ዘሌዋውያን 19:19-37

ዘሌዋውያን 19:19-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ሥር​ዐ​ቴን ጠብቁ፤ በበ​ሬህ በባ​ዕድ ቀን​በር አት​ረስ፤ በወ​ይን ቦታህ የተ​ለ​ያየ ዘር አት​ዝራ፤ ከሁ​ለት ዐይ​ነት ነገር የተ​ሠራ ልብስ ኀፍ​ረት ነውና አት​ል​በስ። “ማና​ቸ​ውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እር​ስ​ዋም ለባል የተ​ሰ​ጠች፥ ዋጋ​ዋም ያል​ተ​ከ​ፈለ፥ አር​ነት ያል​ወ​ጣች ብት​ሆን፥ ቅጣት አለ​ባ​ቸው፤ አር​ነት አል​ወ​ጣ​ች​ምና አይ​ገ​ደ​ሉም። እር​ሱም የበ​ደ​ሉን መሥ​ዋ​ዕት አውራ በግ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ ምስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ ያመ​ጣል። ካህ​ኑም ስለ ሠራው ኀጢ​አት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በበ​ደል መሥ​ዋ​ዕት በግ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ የሠ​ራ​ውም ኀጢ​አት ይቀ​ር​ለ​ታል። “አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ​ሚ​ሰ​ጣ​ችሁ ምድር በገ​ባ​ችሁ ጊዜ፥ የሚ​በላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተ​ከ​ላ​ች​ሁም ጊዜ ከር​ኵ​ሰቱ ሁሉ ታጠ​ሩ​ታ​ላ​ችሁ፤ የሦ​ስቱ ዓመት ፍሬም ርኩስ ነው፤ አይ​በ​ላም። በአ​ራ​ተ​ኛ​ውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ጋና ቅዱስ ይሁን። በአ​ም​ስ​ተ​ኛ​ውም ዓመት ፍሬ​ውን ብሉ፤ ፍሬ​ውም ይበ​ዛ​ላ​ች​ኋል፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝ። “በተ​ራራ ላይ አት​ብሉ፤ አት​ር​ከሱ፥ በወ​ፍም አታ​ሟ​ርቱ። የራስ ጠጕ​ራ​ች​ሁ​ንም ዙሪ​ያ​ውን አት​ከ​ር​ክ​ሙት፤ ጢማ​ች​ሁ​ንም አት​ላጩ። ሰው ቢሞት ምላጭ ወደ ሥጋ​ችሁ አታ​ቅ​ርቡ፤ ገላ​ች​ሁ​ንም አት​ን​ቀ​ሱት፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝ። “ምድ​ሪቱ ከግ​ል​ሙ​ትና፥ ከር​ኵ​ሰ​ትም እን​ዳ​ት​ሞላ ሴት ልጅ​ህን ታመ​ነ​ዝር ዘንድ አታ​ር​ክ​ሳት። ሰን​በ​ታ​ቴን ጠብቁ፤ መቅ​ደ​ሴ​ንም አክ​ብሩ፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝና። “ወደ መና​ፍ​ስት ጠሪ​ዎ​ችና ወደ ጠን​ቋ​ዮች አት​ሂዱ፤ እን​ዳ​ት​ረ​ክ​ሱ​ባ​ቸ​ውም አት​ፈ​ል​ጉ​አ​ቸው፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝና። “በሽ​በ​ታሙ ፊት ተነሣ፤ ሽማ​ግ​ሌ​ው​ንም አክ​ብር፤ አም​ላ​ክ​ህን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ፍራ፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝና። “በሀ​ገ​ራ​ችሁ ውስጥ እን​ግዳ ከእ​ና​ንተ ጋር ቢቀ​መጥ ግፍ አታ​ድ​ር​ጉ​በት። እና​ንተ በግ​ብፅ ምድር እን​ግ​ዶች ነበ​ራ​ች​ሁና፤ ወደ እና​ንተ የመጣ እን​ግዳ እንደ ሀገር ልጅ ይሁ​ን​ላ​ችሁ፤ እር​ሱን እንደ ራሳ​ችሁ ውደ​ዱት፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝና። “በፍ​ርድ፥ በመ​ለ​ካ​ትም፥ በመ​መ​ዘ​ንም፥ በመ​ስ​ፈ​ርም ዐመፃ አታ​ድ​ርጉ። የእ​ው​ነ​ትም ሚዛን፥ የእ​ው​ነ​ትም መመ​ዘኛ፥ የእ​ው​ነ​ትም የፈ​ሳሽ መስ​ፈ​ሪያ ይሁ​ን​ላ​ችሁ፤ ከግ​ብፅ ምድር ያወ​ጣ​ኋ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ እኔ ነኝ። ሕጌን ሁሉ፥ ትእ​ዛ​ዜ​ንም ሁሉ ጠብቁ፤ አድ​ር​ጉ​ትም፤ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ካ​ችሁ ነኝና።”

ዘሌዋውያን 19:19-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ። “ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል። “ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ። “ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም። ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ያምጣ። ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። “ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት ያልተገረዘ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ። በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። በዐምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ። “ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ። “ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ። “ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት። “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ ዐብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤ ዐብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብጽ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭበርብሩ። የጽድቅ መለኪያ፣ የጽድቅ ሚዛን፣ የጽድቅ የኢፍ መስፈሪያ፣ የጽድቅ የሂን መስፈሪያም ይኑራችሁ። ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

ዘሌዋውያን 19:19-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። ማናቸውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እርስዋም ለባል የተሰጠች ዋጋዋም ያልተከፈለ አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ቅጣት አለባቸው፤ አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል። ወደ አገሩም በገባችሁ ጊዜ፥ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁም ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት እንዳልተገረዘ ይሆንላችኋል፤ አይበላም። የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቅዱስ ይሁን። ፍሬውም ይበዛላችሁ ዘንድ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ፤ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ። የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት። ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኩሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቍዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ። የእውነትም ሚዛን፥ የእውነትም መመዘኛ፥ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፥ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ። ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

ዘሌዋውያን 19:19-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ አንዱን እንስሳ ከሌላው ጋር አታዳቅል፥ በአንድ እርሻ ላይ ሁለት ዐይነት እህል አትዝራ፥ ከሁለት ዐይነት ነገር ተፈትሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ። “አንድ ሰው ልጃገረድ የሆነች አገልጋዩን ለሌላ ሰው ቊባት ትሆን ዘንድ ለመሸጥ ካስማማ በኋላ ገዢው ገንዘቡን ከፍሎ ከመጨረሱ በፊት ሻጩ ከልጃገረዲቱ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ ሁለቱም ይቀጣሉ፤ ሆኖም እርስዋ ገና ነጻ ያልወጣች አገልጋዩ ስለ ሆነች የሞት ቅጣት አይፈጸምባቸውም። ይህን በደል የፈጸመ ሰው ለበደል ስርየት መሥዋዕት አድርጎ አንድ የበግ አውራ ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ እኔ ያምጣ። ካህኑም የዚያን ሰው ኃጢአት በአውራ በጉ የበደል መሥዋዕት ያስተሰርይለታል፤ እኔ እግዚአብሔርም በደሉን ይቅር እለዋለሁ። “ወደ ከነዓን ምድር ገብታችሁ ማንኛውንም ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ እስከ መጀመሪያው ሦስት ዓመት ድረስ የሚሰጠውን ፍሬ መብላት የተከለከለ መሆኑን አስታውሱ። በእነዚህም ዓመቶች ውስጥ ፍሬው አይበላም። በአራተኛው ዓመት እኔን እግዚአብሔርን ታመሰግኑበት ዘንድ ለእኔ የተለየ ስጦታ ይሁን። በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ ይህን ብታደርጉ ዛፎቻችሁ በየጊዜው የሚሰጡአችሁ ፍሬ ይበልጥ እየበዛ ይሄዳል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ደም ያለበትን ሥጋ አትብሉ፤ የአስማትን ነገር አትከተሉ፤ የራስ ጠጒራችሁን ዙሪያውን አትከርክሙት፤ ጢማችሁን አሳጥራችሁ አትቊረጡት፤ በሰውነታችሁ ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ ወይም ለሙታን በማዘን ሰውነታችሁን አትቈራርጡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ምድሪቱ በዝሙትና በርኲሰት እንዳትሞላ ታመነዝር ዘንድ ለሴት ልጅህ አትፍቀድላት። ሰንበትን ጠብቁ፤ መቅደሴን አክብሩ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ከሙታን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ከጠንቋዮች ምክር አትጠይቁ፥ ይህን ብታደርጉ የረከሳችሁ ትሆናላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎች ሲመጡ ስታይ ከተቀመጥክበት በመነሣት አክብራቸው፤ እኔን አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “በምድራችሁ ከእናንተ ጋር ባዕዳን ቢኖሩ አትበድሉአቸው፤ ለእስራኤላዊ ወገናችሁ በምታደርጉት ዐይነት መልካም ነገር አድርጉላቸው፤ እንደ ራሳችሁም አድርጋችሁ ውደዱአቸው፤ እናንተም ከዚህ በፊት በግብጽ ምድር ባዕዳን እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “በርዝመት መለኪያ፥ በክብደት መለኪያና በመስፈሪያ አትበድሉ። ትክክለኞች የሆኑ ሚዛኖች ማለት የርዝመት፥ የክብደትና የፈሳሽ መለኪያዎች ይኑሩአችሁ፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ለሰጠኋችሁ ሕግና ትእዛዝ ሁሉ ታማኞች ሁኑ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

ዘሌዋውያን 19:19-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህን ከሌላ ዓይነት ዘር ጋር አታዳቅል፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።” “ማናቸውም ሰው በባርነት ሥር ካለች ሴት ጋር ቢተኛ፥ እርሷም ለሌላ ሰው ታጭታ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ያልተዋጀች ወይም አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ይህ አድራጎት ቅጣት ይረኖረዋል፤ ሆኖም አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ ጌታ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በጌታ ፊት የበደል መሥዋዕት በሆነው በግ ለእርሱ ያስተሰርይለታል፥ የሠራውም ኃጢአት ይቅር ይባላል። “ወደ ምድሪቱም ገብታችሁ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት ለእናንተ እንዳልተገረዘ ይሆናል፤ አይበላም። የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለጌታ ምስጋና የተለየ ይሆናል። የተትረፈረፈም ፍሬ አብዝተው እንዲሰጡዋችሁ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “ከደሙ ጋር ምንም ዓይነት ነገር አትብሉ፤ ሞራ ገላጭም አትሁኑ፥ አስማትም አታድርጉ። የራስ ጠጉራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቁረጡት። ስለ ሞተውም ብላችሁ ሥጋችሁን አትተልትሉ፥ ገላችሁንም ፈጽሞ አትንቀሱት፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ምድሪቱ እንዳታመነዝር በበርኩስነትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን እንድታመነዝር አድርገሃት አታርክሳት። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ ለመቅደሴም ክብርን ስጡ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “ወደ ሙታን መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ አትፈልጉአቸው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “በአዛውንት ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብጽ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገሩ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፥ እርሱንም እንደራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱት፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። “በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም አታታልሉ። ትክክለኛም ሚዛን፥ ትክክለኛም መመዘኛ፥ ትክክለኛም የኢፍ መስፈሪያ፥ ትክክለኛም የኢን መስፈሪያ ይኑሩአችሁ፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉአቸውም፤ እኔ ጌታ ነኝ።”