ሉቃስ 10:17-20
ሉቃስ 10:17-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነዚያም ሰባው ደስ ብሎአቸው ተመለሱና፥ “አቤቱ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ሰይጣንን ከሰማይ እንደ መብረቅ ሲወድቅ አየሁት። እነሆ፥ ጊንጦችንና እባቦችን፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ ትረግጡ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋችሁ፤ የሚጐዳችሁም ነገር የለም። ነገር ግን አጋንንት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ግን ስማችሁ በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
ሉቃስ 10:17-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
ሉቃስ 10:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።
ሉቃስ 10:17-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተላኩበት በጣም ደስ ብሎአቸው ተመለሱ፤ ወደ ኢየሱስም ቀርበው፦ “ጌታ ሆይ! በአንተ ስም አጋንንት እንኳ ታዘውልናል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ተወርውሮ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት፤ እነሆ! እባብንና ጊንጥን እንድትረግጡ፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ እንድትቋቋሙ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ አጋንንት ስለ ታዘዙላችሁ አትደሰቱ።”
ሉቃስ 10:17-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሰባዎቹም ሰዎች በደስታ ተመልሰው፦ “ጌታ ሆይ! አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም ምንም ነገር የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንም ስማችሁ በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”