ሉቃስ 12:25-48
ሉቃስ 12:25-48 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእናንተስ ዐስቦ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚቻለው ማነው? ይህን ቀላሉን የማትችሉ ከሆነ በሌላው ለምን ትጨነቃላችሁ? እነሆ፥ አበባዎችን እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይፈትሉም፤ አይደክሙም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ዘመን ሁሉ ከእነርሱ እንደ አንዱ አልለበሰም። እነሆ፥ ዛሬ ያለውን፥ ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የአበባ አገዳ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያደርገው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ ለእናንተማ እንዴት አብልጦ አያደርግላችሁ? እናንተም የምትበሉትንና የምትጠጡትን አትፈልጉ፤ ወዲያና ወዲህም አትበሉ፤ አትጨነቁለትም። ይህን ሁሉ በውጭ ያሉ የዓለም አሕዛብ ይሹታልና፤ ለእናንተስ አባታችሁ ይህን ሁሉ እንደምትሹት ያውቃል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ ሹ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። “አንተ ታናሽ መንጋ፥ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥቱን ሊሰጣችሁ ወዶአልና። ሀብታችሁን ሸጣችሁ ምጽዋት ስጡ፤ ሌባ በማያገኝበት ነቀዝም በማያበላሽበት፥ የማያረጅ ከረጢት፥ የማያልቅም መዝገብ በሰማያት ለእናንተ አድርጉ። መዝገባችሁ ካለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና። “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን። እናንተም፥ በመጣና በር በመታ ጊዜ ወዲያው ይከፍቱለት ዘንድ ከሰርግ እስኪመለስ ጌታቸውን እንደሚጠብቁ ሰዎች ሁኑ። ጌታቸው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርጉና ሲተጉ የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ወገቡን ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ እየተመላለሰም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል ቢመጣና እንዲሁ ቢያገኛቸው እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው። ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ሌባ የሚመጣበትን ጊዜ ቢያውቅ ተግቶ በጠበቀ፥ ቤቱንም እንዲቈፍሩት ባልፈቀደም ነበር። እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ ባልጠረጠራችሁበት ሰዓት ይመጣልና።” ጴጥሮስም፥ “አቤቱ፥ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ነውን? ወይስ ለሁሉ ነው?” አለው። ጌታችንም እንዲህ አለው፥ “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በሀብቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል፤ ነገር ግን ያ ክፉ አገልጋይ በልቡ፦ ጌታዬ ቶሎ አይመጣም ቢል፥ በጌታው ቤት ያሉትንም ወንዶችንና ሴቶችን አገልጋዮች ሊደበድብና ሊያጕላላ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ ቢሰክርም፥ የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠረጠረው ዕለት፥ ባላወቀውም ሰዓት መጥቶ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ ዕድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርገዋል። የጌታውን ፈቃድ ዐውቆ እንደ ፈቃዱ የማይሠራና የማያዘጋጅ የዚያ አገልጋይ ቅጣቱ ብዙ ነው። ያላወቀ ግን ባይሠራም ቅጣቱ ጥቂት ነው፤ ብዙ ከሰጡት ብዙ ይፈልጉበታልና። ጥቂት ከሰጡትም ጥቂት ይፈልጉበታልና።
ሉቃስ 12:25-48 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ? “እስኪ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ አትሹ፤ አትጨነቁም፤ ይህንማ በዓለም ያሉ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው ይሻሉ፤ አባታችሁም እነዚህ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ይጨመሩላችኋል። “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ሀብት በሰማይ አከማቹ፤ ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይሆናልና። “በዐጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ የሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው ባሮች ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በዐጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ ባሮች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ ባለቤቱ ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል፤ እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።” ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ጭምር ነው?” አለው። ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማነው? ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ባሪያ እርሱ ምስጉን ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ ባሪያ፣ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት ብላቴኖችን ቢደበድብ፣ ደግሞም እንዳሻው ቢበላና ቢጠጣ መስከር ቢጀምር፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባላሰበው ቀንና ባልጠረጠረው ሰዓት ይመጣበታል፤ ስለዚህ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከማያምኑ ጋራ ያደርጋል። “የጌታውን ፍላጎት እያወቀ የማይዘጋጅና ፈቃዱን የማያደርግ ባሪያ እርሱ ክፉኛ ይገረፋል፤ ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራ ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል።
ሉቃስ 12:25-48 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። ጴጥሮስም፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን? አለው። ጌታም አለ፦ እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።
ሉቃስ 12:25-48 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለመሆኑ ከእናንተ መካከል በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ይህን ትንሹን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላው ነገር ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ ያጌጠ ልብስ አለበሰም። ታዲያ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ አስጊጦ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። ይህን ለማግኘትማ የዚህ ዓለም ሰዎችም ይጨነቁበታል፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። ይልቅስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “እናንተ እንደ ታናናሽ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ፤ የሰማይ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ፈቅዶአል። ያላችሁን ሁሉ ሸጣችሁ ገንዘቡን ለድኾች ስጡ፤ የማያረጅ የገንዘብ ቦርሳም አዘጋጅታችሁ ገንዘባችሁን ሌባ በማይደርስበት፥ ብል በማይበላበትና ከቶም በማያልቅበት ቦታ በመንግሥተ ሰማያት አስቀምጡ። ገንዘባችሁ ባለበት ቦታ ልባችሁም በዚያው ይሆናል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ባጭር ታጥቃችሁ ሁልጊዜ ለሥራ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን። በዚህም አኳኋን፥ ጌታቸው ከሠርግ ቤት መመለሱን የሚጠባበቁ አገልጋዮችን ምሰሉ፤ እነርሱ ጌታቸው በድንገት መጥቶ በሩን በሚያንኳኳበት ጊዜ ፈጥነው ለመክፈት ዝግጁዎች ናቸው። እነዚያ ጌታቸው ድንገት በመጣ ጊዜ፥ ነቅተው ሲጠብቁ የሚያገኛቸው አገልጋዮች እንዴት የተመሰገኑ ናቸው? በእውነት እላችኋለሁ፤ እርሱ ባጭር ታጥቆ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ጌታቸው በእኩለ ሌሊት ወይም ከእኩለሌሊት በኋላ በመጣ ጊዜ ነቅተውና ተግተው ሲጠብቁት የሚያገኛቸው አገልጋዮች የተባረኩ ናቸው። ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ አንድ ሰው ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት ቢያውቅ ኖሮ ሌባው ቤቱን ቆፍሮ እንዲገባ አይተወውም ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነውን? ወይስ ለሁሉም ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ታዲያ ቤተሰቦቹን በደንብ እንዲያስተዳድርለትና ለአገልጋዮቹም ምግባቸውን በተመደበው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጌታው የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማን ነው? ጌታው ከሄደበት ሲመለስ ልክ እንደታዘዘው ሲፈጽም የሚያገኘው አገልጋይ እንዴት የተባረከ ነው! በእውነት እላችኋለሁ፤ ጌታው ያን አገልጋይ የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ አድርጎ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ አገልጋይ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ በማሰብ እየበላ፥ እየጠጣ፥ እየሰከረም ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን መምታት ይጀምራል። ይሁን እንጂ ጌታው ባልታሰበበት ቀንና ባልተጠበቀበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ አገልጋዩንም በብርቱ ይቀጣዋል፤ ዕድሉንም ከወስላቶች ጋር እንዲሆን ያደርጋል። “የጌታውን ፈቃድ እያወቀ ያልተዘጋጀ፥ ወይም የጌታውን ትእዛዝ ያልፈጸመ አገልጋይ በብርቱ ይቀጣል። ነገር ግን የጌታውን ፈቃድ ባለማወቅ፥ ቅጣት የሚያመጣበትን ነገር አድርጎ ቢገኝ ቅጣቱ ይቀልለታል፤ ብዙ ከተሰጠው ሰው ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተሰጠው ሰው፥ ብዙ ይጠበቅበታል።”
ሉቃስ 12:25-48 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፤ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። “አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ፤ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን?” አለው። ጌታም አለ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ባርያ ግን ‘ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፤ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደሱም ፈቃድ ያላደረገ ያ ባርያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።