ዘሌዋውያን 1:1-14

ዘሌዋውያን 1:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እን​ዲህ ሲል ተና​ገ​ረው፦ “ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች እን​ዲህ ብለህ ንገ​ራ​ቸው፦ ከእ​ና​ንተ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መባ የሚ​ያ​ቀ​ርብ ሰው ቢኖር መባ​ች​ሁን ከእ​ን​ስሳ ወገን ከላ​ሞች ወይም ከበ​ጎች ታቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ። “መባ​ውም የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ከላ​ሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌ​ለ​በ​ትን ተባ​ቱን ያቀ​ር​ባል፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ተቀ​ባ​ይ​ነት እን​ዲ​ኖ​ረው በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ ፊት ያቀ​ር​በ​ዋል። ተቀ​ባ​ይ​ነት ይኖ​ረው ዘንድ ስለ እር​ሱም ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለት ዘንድ እጁን በሚ​ቃ​ጠ​ለው መሥ​ዋ​ዕት ራስ ላይ ይጭ​ናል። በሬ​ው​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያር​ደ​ዋል፤ የአ​ሮ​ንም ልጆች ካህ​ናቱ ደሙን ያቀ​ር​ባሉ፤ ደሙ​ንም በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ በዙ​ሪ​ያው ይረ​ጩ​ታል። የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ው​ንም መሥ​ዋ​ዕት ይገ​ፍ​ፈ​ዋል፤ በየ​ብ​ል​ቱም ይቈ​ር​ጠ​ዋል። የካ​ህ​ኑም የአ​ሮን ልጆች በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ እሳት ያነ​ድ​ዳሉ፤ በእ​ሳ​ቱም ላይ ዕን​ጨት ይረ​በ​ር​ባሉ፤ የአ​ሮ​ንም ልጆች ካህ​ናቱ የተ​ቈ​ረ​ጡ​ትን ብል​ቶች፥ ራሱ​ንም፥ ስቡ​ንም በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ በእ​ሳቱ ላይ ባለው በዕ​ን​ጨቱ ላይ ይረ​በ​ር​ቡ​ታል። የሆድ ዕቃ​ው​ንና እግ​ሮ​ቹን ግን በውኃ ያጥ​ባሉ፤ ካህ​ኑም ሁሉን የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ በጎ መዓዛ እን​ዲ​ሆን በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ ያቀ​ር​በ​ዋል። “ነገር ግን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ቀ​ር​በው መባ ከበ​ጎች ወይም ከፍ​የ​ሎች ቢሆን፥ ለሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ነውር የሌ​ለ​በ​ትን ተባ​ቱን፥ የፊት እግ​ሮ​ቹ​ንና ራሱን ጨምሮ ያቀ​ር​በ​ዋል። በመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም አጠ​ገብ በመ​ስዕ በኩል በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያር​ዱ​ታል፤ የአ​ሮ​ንም ልጆች ካህ​ናቱ ደሙን በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ በዙ​ሪ​ያው ይረ​ጩ​ታል። በየ​ብ​ል​ቱም ራሱን፥ ስቡ​ንም ይቈ​ር​ጡ​ታል፤ ካህ​ና​ቱም በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ በእ​ሳቱ ላይ ባለው በዕ​ን​ጨቱ ላይ ይረ​በ​ር​ቡ​ታል፤ የሆድ ዕቃ​ው​ንና እግ​ሮ​ቹን ግን በውኃ ያጥ​ቡ​ታል። ካህ​ኑም ሁሉን በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ ለቍ​ር​ባን ያቀ​ር​በ​ዋል፤ የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ በጎ መዓዛ ያለው ቍር​ባን ነው። “ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ያ​ቀ​ር​በው ቍር​ባን የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕት ከዎ​ፎች ቢሆን፥ ቍር​ባ​ኑን ከዋ​ኖስ ወይም ከር​ግብ ያቀ​ር​ባል።

ዘሌዋውያን 1:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ ወገን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ። “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ ነቀፋ የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው። የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት። እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው። የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት። ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤ አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ። የሚቀርበውን መሥዋዕት ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ሁሉ ይርጩት። አቅራቢው ብልቶቹን ያውጣ፤ ካህኑም ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምሮ በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድረው፤ አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑ መባውን ሁሉ አምጥቶ በመሠዊያው ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። “ ‘ለእግዚአብሔር በሚቃጠል መሥዋዕትነት የሚቀርበው መባ ከወፎች ወገን ከሆነ፣ ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ያቅርብ።

ዘሌዋውያን 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔርም ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ። መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል። በሬውንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል። የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የተቈረጡትን ብልቶች ራሱንም ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ቍርባኑም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል። በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። በየብልቱም ራሱንም ስቡንም ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው። ለእግዚአብሔርም የሚቀርበው ቍርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቍርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል።

ዘሌዋውያን 1:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ እንዲህ ብሎም አዘዘው፥ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር መባ በሚያቀርቡበት ጊዜ ሊጠብቁት የሚገባ ሥርዓት ይህ ነው፦ እያንዳንዱ ሰው ከቀንድ ከብትም ሆነ፥ ከበግ ወይም ከፍየል ወገን ማንኛውንም ዐይነት መባ በሚያቀርብበት ጊዜ፥ ይኸውም ከቀንድ ከብቱ መካከል አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ቢፈልግ ምንም ነውር የሌለበትን ኰርማ መርጦ ያምጣ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት የሰመረ መሥዋዕት ይሆንለት ዘንድ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ በር በኩል ያቅርበው። ሰውየው ለሚቃጠል መሥዋዕት ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ እጆቹን ይጫን፤ እርሱም ለኃጢአቱ ማስተስረያ የሰመረ መሥዋዕት ይሆንለታል። ያ ሰው ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ትውልዳቸው ከአሮን ወገን የሆነ ካህናት ደሙን ወደ እግዚአብሔር ያቅርቡት፤ በድንኳኑ በር መግቢያ በኩል በሚገኘው መሠዊያ ጐኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። ከዚያ በኋላ ያ ሰው የዚያን እንስሳ ቆዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም በየዐይነቱ ይቈራርጠው፤ የካህኑ የአሮን ዘሮች የሆኑትም ካህናት በመሠዊያው ላይ እንጨት ረብርበው እሳት ያቀጣጥሉ፤ የእንስሳውንም ሥጋ ብልቶች በየዐይነታቸው ለያይተው ራሱንና ስቡንም ጭምር በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ ያኑሩት። ያም ሰው የእንስሳውን ሆድ ዕቃና የኋላ እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መሥዋዕቱን በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ይህም የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ሰውየው ከበግ ወይም ከፍየል መንጋዎቹ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ቢፈልግ ምንም ነውር የሌለበት ተባዕት ይሁን። እርሱንም ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ የአሮን ዘር የሆኑ ካህናትም ደሙን ወስደው በመሠዊያው ጐኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። ያም ሰው እንስሳውን በየብልቱ ከቈራረጠው በኋላ ካህኑ ብልቶቹን ሁሉ፥ ራሱንና ስቡን ጭምር በመሠዊያ ላይ ተረብርቦ በሚቃጠለው እንጨት ላይ ያኑር፤ ሰውየውም የእንስሳውን የሆድ ዕቃና የኋላ እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም ያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ በመሠዊያው ላይ በሙሉ ያቃጥለው፤ ይህም ዐይነት በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። ሰውየው፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የፈለገው መባ ከወፎች ወገን ከሆነም የርግብ ጫጩት ወይም ዋኖስ መሆን ይችላል፤

ዘሌዋውያን 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታም ሙሴን ጠርቶ ከመገናኛው ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለጌታ መባ ሲያቀርብ፥ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከሆኑ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ ታቀርባላችሁ። “መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበሬ መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በጌታ ፊት እንዲሠምርለት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የእርሱንም ኃጢአት ለማስተስረይ የሠመረ ይሆንለታል። በሬውንም በጌታ ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል። የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ብልቶቹንና ራሱን ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ በእሳትም የሚቀርብ ቁርባን አድርጎ፥ በጌታ ዘንድ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ሁሉንም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። “የእርሱም ቁርባን ለሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል። በመሠዊያውም አጠገብ በስተ ሰሜን በኩል በጌታ ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። እንዲሁም ከራሱና ከስቡ ጋር አብሮ በየብልቱ ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን ያቀርበዋል፤ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም በጌታ ዘንድ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። “ለጌታም የሚቀርበው ቁርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቁርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል።