ኢያሱ 7:21-26
ኢያሱ 7:21-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ ካባ፥ ሁለት መቶ ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፤ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፤ ብሩም ከሁሉ በታች ነው” አለው። ኢያሱም መልእክተኞችን ላከ፤ ወደ ሰፈርም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም እርሱ በድንኳኑ ውስጥ ተደብቆ፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ አውጥተው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ አመጡት፤ በእግዚአብሔርምፊት አኖሩት። ኢያሱም የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ልብሱንም፥ ልሳነ ወርቁንም ወደ አኮር ሸለቆ ወሰዳቸው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ንብረቱንም ሁሉ ወደ ዔሜቃኮር ወሰደ። ኢያሱም፥ “ለምን አጠፋኸን? ዛሬ እንዳጠፋኸን እግዚአብሔር ዛሬ ያጥፋህ” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉት፤ በድንጋይም ወገሩአቸው። በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ እግዚአብሔርም ከቍጣው መቅሠፍት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዔሜቃኮር ተብሎ ተጠራ።
ኢያሱ 7:21-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ ዐምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሯል።” በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ። ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩ። ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋራ ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ። ኢያሱም፣ “እንዲህ ያለውን መከራ ለምን አመጣብህን? እነሆ፤ ዛሬ በአንተም ላይ እግዚአብሔር መከራ ያመጣብሃል” አለው። ከዚያም እስራኤል በሙሉ በድንጋይ ወገሩት፤ የቀሩትንም እንደዚሁ ከወገሩ በኋላ በእሳት አቃጠሏቸው። በአካንም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታየውን ታላቅ የድንጋይ ቍልል ከመሩበት፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቍጣው ተመለሰ። ስለዚህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያ ስፍራ የአኮር ሸለቆ ተባለ።
ኢያሱ 7:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፥ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው። ኢያሱም መልክተኞች ሰደደ ወደ ድንኳኑም ሮጡ፥ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፥ በእግዚአብሔርም ፊት አኖሩት። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። ኢያሱም፦ ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፥ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፥ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፥ እግዚአብሔርም ከቁጣው ትኩሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።
ኢያሱ 7:21-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ካገኘነው ዕቃ መካከል ውብ የሆነ የባቢሎናውያን ካባ፥ ሁለት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብርና ግማሽ ኪሎ ያህል የሚመዝን ምዝምዝ ወርቅ አየሁ፤ እነርሱንም ለማግኘት ብርቱ ፍላጎት ስላደረብኝ ወስጃቸዋለሁ፤ እነርሱንም ብሩ ከታች ሆኖ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተቀብረዋል።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ እየሮጡ ሄዱ፥ እዚያም ብር ከስር ሆኖ የተቀበሩት እርም የሆኑ ዕቃዎች ነበሩ፤ እነርሱንም ከድንኳኑ በማውጣት፥ ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤላውያን አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩአቸው። ኢያሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ዓካንን ይዞ ብሩን፥ ካባውን፥ የወርቅ ምዝምዙን ከዓካን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር ከብቶቹን፥ አህዮቹንና በጎቹን ጭምር፥ ድንኳኑንና የእርሱ ንብረት የሆነውን ሁሉ ሰብስቦ፥ ወደ አኮር ሸለቆ አመጣቸው፤ ኢያሱም “ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ ያመጣህብን ስለምንድን ነው? እነሆ! በአንተም ላይ ዛሬ እግዚአብሔር መከራን ያመጣብሃል!” አለው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ዓካንን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ ቤተሰቡንም በድንጋይ ወግረው ንብረቱን ሁሉ አቃጠሉ፤ በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እግዚአብሔርም ከቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህም ያ ቦታ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ይጠራል።
ኢያሱ 7:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በምርኮ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም ኀምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው።” ኢያሱም መልክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በጌታም ፊት አኖሩት። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። ኢያሱም፦ “ለምን መከራን አመጣህብን? ጌታ ዛሬ መከራን ያመጣብሃል” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ ጌታም ከጽኑ ቁጣው ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።