ዘሌዋውያን 18:24-30
ዘሌዋውያን 18:24-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ በእነዚህ ሁሉ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኀጢአቷን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፤ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። ሥርዐቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የሀገሩ ልጆች፥ በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩት የሀገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱንም አርክሰዋታልና፤ ምድሪቱም ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች ባረከሳችኋት ጊዜ እናንተንም እንዳትተፋችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዐቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።”
ዘሌዋውያን 18:24-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ከእነዚህ በአንዱ እንኳ ራሳችሁን አታርክሱ፤ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ በእነዚህ ሁሉ ረክሰዋልና። ምድሪቱም ሳትቀር ረከሰች፤ እኔም ስለ ኀጢአቷ ቀጣኋት፤ ስለዚህ የሚኖሩባትን ሰዎች ተፋቻቸው። እናንተ ግን ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እናንተ የአገር ተወላጆችና በመካከላችሁ የሚኖሩ መጻተኞች ከእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች ማንኛውንም አትፈጽሙ። ከእናንተ በፊት በምድሪቱ የኖሩ ሰዎች እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ስለ ፈጸሙ፣ ምድሪቱ ረክሳለች። እናንተም ምድሪቱን ብታረክሷት፣ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም ትተፋችኋለች። “ ‘ከእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች ማንኛውንም የሚፈጽም ሰው ሁሉ ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ። ትእዛዜን ጠብቁ፤ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ የኖሩ ሰዎች ካደረጓቸው አስጸያፊ ድርጊቶች አንዱንም አትፈጽሙ፤ በእነዚህም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
ዘሌዋውያን 18:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤ ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ። ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
ዘሌዋውያን 18:24-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ወደ ምድራቸው ያስገባህ ዘንድ እግዚአብሔር ከፊትህ የሚያስወግዳቸው ሕዝቦች ራሳቸውን ያረከሱባቸው ስለ ሆኑ፥ ከእነዚህ ድርጊቶች በአንዱ እንኳ ራስህን አታርክስ። ምድሪቱ ረከሰች፤ በበደልዋ ምክንያት ቀጣኋት፤ እርስዋም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ተፋቻቸው። ትእዛዞቼንና ኅጎቼን ጠብቁ፤ ከእነዚህ ርኲሰቶች እናንተም ሆናችሁ በመካከላችሁ የሚኖሩ ባዕዳን አንዳቸውንም አታድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩት የምድሪቱ ኗሪዎች እነዚህን ርኲሰቶች ሁሉ ስለ ፈጸሙ ምድሪቱን አርክሰዋታል። ምድሪቱን ብታረክስዋት ከእናንተ በፊት የነበሩትን ሕዝቦች እንደ ተፋች እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች። እነዚህን ርኲሰቶች የሚፈጽም ያ ሰው ከሕዝቡ ይለይ። “እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዝ ሁሉ ፈጽሙ፤ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ይፈጽሙት የነበረውን የረከሰ ልማድ አትከተሉ፤ ከእነዚህ አሳፋሪ ተግባሮች አንዱንም በመፈጸም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”
ዘሌዋውያን 18:24-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ስለ በደልዋ እቀጣታለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ትተፋቸዋለች። ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩም ተወላጅ በእናንተም መካከል የሚኖር እንግዳ ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ማናቸውንም ነገር አታድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩ የምድሪቱ ሰዎች ይህን ርኩሰት ሁሉ አድርገዋልና፥ ስለዚህ ምድሪቱ ረክሳለች፤ ያለዚያ ግን ምድሪቱን ካረከሳችሁ እርሷ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ አንቅራ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች። በእርግጥ ማንም ሰው ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ነገሮች ማናቸውንም ነገር ቢያደርግ፥ ያደረጋችው ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። ስለዚህ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ላይ የተደረገውን ጸያፍ ወግ ሁሉ ፈጽሞ እንዳታደርጉ፥ በእርሱም ራሳችሁን ፈጽሞ እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”