ገንዘቡንም ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር ብርቱ ራብ በመግባቱ በችግር ላይ ወደቀ። ስለዚህ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ተጠጋ፤ ሰውየውም የዐሣማ እረኛ አደረገው። ዐሣማዎቹ ከሚመገቡት ብጣሪ ዐሠር ሆዱን ለመሙላት ይመኝ ነበር፤ ግን ይህንኑ እንኳ የሚሰጠው አልነበረም። በዚህ ጊዜ ልጁ ስሕተቱን ተገንዝቦ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘በአባቴ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ አገልጋዮች እንጀራ እስኪጠግቡ በልተው የሚተርፋቸው ስንት ናቸው! እኔ ግን እዚህ በረሀብ መሞቴ ነው፤ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ልጅ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከቅጥረኞች አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ልበለው።’