ሉቃስ 11:1-4
ሉቃስ 11:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአንዲት ቦታ ጸለየ፤ ጸሎቱን በጨረሰ ጊዜም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ አስተማራቸው ጸሎት አስተምረን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን። የዕለት ምግባችንን በየዕለቱ ስጠን። እኛም የበደለንን ሁሉ ይቅር እንድንል በደላችንን ይቅር በለን፤ አቤቱ፥ ወደ ፈተና አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ።”
ሉቃስ 11:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤ “ ‘አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤ በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና። ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።’ ”
ሉቃስ 11:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።
ሉቃስ 11:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም ባበቃ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው፥ አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን!” አለው። ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤ ‘[በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ! መንግሥትህ ትምጣ! የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን! እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በልልን፤ ወደ ፈተናም አታግባን’ [ከክፉ አድነን እንጂ።]”
ሉቃስ 11:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንዲሁ መጸለይን አስተምረን፤” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በማናቸውም ጊዜ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባት ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በለን፤ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለንና፤ ወደ ፈተናም አታግባን።’ ”