ዘሌዋውያን 26:14-21
ዘሌዋውያን 26:14-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዐቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ሰውነታችሁ ፍርዴን ብትሰለች፥ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሀትን፥ ክሳትንም፥ ዐይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያጠፋ ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሏችሁም ያሸንፉአችኋል። ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኀጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ መቅሠፍትን እጨምራለሁ። የትዕቢታችሁን ስድብ አጠፋለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፤ የዱር ዛፎችም ፍሬያቸውን አይሰጡም። “ከዚያም በኋላ በእንቢተኝነት ብትሄዱብኝ፥ ልትሰሙኝም ባትፈቅዱ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።
ዘሌዋውያን 26:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትእዛዞች ባትጠብቁ፣ ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዞቼንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣ እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ በሽታ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኵሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ። “ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤ የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና። “ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ።
ዘሌዋውያን 26:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥ እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም። በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።
ዘሌዋውያን 26:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ባትፈጽሙ፥ ትእዛዞቼን ባትጠብቁ፥ ሕግጋቴን ብትንቁ፥ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱና ሥርዓቶቼን ብትጸየፉ፥ የሚከተለውን አመጣባችኋለሁ፦ ታላቅ ድንጋጤን፥ ክሳትን፥ ዐይንን የሚያፈዝና ሰውነትን የሚያመነምን የንዳድ በሽታ አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁ የሚበሉት ስለ ሆነ ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። ፊቴን በቊጣ እመልስባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ትሸነፋላችሁ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። “ይህም ሁሉ ከደረሰባችሁ በኋላ እንኳ የማትታዘዙኝ ከሆናችሁ፥ በእናንተ ላይ የማመጣውን ቅጣት ሰባት ጊዜ እጥፍ እንዲበዛ አደርገዋለሁ። እልኸኛ ትዕቢታችሁን አዋርዳለሁ፤ ሰማይን እንደ ብረት አጠንክሬ ዝናብ እንዳይዘንብ አደርጋለሁ፤ ምድርንም በድርቅ መትቼ እንደ ነሐስ የጠጠረች አደርጋለሁ። ምድራችሁ ሰብልን ዛፎቻችሁም ፍሬን ስለማይሰጡ በከንቱ ትደክማላችሁ። “እኔን በመቃወም ከቀጠላችሁና እኔን የማትሰሙኝ ከሆነ፥ እንደ ኃጢአታችሁ ብዛት ሰባት ጊዜ እጥፍ የሆነ መቅሠፍት አመጣባችኋለሁ።
ዘሌዋውያን 26:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዓቴንም ባትቀበሉ፥ ነፍሳችሁም ፍርዴን በመጸየፉዋ ምክንያት ትእዛዛቴን ሳታደርጉ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፥ እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ነፍስን የሚያኮስስና ዓይንን የሚያፈዝዝ ክሳትና ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ይበሉታልና ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። ፊቴንም አጠቊርባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትሸነፋላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እነዚህም ነገሮች ተደርገውባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ ጨምሬ ዳግመኛ እቀጣችኋለሁ። የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጉልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም የተትረፈረፈውን ምርትዋን አትሰጥም፥ የምድሪቱም ዛፎች ፍሬያቸውን አይሰጡም። “እኔንም በመቃወም ብትሄዱ ልትሰሙኝም ባትፈልጉ፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ ቸነፈር እጨምርባችኋለሁ።