ሉቃስ 10:1-24

ሉቃስ 10:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ህም በኋላ ጌታ​ችን ሌሎች ሰባ ሰዎ​ችን መረጠ፤ ሁለት ሁለት አድ​ር​ጎም ሊሄ​ድ​በት ወደ አለው ከተ​ማና መን​ደር በፊቱ ላካ​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አላ​ቸው፥ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራ​ተ​ኛው ግን ጥቂት ነው፤ እን​ግ​ዲህ ለመ​ከሩ ሠራ​ተኛ ጨምሮ ይልክ ዘንድ ባለ መከ​ሩን ለም​ኑት። ሂዱ፤ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተ​ኵ​ላ​ዎች መካ​ከል እል​ካ​ች​ኋ​ለሁ። ከረ​ጢ​ትም፥ ስል​ቻም፥ ጫማም፥ ምንም ምን አት​ያዙ፤ በመ​ን​ገ​ድም ማን​ንም ሰላም አት​በሉ። ወደ ገባ​ች​ሁ​በት ቤትም አስ​ቀ​ድ​ማ​ችሁ ‘ለዚህ ቤት ሰዎች ሰላም ይሁን’ በሉ። በዚ​ያም የሰ​ላም ልጅ ቢኖር ሰላ​ማ​ችሁ ያድ​ር​በ​ታል፤ ያለ​ዚያ ግን ሰላ​ማ​ችሁ ይመ​ለ​ስ​ላ​ች​ኋል። በዚ​ያም ቤት ተቀ​መጡ፤ ከእ​ነ​ርሱ የተ​ገ​ኘ​ው​ንም ብሉ፥ ጠጡም፤ ለሠ​ራ​ተኛ ዋጋው ይገ​ባ​ዋ​ልና፤ ከቤ​ትም ወደ ቤት አት​ሂዱ። ወደ ማና​ቸ​ውም ከተማ ብት​ገቡ፥ የዚያ ከተማ ሰዎ​ችም ቢቀ​በ​ሉ​አ​ችሁ ያቀ​ረ​ቡ​ላ​ች​ሁን ብሉ። በው​ስ​ጥዋ የሚ​ገ​ኙ​ትን ድው​ያ​ን​ንም ፈውሱ፤ ‘የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መን​ግ​ሥት ወደ እና​ንተ ቀር​ባ​ለች’ በሉ​አ​ቸው። ነገር ግን ወደ ማና​ቸ​ውም ከተማ ብት​ገቡ፥ የዚ​ያች ከተማ ሰዎ​ችም ባይ​ቀ​በ​ሉ​አ​ችሁ ወደ አደ​ባ​ባ​ይዋ ወጥ​ታ​ችሁ የእ​ግ​ራ​ች​ሁን ትቢያ አራ​ግፉ። እን​ዲ​ህም በሉ፦ ከከ​ተ​ማ​ችሁ የተ​ጣ​በ​ቀ​ብ​ንን ትቢያ እን​ኳን እና​ራ​ግ​ፍ​ላ​ች​ኋ​ለን፤ ነገር ግን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት ወደ እና​ንተ እንደ ቀረ​በች ይህን ዕወቁ። በፍ​ርድ ቀን ሰዶም ከዚ​ያች ከተማ ይልቅ እን​ደ​ም​ት​ሻል ይቅ​ር​ታ​ንም እን​ደ​ም​ታ​ገኝ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ። “ኮራዚ ወዮ​ልሽ! ቤተ ሳይዳ ወዮ​ልሽ! በእ​ና​ንተ የተ​ደ​ረ​ገው ተአ​ም​ራት በጢ​ሮ​ስና በሲ​ዶና ተደ​ርጎ ቢሆን ቀድሞ ማቅ ለብ​ሰው አመ​ድም ነስ​ን​ሰው በተ​ቀ​መጡ ንስ​ሓም በገቡ ነበር። ነገር ግን ጢሮ​ስና ሲዶና ከእ​ና​ንተ ይልቅ በፍ​ርድ ቀን ይቅ​ር​ታን ያገ​ኛሉ። አን​ቺም ቅፍ​ር​ና​ሆም እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወ​ር​ጃ​ለሽ። “እና​ን​ተን የሚ​ሰማ እኔን ይሰ​ማል፤ እና​ን​ተ​ንም እንቢ የሚል እኔን እንቢ ይላል፤ እኔ​ንም እንቢ የሚል የላ​ከ​ኝን እንቢ ይላል፤ እኔ​ንም የሚ​ሰማ የላ​ከ​ኝን ይሰ​ማል።” እነ​ዚ​ያም ሰባው ደስ ብሎ​አ​ቸው ተመ​ለ​ሱና፥ “አቤቱ፥ አጋ​ን​ንት ስንኳ በስ​ምህ ተገ​ዙ​ልን” አሉት። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ሰይ​ጣ​ንን ከሰ​ማይ እንደ መብ​ረቅ ሲወ​ድቅ አየ​ሁት። እነሆ፥ ጊን​ጦ​ች​ንና እባ​ቦ​ችን፥ የጠ​ላ​ት​ንም ኀይል ሁሉ ትረ​ግጡ ዘንድ ሥል​ጣ​ንን ሰጠ​ኋ​ችሁ፤ የሚ​ጐ​ዳ​ች​ሁም ነገር የለም። ነገር ግን አጋ​ን​ንት ስለ ተገ​ዙ​ላ​ችሁ በዚህ ደስ አይ​በ​ላ​ችሁ፤ ግን ስማ​ችሁ በሰ​ማ​ያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበ​ላ​ችሁ።” በዚ​ያች ሰዓ​ትም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ደስ አለው፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “የሰ​ማ​ይና የም​ድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከዐ​ዋ​ቂ​ዎ​ችና ከአ​ስ​ተ​ዋ​ዮች ሰው​ረህ ለሕ​ፃ​ናት ስለ​ገ​ለ​ጥ​ኸው አመ​ሰ​ግ​ን​ሃ​ለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃ​ድህ በፊ​ትህ እን​ዲሁ ሆኖ​አ​ልና። ሁሉ ከአ​ባቴ ዘንድ ተሰ​ጠኝ፤ ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚ​ያ​ውቅ የለም፤ አብም ማን እንደ ሆነ ከወ​ልድ በቀር የሚ​ያ​ውቅ የለም። ወልድ ግን ለወ​ደ​ደው ይገ​ል​ጥ​ለ​ታል።” ተመ​ል​ሶም ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን ለብ​ቻ​ቸው አድ​ርጎ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ የም​ታ​ዩ​ትን የሚ​ያዩ ዐይ​ኖች ብፁ​ዓን ናቸው። ብዙ ነቢ​ያ​ትና ነገ​ሥ​ታት እና​ንተ የም​ታ​ዩ​ትን ሊያዩ ተመኙ፤ አላ​ዩ​ምም፤ እና​ንተ የም​ት​ሰ​ሙ​ት​ንም ሊሰሙ ተመኙ፥ አል​ሰ​ሙም።”

ሉቃስ 10:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ ለምኑት። ሂዱ፤ እንግዲህ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ኰረጆ ወይም ከረጢት ወይም ጫማ አትያዙ፤ በመንገድ ላይም ለማንም ሰላምታ አትስጡ። “ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ፤ የሰላም ሰው በዚያ ካለ፣ ሰላማችሁ ያርፍበታል፤ አለዚያም ሰላማችሁ ለእናንተው ይመለሳል። ያቀረቡላችሁን ሁሉ እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያ ቤት ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ። “ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ። በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው። ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ፤ ‘ለማስጠንቀቂያ እንዲሆናችሁ በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች ይህን ዕወቁ።’ እላችኋለሁ፤ በዚያ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ልትዪ ነውን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።” ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና። “ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።”

ሉቃስ 10:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው። አላቸውም፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ። ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ። ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው። ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ፦ ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ። እላችኋለሁ፥ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። ወዮልሽ ኮራዚን፥ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው በአመድም ተቀምጠው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና፦ የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው፦ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም አለ።

ሉቃስ 10:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ጌታ፥ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መረጠ፤ እርሱ ሊሄድበት ወደአሰበውም ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። እንዲህም አላቸው፦ “እነሆ፥ መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሥራ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት። እንግዲህ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ለመንገዳችሁ ምንም አትያዙ፤ የገንዘብ ቦርሳም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ ጫማም ቢሆን አትያዙ፤ ከሰው ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ በመንገድ ላይ ቆማችሁ ጊዜ አታጥፉ። በገባችሁበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፥’ በሉ፤ ሰላም ወዳድ ሰው በዚያ ቤት ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለበለዚያ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። ለሠራተኛ ደመወዝ ይገባዋል፤ ስለዚህ በገባችሁበት ቤት ያቀረቡላችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ ቈዩ፤ ከቤት ወደ ቤትም አትዘዋወሩ። በማናቸውም ከተማ ስትገቡና ሰዎችም ሲቀበሉአችሁ የሚያቀርቡላችሁን ብሉ። በዚያችም ከተማ የሚገኙትን በሽተኞች ፈውሱ፤ ለሕዝቡም፦ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች፤’ እያላችሁ ተናገሩ። ነገር ግን በማናቸውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ የማይቀበሉአችሁ ቢሆን ወደ ከተማይቱ አደባባይ ውጡና እንዲህ በሉአቸው፦ ‘እነሆ፥ በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ዕወቁ።’ በፍርድ ቀን ከዚህች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ከተማ ቅጣቱ ይቀልላታል እላችኋለሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ ላይ ተቀምጠው፥ ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር። ስለዚህ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም! እስከ ሰማይ ከፍ ለማለት ፈልገሻልን? ታዲያ ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ።” እንደገናም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔን የማይቀበልም የላከኝን አይቀበልም፤” አላቸው። ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተላኩበት በጣም ደስ ብሎአቸው ተመለሱ፤ ወደ ኢየሱስም ቀርበው፦ “ጌታ ሆይ! በአንተ ስም አጋንንት እንኳ ታዘውልናል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ተወርውሮ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት፤ እነሆ! እባብንና ጊንጥን እንድትረግጡ፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ እንድትቋቋሙ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ አጋንንት ስለ ታዘዙላችሁ አትደሰቱ።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በቅዱስ መንፈሱ ተደስቶ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህንን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ላልተማሩት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ፥ አባት ሆይ፥ ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። “ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድ ማን መሆኑን ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም አብ ማን መሆኑን ከወልድ በቀር ወይም ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት ሰው በቀር ሌላ ማንም የሚያውቅ የለም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መለስ ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ የተባረኩ ናቸው። በእውነቱ ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም።”

ሉቃስ 10:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መረጠ፤ ሁለት ሁለትም አድርጎ ራሱ ሊሄድበት ወደአሰበው ከተማና ስፍራ ሁሉ አስቀድሞ ላካቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት። እንግዲህ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ቦርሳም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድ ላይ ለማንም ሰላምታን አትስጡ። ወደምትገቡበትም ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፤’ በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ያድርበታል፤ ካልሆነ ግን ይመለስላችኋል። ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋልና እነርሱ የሚሰጡአችሁን እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያው ቤት ተቀመጡ። ከቤት ወደ ቤት አትዘዋወሩ። ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ የሚያቀርቡላችሁን ብሉ፤ በእርሷም ያሉትን ሕሙማንን ፈውሱና፦ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቦአል፤’ በሉአቸው። ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባዮቹዋ ወጥታችሁ እንዲህ በሉ፦ ‘ከከተማችሁም በእግሮቻችን ላይ የተጣበቀብንን ትቢያ ሳይቀር እናንተን በመቃወም እናራግፋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦአል፥ ይህን እወቁ።’ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል እላችኋለሁ። “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው በአመድ ላይም ተቀምጠው፥ ገና ድሮ፥ ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ የምትደረጊ ይመስልሻልን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። “የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።” ሰባዎቹም ሰዎች በደስታ ተመልሰው፦ “ጌታ ሆይ! አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም ምንም ነገር የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንም ስማችሁ በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ! መልካም ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድንም ማን እንደሆነ ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ አብንም ማን እንደሆነ ከወልድ በቀር ወልድም በፈቃዱ ከሚገልጥለት ሰው በቀር ማንም የሚያውቅ የለም።” ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሳሉ ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፦ “የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው። እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙምም።”