ኢያሱ 7:1-26

ኢያሱ 7:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ግን እርም በሆ​ነው ነገር ታላቅ በደል በደሉ፤ ከይ​ሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እር​ሱም የከ​ርሚ ልጅ፥ የዘ​ን​በሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ እርም ከሆ​ነው ነገር ወሰደ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ላይ ተቈጣ። ኢያ​ሱም ከቤ​ቴል በም​ሥ​ራቅ በኩል በቤ​ት​አ​ዊን አጠ​ገብ ወዳ​ለ​ችው ወደ ጋይ ሰዎ​ችን ከኢ​ያ​ሪኮ ልኮ፥ “ውጡ፤ ጋይ​ንም ሰልሉ” ብሎ ተና​ገ​ራ​ቸው፤ ሰዎ​ቹም ወጡ፤ ጋይ​ንም ሰለሉ። ወደ ኢያ​ሱም ተመ​ል​ሰው፥ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥ​ተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይ​ውጣ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ​ዚያ አት​ው​ሰድ፤ ጥቂ​ቶች ናቸ​ውና” አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎ​ችም ወደ​ዚያ ወጡ፤ የጋ​ይም ሰዎች አባ​ረ​ሩ​አ​ቸው፤ ከፊ​ታ​ቸ​ውም ሸሹ። የጋይ ሰዎ​ችም ከእ​ነ​ርሱ ሠላሳ ስድ​ስት ሰዎ​ችን ገደሉ፤ ከበሩ ጀም​ረው እስከ አጠ​ፉ​አ​ቸው ድረስ አባ​ረ​ሩ​አ​ቸው፤ በቍ​ል​ቍ​ለ​ቱም ገደ​ሉ​አ​ቸው፤ የሕ​ዝ​ቡም ልብ ደነ​ገጠ፤ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያ​ሱም ልብ​ሱን ቀደደ፤ እር​ሱና የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግ​ን​ባ​ራ​ቸው ተደፉ፤ በራ​ሳ​ቸ​ውም ላይ ትቢያ ነሰ​ነሱ። ኢያ​ሱም አለ፥ “ወዮ! ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሆይ! በአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያን እጅ አሳ​ል​ፈህ ትሰ​ጠን፥ ታጠ​ፋ​ንም ዘንድ አገ​ል​ጋ​ይህ ይህን ሕዝብ ዮር​ዳ​ኖ​ስን ለምን አሻ​ገረ? በዮ​ር​ዳ​ኖስ ማዶ ተቀ​ም​ጠን በኖ​ርን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስ​ራ​ኤል ጀር​ባ​ውን ወደ ጠላ​ቶቹ ከመ​ለሰ እን​ግ​ዲህ ምን እላ​ለሁ? ከነ​ዓ​ና​ው​ያ​ንም፥ በም​ድ​ሪ​ቱም የሚ​ኖሩ ሁሉ ሰም​ተው ይከ​ብ​ቡ​ናል፤ ከም​ድ​ርም ያጠ​ፉ​ናል፤ ለታ​ላቁ ስም​ህም የም​ታ​ደ​ር​ገው ምን​ድር ነው?” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ኢያ​ሱን አለው፥ “ለምን በግ​ን​ባ​ርህ ተደ​ፍ​ተ​ሃል? ተነሥ! ሕዝቡ በድ​ለ​ዋል፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር የገ​ባ​ሁ​ትን ቃል ኪዳ​ኔን አፍ​ር​ሰ​ዋል፤ እርም ከሆ​ነ​ውም ነገር ሰር​ቀው ወሰዱ፤ በዕ​ቃ​ቸ​ውም ውስጥ ሸሸ​ጉት። ስለ​ዚ​ህም የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸው ፊት መቆም አይ​ች​ሉም፤ የተ​ረ​ገሙ ስለ​ሆኑ በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸው ፊት ይሸ​ሻሉ፤ እርም የሆ​ነ​ው​ንም ነገር ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ካላ​ጠ​ፋ​ችሁ ከዚህ በኋላ ከእ​ና​ንተ ጋር አል​ሆ​ንም። ተነ​ሣና ሕዝ​ቡን ቀድስ እን​ዲ​ህም በላ​ቸው፦ ‘እስ​ራ​ኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመ​ካ​ከ​ልህ አለ፤ እር​ምም የሆ​ነ​ውን ነገር ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ እስ​ክ​ታ​ጠፉ ድረስ በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችሁ ፊት መቆም አት​ች​ሉም’ ብሎ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተና​ግ​ሮ​አ​ልና እስከ ነገ ራሳ​ች​ሁን አንጹ። ነገም በየ​ነ​ገ​ዳ​ችሁ ትቀ​ር​ባ​ላ​ችሁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ለ​የው ነገድ በየ​ወ​ገ​ኖቹ ይቀ​ር​ባል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ለ​የው ወገን በየ​ቤተ ሰቦቹ ይቀ​ር​ባል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ለ​የው ቤተ ሰብ በየ​ሰዉ ይቀ​ር​ባል። ምል​ክት የታ​የ​በት ሰው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ኪዳን አፍ​ር​ሶ​አ​ልና፥ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ዘንድ በደል አድ​ር​ጎ​አ​ልና፥ እር​ሱና ያለው ሁሉ በእ​ሳት ይቃ​ጠ​ላሉ።” ኢያ​ሱም ማልዶ ተነሣ፤ እስ​ራ​ኤ​ል​ንም በየ​ነ​ገ​ዶ​ቻ​ቸው ሰበ​ሰ​ባ​ቸው፤ በይ​ሁ​ዳም ነገድ ላይ ምል​ክት ታየ፤ የይ​ሁ​ዳም ወገ​ኖች ተለዩ፤ በዛ​ራም ወገን ምል​ክት ታየ፤ የዛ​ራም ወገን በየ​ቤተ ሰቡ ተለየ፤ በዘ​ን​በ​ሪም ወገን ምል​ክት ታየ፤ የዘ​ን​በ​ሪም ቤተ ሰብ እያ​ን​ዳ​ንዱ ተለየ፤ ከይ​ሁ​ዳም ወገን በሆነ በከ​ርሚ ልጅ በዘ​ን​በሪ ልጅ በዛራ ልጅ በአ​ካን ላይ ምል​ክት ታየ። ኢያ​ሱም አካ​ንን፥ “ልጄ ሆይ! ለእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብር ስጥ፤ ለእ​ር​ሱም ተና​ዘዝ፤ ያደ​ረ​ግ​ኸ​ው​ንም ንገ​ረኝ፤ አት​ሸ​ሽ​ገ​ኝም” አለው። አካ​ንም መልሶ ኢያ​ሱን፥ “በእ​ው​ነት በእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በድ​ያ​ለሁ፤ እን​ዲ​ህና እን​ዲ​ህም አድ​ር​ጌ​አ​ለሁ። በዘ​ረፋ መካ​ከል አንድ ያማረ ካባ፥ ሁለት መቶ ሰቅል ብር፥ ሚዛ​ኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመ​ኘ​ኋ​ቸው፤ ወሰ​ድ​ኋ​ቸ​ውም፤ እነ​ሆም በድ​ን​ኳኔ ውስጥ በመ​ሬት ተሸ​ሽ​ገ​ዋል፤ ብሩም ከሁሉ በታች ነው” አለው። ኢያ​ሱም መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ ወደ ሰፈ​ርም ወደ ድን​ኳኑ ሮጡ፤ እነ​ሆም እርሱ በድ​ን​ኳኑ ውስጥ ተደ​ብቆ፥ ብሩም በበ​ታቹ ነበረ። ከድ​ን​ኳ​ኑም ውስጥ አው​ጥ​ተው ወደ ኢያ​ሱና ወደ እስ​ራ​ኤል ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ሁሉ አመ​ጡት፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ም​ፊት አኖ​ሩት። ኢያ​ሱም የዛ​ራን ልጅ አካ​ንን፥ ብሩ​ንም፥ ልብ​ሱ​ንም፥ ልሳነ ወር​ቁ​ንም ወደ አኮር ሸለቆ ወሰ​ዳ​ቸው፤ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ልጆ​ቹ​ንም፥ በሬ​ዎ​ቹ​ንም፥ አህ​ያ​ዎ​ቹ​ንም፥ በጎ​ቹ​ንም፥ ድን​ኳ​ኑ​ንም፥ ንብ​ረ​ቱ​ንም ሁሉ ወደ ዔሜ​ቃ​ኮር ወሰደ። ኢያ​ሱም፥ “ለምን አጠ​ፋ​ኸን? ዛሬ እን​ዳ​ጠ​ፋ​ኸን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዛሬ ያጥ​ፋህ” አለው፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ በድ​ን​ጋይ ወገ​ሩት፤ በእ​ሳ​ትም አቃ​ጠ​ሉት፤ በድ​ን​ጋ​ይም ወገ​ሩ​አ​ቸው። በላ​ዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድ​ን​ጋይ ክምር ከመሩ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከቍ​ጣው መቅ​ሠ​ፍት ተመ​ለሰ። ስለ​ዚ​ህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዔሜ​ቃ​ኮር ተብሎ ተጠራ።

ኢያሱ 7:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱ ከቤቴል በስተምሥራቅ ካለችው ከቤትአዌን አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጋይ ከኢያሪኮ ሰዎችን ልኮ፣ “ወደዚያ ውጡ፤ አገሪቱንም ሰልሉ” አላቸው፤ ሰዎቹም ወጥተው ጋይን ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፣ “ጋይን ለመውጋት ሕዝቡ ሁሉ መሄድ አያስፈልገውም፤ በዚያ ያለው ሕዝብ ጥቂት ስለ ሆነ፣ ከተማዪቱን ለመውጋት ሁለት ወይም ሦስት ሺሕ ሰው ስለሚበቃ ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ በመሄድ አይድከም” አሉት። ስለዚህ ሦስት ሺሕ ያህል ሰው ወጣ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሸ፤ የጋይም ሰዎች እስራኤላውያንንም ከከተማዪቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሽባሪም ድረስ በማባረር ቍልቍለቱ ላይ መቷቸው፤ ከእነርሱም ሠላሳ ስድስት ያህል ሰው ገደሉባቸው። ከዚህ የተነሣም የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውሃም ፈሰሰ። በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፋ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንደዚሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፤ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዮርዳኖስን አሻግረህ ይህን ሕዝብ ወደዚህ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንዲያጠፉን ነውን? ምነው ሳንሻገር እዚያው ማዶ በቀረን ኖሮ! ጌታ ሆይ፤ እስራኤል በጠላቱ ፊት ሲሸሽ እኔ ምን ልበል? ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከብቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ? እስራኤል በድሏል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ ዕርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋራ ደባልቀዋል። እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። ዕርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ ዕርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ። “ ‘ማለዳ በየነገድ በየነገዳችሁ ሆናችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ይወጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተ ሰቡ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተ ሰብ ደግሞ በግለ ሰብ በግለ ሰብ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል። ዕርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሷል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟልና።’ ” በማግስቱም ጧት ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ እስራኤልንም በየነገድ በየነገዳቸው ሆነው እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ተለየ። የይሁዳንም ጐሣዎች ወደ ፊት አቀረበ፤ ከእነዚህም የዛራን ጐሣ ለየ፤ እነዚህን ደግሞ በየቤተ ሰባቸው እንዲወጡ አደረገ፤ ከእነዚህም ዘንበሪ ተለየ። ኢያሱ የዘንበሪን ቤተ ሰብ አባላት አንድ በአንድ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የሆነውም የዛራ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የከርሚ ልጅ አካን ለብቻው ተለየ። ኢያሱም አካንን፣ “ልጄ ሆይ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ፤ ለርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውን ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው። አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤ ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ ዐምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሯል።” በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ። ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩ። ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋራ ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ። ኢያሱም፣ “እንዲህ ያለውን መከራ ለምን አመጣብህን? እነሆ፤ ዛሬ በአንተም ላይ እግዚአብሔር መከራ ያመጣብሃል” አለው። ከዚያም እስራኤል በሙሉ በድንጋይ ወገሩት፤ የቀሩትንም እንደዚሁ ከወገሩ በኋላ በእሳት አቃጠሏቸው። በአካንም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታየውን ታላቅ የድንጋይ ቍልል ከመሩበት፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቍጣው ተመለሰ። ስለዚህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያ ስፍራ የአኮር ሸለቆ ተባለ።

ኢያሱ 7:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፥ የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፦ ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፥ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፦ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፥ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፥ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፥ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም መቱአቸው፥ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ፦ ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፥ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፥ እስራኤል በድሎአል፥ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፥ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፥ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፥ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፥ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ። ነገም በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፥ እግዚአብሔርም የሚለየው ቤተ ሰብ በየሰዉ ይቀርባል። እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል አድርጎአልና እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ። ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፥ የይሁዳም ነገድ ተለየ፥ የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፥ የዛራንም ወገን ሰዎች አቀረበ፥ ዘንበሪም ተለየ፥ የቤቱንም ሰዎች አቀረበ፥ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የከርሚ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የዛራ ልጅ አካን ተለየ። ኢያሱም አካንን፦ ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፥ ያደረግኸውንም ንገረኝ፥ አትሸሽገኝ አለው። አካንም መልሶ ኢያሱን፦ በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፥ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው። ኢያሱም መልክተኞች ሰደደ ወደ ድንኳኑም ሮጡ፥ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፥ በእግዚአብሔርም ፊት አኖሩት። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። ኢያሱም፦ ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፥ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፥ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፥ እግዚአብሔርም ከቁጣው ትኩሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።

ኢያሱ 7:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስራኤላውያን ግን የተከለከሉ ነገሮችን በተመለከተ ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ዓካን፥ የከርሚ ልጅ፥ የዘብዲ የልጅ ልጅ፥ የዛራ ልጅ ከተከለከሉት ነገሮች በመውሰድ በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አስነሣ። ኢያሱ በኢያሪኮ ሳለ በቤትአዌን አጠገብ ከቤትኤል በስተምሥራቅ የምትገኘውን “ዐይ” ተብላ የምትጠራውን ከተማና የምድሪቱን አቀማመጥ አጥንተው ይመለሱ ዘንድ ጥቂት ሰዎችን ላከ። ይህንንም በትእዛዙ መሠረት ከፈጸሙ በኋላ፥ ለኢያሱ ከዚህ የሚከተለውን ማስረጃ አቀረቡለት፦ “እነርሱ ጥቂቶች ስለ ሆኑ በዐይ ላይ አደጋ ለመጣል ያለውን ሰው ሁሉ በአጠቃላይ ማዝመት አያስፈልግም፤ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ላክ፤ በዚያ ለመዋጋት መላውን ሠራዊት አትላክ።” ስለዚህም ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ዘምተው አደጋ ጣሉባት፤ ነገር ግን እነርሱ ከዐይ ወታደሮች ፊት ሸሹ፤ የዐይ ሰዎችም ወደ ሠላሳ ስድስት ያኽል ሰዎችን ገደሉባቸው፤ ከከተማይቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሼባሪዎ ቊልቊለት ድረስ እየገደሉ አባረሩአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀልጦ እንደ ውሃ ፈሰሰ። ኢያሱና የእስራኤል መሪዎች በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ ሐዘናቸውን ለመግለጥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ወዮ! እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህን ሕዝብ ለምን ዮርዳኖስን አሻገርከው? አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነርሱ አሳልፈህ ለመስጠት ነውን? ከዮርዳኖስ ማዶ ብንቀመጥ እንዴት በተሻለን ነበር! አምላክ ሆይ፥ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት ከሸሸ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንና ሌሎችም በዚህች ምድር የሚኖሩት ሁሉ ይህን ነገር ይሰማሉ፤ ስለዚህም ዙሪያችንን ከበው ሁላችንንም ይፈጁናል፤ ታዲያ ስለ ክብርህ የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ስለምን በግንባርህ ወደቅኽ? እስራኤላውያን በድለዋል፤ እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ ከተከለከሉት ነገሮች ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ከራሳቸው ንብረት ጋር በማቀላቀል አታላዮች ሆነዋል። እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም ያልቻሉበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እነርሱ ራሳቸው እንዲጠፉ ስለ ተፈረደባቸው ከጠላቶች ፊት ወደ ኋላ ይሸሻሉ። እንዲደመሰስ የታዘዘውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ሂድ! ሕዝቡን አንጻ! ‘በመካከላችሁ የተከለከለ ነገር ስላለ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለነገ ራሳችሁን አንጹ!’ ይላል በላቸው። እስራኤል ሆይ! ይህን የተከለከለ ነገር ከመካከልህ ካላስወገድህ በጠላቶችህ ፊት ልትቆም አትችልም። ስለዚህ ነገ ጧት በየነገዳችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣው ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተሰቡ ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተሰብ በየግለሰቡ ይቅረብ፤ እርም የሆኑ (የተከለከሉ) ነገሮች የተገኙበትም ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስላፈረሰና በእስራኤል ላይ በደል ስለ ፈጸመ እርሱና የእርሱ የሆነ ሁሉ በእሳት ይቃጠል።” በማግስቱም ማለዳ ኢያሱ እስራኤላውያንን በየነገዳቸው አምጥቶ አቀረባቸው፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ለብቻው ተለየ፤ ኢያሱም የይሁዳን ነገድ በየጐሣው አቀረበ፤ ከዚያም በኋላ የዛራሕ ጐሳ ለብቻው ተለየ፤ የዛራሕንም ጐሣ በየቤተሰቡ አቀረበው፤ የዛብዲም ቤተሰብ ለብቻው ተለየ፤ የዛብዲንም ቤተሰብ በየግለሰቡ ለይቶ አቀረበ፤ በመጨረሻም የዛብዲ የልጅ ልጅ የሆነው የካርሚ ልጅ ዓካን ለብቻው ተለየ፤ ኢያሱም ዓካንን “ልጄ ሆይ፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አክብር፤ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረግኸውንም ከእኔ ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው። ዓካንም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “እውነት ነው፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የበደልኩ እኔ ነኝ፤ እነሆ፥ ያደረግኹትም ከዚህ የሚከተለው ነው፤ ካገኘነው ዕቃ መካከል ውብ የሆነ የባቢሎናውያን ካባ፥ ሁለት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብርና ግማሽ ኪሎ ያህል የሚመዝን ምዝምዝ ወርቅ አየሁ፤ እነርሱንም ለማግኘት ብርቱ ፍላጎት ስላደረብኝ ወስጃቸዋለሁ፤ እነርሱንም ብሩ ከታች ሆኖ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተቀብረዋል።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ እየሮጡ ሄዱ፥ እዚያም ብር ከስር ሆኖ የተቀበሩት እርም የሆኑ ዕቃዎች ነበሩ፤ እነርሱንም ከድንኳኑ በማውጣት፥ ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤላውያን አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩአቸው። ኢያሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ዓካንን ይዞ ብሩን፥ ካባውን፥ የወርቅ ምዝምዙን ከዓካን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር ከብቶቹን፥ አህዮቹንና በጎቹን ጭምር፥ ድንኳኑንና የእርሱ ንብረት የሆነውን ሁሉ ሰብስቦ፥ ወደ አኮር ሸለቆ አመጣቸው፤ ኢያሱም “ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ ያመጣህብን ስለምንድን ነው? እነሆ! በአንተም ላይ ዛሬ እግዚአብሔር መከራን ያመጣብሃል!” አለው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ዓካንን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ ቤተሰቡንም በድንጋይ ወግረው ንብረቱን ሁሉ አቃጠሉ፤ በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እግዚአብሔርም ከቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህም ያ ቦታ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ይጠራል።

ኢያሱ 7:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ፤” ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው እንዲህ አሉት፦ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም።” ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም ላይ ሳሉ መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በጌታ ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ልትሰጠን ልታጠፋንም ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስራኤል ከጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድነው?” ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ለምን በግምባርህ ተደፍተኽ ትሰግዳለህ? ቁም፤ እስራኤል ኃጢአት ሠርቶአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስከ ነገ ተቀደሱ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፦ “እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም።” ነገ ጧት በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ ጌታም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ቤተሰብ በየሰዉ ይቀርባል። እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የጌታን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል ፈጽሟልና እርሱና የእርሱ የሆነው ነገር ሁሉ በእሳት ይቃጠል።’ ” ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፤ የይሁዳም ነገድ ተለየ፤ የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፤ የዛራንም ወገን ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ዘንበሪም ተለየ፤ የቤቱንም ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የዛራ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የከርሚ ልጅ አካን ተለየ። ኢያሱም አካንን እንዲህ አለው፦ “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ።” አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእውነት በእስራኤል አምላክ በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ፤ በምርኮ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም ኀምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው።” ኢያሱም መልክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በጌታም ፊት አኖሩት። ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። ኢያሱም፦ “ለምን መከራን አመጣህብን? ጌታ ዛሬ መከራን ያመጣብሃል” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ ጌታም ከጽኑ ቁጣው ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።