ኢያሱ 8:1-8

ኢያሱ 8:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ኢያ​ሱን፥ “አት​ፍራ፤ አት​ደ​ን​ግጥ፤ ተዋ​ጊ​ዎ​ችን ሁሉ ከአ​ንተ ጋር ውሰድ፤ ተነ​ሥ​ተ​ህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እነሆ፥ የጋ​ይ​ንም ንጉሥ፥ ሕዝ​ቡ​ንም ከተ​ማ​ው​ንም ምድ​ሩ​ንም በእ​ጅህ አሳ​ልፌ ሰጥ​ቼ​ሃ​ለሁ። በኢ​ያ​ሪ​ኮና በን​ጉ​ሥ​ዋም እን​ዳ​ደ​ረ​ግህ እን​ዲሁ በጋ​ይና በን​ጉ​ሥዋ ታደ​ር​ጋ​ለህ፤ የከ​ብ​ቱን ምርኮ ግን ለራ​ሳ​ችሁ ትዘ​ር​ፋ​ላ​ችሁ፤ ከከ​ተ​ማ​ዪ​ቱም በስ​ተ​ኋላ ይከ​ብ​ቧት ዘንድ ጦር ላክ” አለው። ኢያ​ሱም፥ ተዋ​ጊ​ዎ​ቹም ሕዝብ ሁሉ ተነ​ሥ​ተው ወደ ጋይ ወጡ፤ ኢያ​ሱም ጽኑ​ዓን፥ ተዋ​ጊ​ዎ​ችና ኀያ​ላን የሆ​ኑ​ትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ፤ በሌ​ሊ​ትም ላካ​ቸው። እን​ዲ​ህም ብሎ አዘ​ዛ​ቸው፥ “እነሆ፥ ሂዱና ከከ​ተ​ማ​ዪቱ በስ​ተ​ኋላ ተደ​በቁ፤ ከከ​ተ​ማ​ዪቱ አት​ራቁ፤ ሁላ​ች​ሁም ተዘ​ጋ​ጅ​ታ​ችሁ ተቀ​መጡ፤ እኔ፥ ከእ​ኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተ​ማ​ዪቱ እን​ቀ​ር​ባ​ለን፤ የጋ​ይም ሰዎች እኛን ሊገ​ናኙ እንደ ፊተ​ኛው በወጡ ጊዜ ከፊ​ታ​ቸው እን​ሸ​ሻ​ለን፤ ወጥ​ተ​ውም በተ​ከ​ተ​ሉን ጊዜ ከከ​ተማ እና​ር​ቃ​ቸ​ዋ​ለን፤ እነ​ር​ሱም እንደ በፊቱ ከፊ​ታ​ችን ሸሹ ይላሉ፤ እኛም ከፊ​ታ​ቸው እን​ሸ​ሻ​ለን። እን​ግ​ዲህ እና​ን​ተም ከተ​ደ​በ​ቃ​ች​ሁ​በት ስፍራ ተነሡ፤ አም​ላ​ካ​ች​ሁም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እር​ስ​ዋን በእ​ጃ​ችሁ አሳ​ልፎ ይሰ​ጣ​ልና ከተ​ማ​ዪ​ቱን ያዙ። በያ​ዛ​ች​ኋ​ትም ጊዜ ከተ​ማ​ዪ​ቱን በእ​ሳት አቃ​ጥ​ሉ​አት፤ እንደ አል​ኋ​ችሁ አድ​ርጉ፤ እነሆ፥ አዝ​ዣ​ች​ኋ​ለሁ።”

ኢያሱ 8:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ሰራዊቱን ሁሉ ይዘህ በመውጣት ጋይን ውጋ፤ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና። በኢያሪኮና በንጉሧ ላይ ያደረግኸውንም ሁሉ፣ በጋይና በንጉሧ ላይ ትደግመዋለህ፤ በዚህ ጊዜ ግን ምርኮውንና ከብቱን ለራሳችሁ ታደርጉታላችሁ፤ ታዲያ ከከተማዪቱ በስተጀርባ የደፈጣ ጦር አዘጋጅ።” ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ፤ ኢያሱም ምርጥ ከሆኑት ተዋጊዎቹ ሠላሳ ሺሕ ጦር አዘጋጅቶ በሌሊት ላካቸው፤ እንዲህ የሚል ትእዛዝም ሰጣቸው፤ “እነሆ፤ ከከተማዪቱ በስተጀርባ ታደፍጣላችሁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ነቅታችሁ ተጠባበቁ፤ እኔና ዐብረውኝ ያሉት ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንጠጋለን፤ ሰዎቹ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሊወጉን ወደኛ ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እንሸሻለን፤ እነርሱም፣ ‘ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት አሁንም ከእኛ በመሸሽ ላይ ናቸው’ በማለት ከከተማዪቱ እስክናርቃቸው ድረስ ይከታተሉናል፤ በዚህ ሁኔታ እኛም እንሸሻለን፤ እናንተም ከተደበቃችሁበት ትወጡና ከተማዪቱን ትይዛላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከተማዪቱን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና። ከተማዪቱን ስትይዙም በእሳት አቃጥሏት፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም አድርጉ፤ እነሆ አዝዣችኋለሁ።”

ኢያሱ 8:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ሰልፈኞችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፥ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፥ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፥ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ አለው። ኢያሱም ሰልፈኞቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፥ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፥ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ተዘጋጁ፥ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፥ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፥ አስቀድመን እንደ ሸሸን የምንሸሽ ይመስላቸዋልና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፥ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጉ፥ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።

ኢያሱ 8:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “የጦር ወታደሮችህን ይዘህ ወደ ዐይ ከተማ ለመዝመት ውጣ፤ ከቶ አትፍራ፤ ደፋር ሁን፤ እኔ በዐይ ንጉሥ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አድርጌሃለሁ፤ ሕዝቡ፥ ከተማይቱና ምድሪቱ የአንተ ይሆናሉ፤ ከዚህ በፊት በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ የደረሰውን ጥፋት በዐይና በንጉሥዋም ላይ ደግሞ ትፈጽምባቸዋለህ፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከእርስዋ የሚገኘውን የንብረትና የከብት ምርኮ ለራሳችሁ ታደርጋላችሁ፤ ከኋላ በኩል በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ።” ስለዚህም፥ ኢያሱ ከወታደሮቹ ጋር በዐይ ላይ ዘመተ፤ ከሠራዊቱም የተሻለ ችሎታ ያላቸውን ሠላሳ ሺህ ወታደሮች መርጦ በሌሊት ሲልካቸው እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው፦ “ከከተማይቱ በስተኋላ አድፍጣችሁ ቈዩ፤ ይሁን እንጂ ከከተማይቱ ብዙ ሳትርቁ አደጋ ለመጣል በሚያስችላችሁ ሁኔታ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት የጦር ሰልፈኞች ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ የዐይ ወታደሮች በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል በሚመጡብን ጊዜ ልክ ከዚህ በፊት ባደረግነው ዐይነት ወደ ኋላ እንሸሻለን፤ ከእነርሱ እየሸሸን ሳለን እንደ ቀድሞው ከእኛ እየሸሹ ነው ይላሉ፤ ከከተማው እስክናርቃቸው ድረስ እኛን ይከተላሉ፤ በዚህን ጊዜ እናንተ ከተደበቃችሁበት ስፍራ ወጥታችሁ ከተማይቱን ያዙ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከተማይቱን ለእናንተ አሳልፎ ይሰጣችኋል። ከተማይቱን ከያዛችሁ በኋላ፥ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእሳት አቃጥሉአት። እነሆ፥ አዝዤአችኋለሁ።”

ኢያሱ 8:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፥ አትደንግጥ፤ ተዋጊዎቹን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ።” ኢያሱም ተዋጊዎቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፤ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ነቅታችሁ ጠብቁ፤ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ እነርሱም፦ ‘እንደ ቀድሞው ከእኛ ዘንድ እየሸሹ ናቸው’ ይላሉና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ ጌታም አምላካችሁ እርሷን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ ጌታ ቃል አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።”