ኢያሱ 8:1-26
ኢያሱ 8:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ተዋጊዎችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እነሆ፥ የጋይንም ንጉሥ፥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ የከብቱን ምርኮ ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማዪቱም በስተኋላ ይከብቧት ዘንድ ጦር ላክ” አለው። ኢያሱም፥ ተዋጊዎቹም ሕዝብ ሁሉ ተነሥተው ወደ ጋይ ወጡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን፥ ተዋጊዎችና ኀያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ፤ በሌሊትም ላካቸው። እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “እነሆ፥ ሂዱና ከከተማዪቱ በስተኋላ ተደበቁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ፤ እኔ፥ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንቀርባለን፤ የጋይም ሰዎች እኛን ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ ወጥተውም በተከተሉን ጊዜ ከከተማ እናርቃቸዋለን፤ እነርሱም እንደ በፊቱ ከፊታችን ሸሹ ይላሉ፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እንግዲህ እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማዪቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማዪቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ አልኋችሁ አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።” ኢያሱም ላካቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፤ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በባሕር በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ ሕዝቡንም አያቸው፤ እርሱም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሕዝብ ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፤ ወደ ከተማዪቱም ፊት ደረሱ፤ በጋይም በምሥራቅ በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። ኢያሱም አምስት ሺህ ሰዎችን ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በጋይ ባሕር በኩል ይከብቡ ዘንድ አስቀመጣቸው። ሕዝቡም ሁሉ ሠራዊቶቻቸውን በከተማው መስዕ በኩል አኖሩ፤ ዳርቻውም እስከ ከተማው ባሕር ድረስ ነው፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ። የጋይም ንጉሥ በሰማ ጊዜ ፈጥኖ ሄደ። የከተማዪቱም ሰዎች ወጡ፤ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ባለው አንድ ስፍራ እስራኤልን በጦርነት ተቀበሉአቸው፤ እርሱ ግን ከከተማዪቱ በስተኋላ እንደ ተደበቁ አያውቅም ነበር። በደረሱባቸውም ጊዜ ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ከፊታቸው አፈገፈጉ፤ በምድረ በዳው መንገድም ሸሹ። የሀገሪቱም ሰዎች ሁሉ ተጠሩ፤ የእስራኤልንም ልጆች ተከትለው አሳደዱአቸው፤ ከከተማዪቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ከፍተው ተዉ፤ እስራኤልንም አሳደዱት። እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ፤ ከተማዪቱንም የከበቡአት ፈጥነው ከስፍራቸው ይነሣሉ” አለው፤ ኢያሱም በከተማዋ ላይ በእጁ ያለውን ጦር ዘረጋ። የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፤ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ወጡ፤ ወደ ከተማዋም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም በእሳት አቃጠሉአት። የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው በተመለከቱ ጊዜ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወዲህና ወዲያ መሸሽ አልቻሉም፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ። ኢያሱ፥ እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማዪቱን እንደ ያዙ፥ የከተማዪቱም ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ ባዩ ጊዜ ወደኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉአቸው። እነዚያም ከከተማ ወጥተው ተቀበሉአቸው፤ በእስራኤል ልጆች ሠራዊት መካከልም አገቡአቸው፤ እኒያ ከወዲያ፥ እኒህም ከወዲህ ሆነው አንድ እንኳን ሳይቀርና ሳያመልጥ ገደሉአቸው። የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። የእስራኤልም ልጆች ተከትለዋቸው በነበረበት በተራራው ቍልቍለትና በምድረ በዳ የጋይን ሰዎች መግደልን ከጨረሱ፥ ሁሉንም በጦር ወግተው ከአጠፉአቸው በኋላ ኢያሱ ወዲያውኑ ወደ ጋይ ተመልሶ፥ በሰይፍ አጠፋት። በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም፥ ሴትም፥ የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ። ኢያሱም የጋይን ሰዎች እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋበትን እጁን አላጠፈም።
ኢያሱ 8:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ሰራዊቱን ሁሉ ይዘህ በመውጣት ጋይን ውጋ፤ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና። በኢያሪኮና በንጉሧ ላይ ያደረግኸውንም ሁሉ፣ በጋይና በንጉሧ ላይ ትደግመዋለህ፤ በዚህ ጊዜ ግን ምርኮውንና ከብቱን ለራሳችሁ ታደርጉታላችሁ፤ ታዲያ ከከተማዪቱ በስተጀርባ የደፈጣ ጦር አዘጋጅ።” ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ፤ ኢያሱም ምርጥ ከሆኑት ተዋጊዎቹ ሠላሳ ሺሕ ጦር አዘጋጅቶ በሌሊት ላካቸው፤ እንዲህ የሚል ትእዛዝም ሰጣቸው፤ “እነሆ፤ ከከተማዪቱ በስተጀርባ ታደፍጣላችሁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ነቅታችሁ ተጠባበቁ፤ እኔና ዐብረውኝ ያሉት ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንጠጋለን፤ ሰዎቹ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሊወጉን ወደኛ ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እንሸሻለን፤ እነርሱም፣ ‘ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት አሁንም ከእኛ በመሸሽ ላይ ናቸው’ በማለት ከከተማዪቱ እስክናርቃቸው ድረስ ይከታተሉናል፤ በዚህ ሁኔታ እኛም እንሸሻለን፤ እናንተም ከተደበቃችሁበት ትወጡና ከተማዪቱን ትይዛላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከተማዪቱን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና። ከተማዪቱን ስትይዙም በእሳት አቃጥሏት፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም አድርጉ፤ እነሆ አዝዣችኋለሁ።” ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነርሱም ሄደው ከጋይ በስተምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል ባለው ቦታ አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን እዚያው ከሕዝቡ ጋራ ዐደረ። በማግስቱም ጧት ኢያሱ ማልዶ በመነሣት ወንዶቹን ሰበሰበ፤ እርሱና የእስራኤል አለቆችም ከፊት ሆነው እየመሯቸው ወደ ጋይ ወጡ። ከርሱ ጋራ የነበሩትም ተዋጊዎች በሙሉ ወጥተው ወደ ከተማዪቱ በመጠጋት ከፊት ለፊቷ ደረሱ፤ ከዚያም ከጋይ በስተሰሜን መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈሩ። ኢያሱ ቀደም ብሎ ዐምስት ሺሕ ሰው ያህል በመውሰድ ከከተማዪቱ በስተምዕራብ፣ በቤቴልና በጋይ መካከል እንዲያደፍጡ አድርጎ ነበር። ከከተማዪቱ በስተሰሜን የነበሩትንም፣ ከከተማዪቱ በስተምዕራብ የሸመቁትንም ወታደሮች ሁሉ ስፍራ ስፍራቸውን እንዲይዙ አደረጋቸው፤ በዚያችም ሌሊት ኢያሱ ወደ ሸለቆው ሄደ። የጋይ ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማዪቱ ወንዶች ሁሉ ማልደው በመገሥገሥ፣ እስራኤልን ለመውጋት ከዓረባ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ስፍራ መጡ፤ ንጉሡ ግን ከከተማዪቱ በስተጀርባ ያደፈጠ ኀይል የሚጠባበቀው መሆኑን አያውቅም ነበር። ኢያሱና እስራኤል በሙሉ ድል የተመቱ መስለው በመታየት፣ ወደ ምድረ በዳው ሸሹ። የጋይ ሰዎች በሙሉ እንዲያሳድዷቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፤ በዚህ ሁኔታም የጋይ ሰዎች ከከተማዪቱ እንዲርቁ ተደረገ። እስራኤልን ለማሳደድ ከጋይና ከቤቴል ያልወጣ ወንድ አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ከፍተው ትተው እስራኤልን ማሳደድ ያዙ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “ከተማዪቱን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፣ የያዝኸውን ጦር ወደ ጋይ አነጣጥር” አለው፤ ኢያሱም ጦሩን ወደ ጋይ አነጣጠረ። ይህን እንዳደረገም ያደፈጡት ሰዎች ከተደበቁበት ስፍራ በፍጥነት ወጥተው ወደ ፊት ሮጡ፤ ገብተው ከተማዪቱን ያዟት፤ ወዲያውኑም በእሳት አቃጠሏት። የጋይ ሰዎች ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሸሹ የነበሩት እስራኤላውያን ፊታቸውን ስላዞሩባቸውም፣ በየትኛውም በኩል ማምለጫ መንገድ አልነበራቸውም። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ያደፈጠው ጦር ከተማዪቱን መያዙንና ጢሱ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያዩ፣ ወደ ኋላ ተመልሰው በጋይ ሰዎች ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤ ያደፈጡትም ሰዎች እንደዚሁ ከከተማዪቱ ወጥተው መጡባቸው። ስለዚህ እስራኤላውያን በዚያም በዚህም ስለ ከበቧቸው የጋይን ሰዎች ከመካከል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም ሰዎቹን ፈጇቸው፤ አንድ እንኳ የተረፈ ወይም ያመለጠ አልነበረም፤ ነገር ግን የጋይን ንጉሥ ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምድረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ። በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺሕ ነበር። ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር።
ኢያሱ 8:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ሰልፈኞችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፥ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፥ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፥ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ አለው። ኢያሱም ሰልፈኞቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፥ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፥ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ተዘጋጁ፥ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፥ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፥ አስቀድመን እንደ ሸሸን የምንሸሽ ይመስላቸዋልና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፥ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጉ፥ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ። ኢያሱም ሰደዳቸው፥ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፥ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ ሕዝቡንም አሰለፈ፥ እርሱም የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፥ ወደ ከተማይቱም ፊት ደረሱ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፥ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው። በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የተደበቁትን ሕዝብ አኖሩ፥ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ። የጋይም ንጉሥ ባየ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ቸኩለው በማለዳ ተነሡ፥ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በሰልፍ ለመገናኘት ወጡ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ። በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሊያሳድዱአቸው ተጠሩ፥ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፥ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት። እግዚአብሔር ኢያሱን፦ ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ አለው፥ ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ። የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፥ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት። የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፥ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም፥ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ እንደ ተነሣ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ። ሌሎቹም በላያቸው ከከተማይቱ ወጡ፥ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፥ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው። የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። እንዲህም ሆነ፥ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከወደቁ በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት። በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ አሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ። ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስከሚያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም።
ኢያሱ 8:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “የጦር ወታደሮችህን ይዘህ ወደ ዐይ ከተማ ለመዝመት ውጣ፤ ከቶ አትፍራ፤ ደፋር ሁን፤ እኔ በዐይ ንጉሥ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አድርጌሃለሁ፤ ሕዝቡ፥ ከተማይቱና ምድሪቱ የአንተ ይሆናሉ፤ ከዚህ በፊት በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ የደረሰውን ጥፋት በዐይና በንጉሥዋም ላይ ደግሞ ትፈጽምባቸዋለህ፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከእርስዋ የሚገኘውን የንብረትና የከብት ምርኮ ለራሳችሁ ታደርጋላችሁ፤ ከኋላ በኩል በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ።” ስለዚህም፥ ኢያሱ ከወታደሮቹ ጋር በዐይ ላይ ዘመተ፤ ከሠራዊቱም የተሻለ ችሎታ ያላቸውን ሠላሳ ሺህ ወታደሮች መርጦ በሌሊት ሲልካቸው እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው፦ “ከከተማይቱ በስተኋላ አድፍጣችሁ ቈዩ፤ ይሁን እንጂ ከከተማይቱ ብዙ ሳትርቁ አደጋ ለመጣል በሚያስችላችሁ ሁኔታ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት የጦር ሰልፈኞች ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ የዐይ ወታደሮች በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል በሚመጡብን ጊዜ ልክ ከዚህ በፊት ባደረግነው ዐይነት ወደ ኋላ እንሸሻለን፤ ከእነርሱ እየሸሸን ሳለን እንደ ቀድሞው ከእኛ እየሸሹ ነው ይላሉ፤ ከከተማው እስክናርቃቸው ድረስ እኛን ይከተላሉ፤ በዚህን ጊዜ እናንተ ከተደበቃችሁበት ስፍራ ወጥታችሁ ከተማይቱን ያዙ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከተማይቱን ለእናንተ አሳልፎ ይሰጣችኋል። ከተማይቱን ከያዛችሁ በኋላ፥ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእሳት አቃጥሉአት። እነሆ፥ አዝዤአችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ ወታደሮቹን ላከ፤ ከዐይ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል ድብቅ ጦር ሆነው ቈዩ፤ ኢያሱም በሠራዊቱ መካከል ዐደረ። በማግስቱም ጠዋት ኢያሱ ቀደም ብሎ በመነሣት ሕዝቡን ጠራ፤ እርሱና የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ዘማቹን ጦር ወደ ዐይ መምራት ጀመሩ፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሠራዊት ወደ ፊት ቀድሞ በመጓዝ ወደ ከተማይቱ ቀረበ፤ በስተሰሜንም በኩል በእርሱና በዐይ መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈረ። ኢያሱ አምስት ሺህ ሰዎችን ያኽል መርጦ ከከተማይቱ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል እንዲሸምቁ አድርጎ ነበር። እነርሱም ዋናውን ሠራዊት ከከተማ በስተሰሜን በኩል፥ የኋላውን ደጀን በስተምዕራብ በኩል አሰለፉ፤ ኢያሱ ግን ሌሊቱን በሸለቆው አሳለፈ። የዐይ ንጉሥ ይህን በአየ ጊዜ እርሱና የከተማው ሕዝብ እስራኤልን በጦርነት ለመግጠም ወደ ዓራባ ፊት ለፊት ወጡ። ከከተማው በስተጀርባ በኩል የደጀን ጦር መኖሩን አላወቁም ነበር። ኢያሱና ሠራዊቱ ሁሉ የተሸነፉ በማስመሰል ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ምድረ በዳ ሸሹ። የከተማይቱም ሰዎች እርስ በርስ በመጠራራት በሙሉ ወጥተው እነርሱን ማሳደድ ቀጠሉ፤ ኢያሱንም በሚያሳድዱበት ጊዜ ከከተማይቱ እየራቁ ሄዱ። በዐይ ወይም በቤትኤል የሚገኝ ሰው ሁሉ ወጥቶ እስራኤላውያንን ሲያሳድድ ከተማይቱ ባዶዋን ክፍት ሆና ቀረች። ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን፦ “ጦርህን በዐይ ከተማ ላይ አንሣ፤ እኔ እርስዋን ለአንተ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር ወደ ከተማይቱ ዘረጋ። እጁንም በዘረጋ ጊዜ ሸምቀው የነበሩት ወታደሮች ከቦታቸው ተነሥተው ወደፊት ሄዱ፤ ወደ ከተማዋም በፍጥነት ገብተው በቊጥጥራቸው ሥር አደረጓትና ወዲያውኑ አቃጠሉአት። የዐይ ከተማ ሰዎችም ወደ ኋላ መለስ ብለው ባዩ ጊዜ የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ የሸሹት እስራኤላውያን በአሳዳጆቻቸው ላይ ስለ ተመለሱባቸው፥ በየትም በኩል ለማምለጥ አልቻሉም። ኢያሱና ከእርሱ ጋር ተሰልፎ የነበረው ሠራዊት ቀደም ብለው ያዘጋጁት ሽምቅ ጦር ከተማይቱን በቊጥጥር ሥር ማድረጉንና በእሳት ማቃጠሉን በተመለከቱ ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው የዐይን ሰዎች መቱ። ወደ ከተማይቱም ገብተው የነበሩት እስራኤላውያን ወደ እነርሱ ወርደው የጦርነቱ ተካፋዮች ሆኑ፤ ስለዚህም የዐይን ሰዎች የተወሰኑ እስራኤላውያን በአንድ በኩል፥ ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል ከበዋቸው ስለ ነበረ ወደየትም ለማምለጥ አልቻሉም። ከእነርሱም አንድ እንኳ እንዳያመልጥ ወይም በሕይወት እንዳይኖር ሁሉንም ፈጁአቸው። የዐይ ንጉሥ ግን ተማርኮ ወደ ኢያሱ ቀረበ። እስራኤላውያን በሜዳና በምድረ በዳ ቀደም ሲል የዐይ ወታደሮች እነርሱን አሳደዋቸው በነበረው ስፍራ ሁሉንም ገድለው ከጨረሱ በኋላ ወደ ዐይ ከተማ ገብተው በዚያ የተረፉትንም በሰይፍ ፈጁአቸው። በዚያን ቀን የሞቱት የዐይ ወንዶችና ሴቶች ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ። ኢያሱም በዐይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም።
ኢያሱ 8:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፥ አትደንግጥ፤ ተዋጊዎቹን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ።” ኢያሱም ተዋጊዎቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፤ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ነቅታችሁ ጠብቁ፤ እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ እነርሱም፦ ‘እንደ ቀድሞው ከእኛ ዘንድ እየሸሹ ናቸው’ ይላሉና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ ጌታም አምላካችሁ እርሷን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ ጌታ ቃል አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።” ኢያሱም ሰደዳቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። ኢያሱም ማልዶ በጠዋት ተነሣ፥ ሕዝቡንም ሰበሰበ፤ እርሱም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ ወጥተው በመጓዝ ወደ ከተማይቱ ቀረቡ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው። በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የኋላ ደጀን የሆነውን ሕዝብ አኖሩ፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት በሸለቆው ውስጥ አደረ። የጋይም ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ቸኩለው በማለዳ ተነሡ፤ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በጦርነት ለመግጠም ወጡ፤ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ። በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እነርሱን እዲያሳድዱአቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት። ጌታ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በእርሷ ላይ ዘርጋ፤” ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ። የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት። የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሸው ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ስለ ተመለሱ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም። ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ ወደ ላይ እንደ ጤሰ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ። ሌሎቹም በእነርሱ ላይ ከከተማይቱ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፤ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው። የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። እንዲህም ሆነ፤ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከፈጁአቸው በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት። በዚያም ቀን የሞቱት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ነበሩ። ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስከሚያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋበትን እጁን አላጠፈም።