ሉቃስ 1:5-13
ሉቃስ 1:5-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ሥርዐትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ። ልጅም አልነበራቸውም፤ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፤ ሁለቱም አርጅተው ነበር፤ ዘመናቸውም አልፎ ነበር። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራው የክህነትን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥ ካህናት እንደሚያደርጉት የሚያጥንበት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸልዩ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክም በዕጣን መሠውያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሀትም ረዓድም ወረደበት። መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
ሉቃስ 1:5-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ነገድ ስትሆን፣ ስሟም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
ሉቃስ 1:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
ሉቃስ 1:5-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሄሮድስ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ ከአብያ የክህነት አገልግሎት ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር። እርሱም ከአሮን ዘር የምትወለድ ኤልሳቤጥ የምትባል ሚስት ነበረችው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የጌታንም ትእዛዝና ሥርዓት ያለ ነቀፋ ይጠብቁ ነበር። ኤልሳቤጥ መኻን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ደግሞ ሁለቱም በጣም አርጅተው ነበር። በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ።
ሉቃስ 1:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ።