ኢያሱ 6:15-19
ኢያሱ 6:15-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፤ እንደዚህም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያም ቀን ብቻ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። እንዲህም ሆነ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ በዞሩና ካህናቱ ቀንደ መለከቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች አለ፥ “እግዚአብሔር ከተማዪቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማዪቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱ ረዓብ፥ ከእርስዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ብለን ከተውነው እንዳትወስዱ ተጠንቀቁ፤ ከእርሱም ተመኝታችሁ አትውሰዱ፤ ብትወስዱ ግን የእስራኤልን ሰፈር የተረገመች ታደርጓታላችሁ፤ እኛንም ታጠፉናላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።”
ኢያሱ 6:15-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያ ቀን ብቻ ነው። በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ መለከቱን ሲነፉ፣ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሰጥቷችኋልና ጩኹ ከተማዪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለ ሆነ ፈጽማችሁ አጥፉ እኛ የላክናቸውን ሰላዮች ስለ ሸሸገች ጋለሞታዪቱ ረዓብ ብቻና ከርሷ ጋራ በቤቷ ውስጥ ያሉት ሁሉ ይትረፉ። እናንተ ግን ዕርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ አለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤ ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለ ሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።”
ኢያሱ 6:15-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፥ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ፦ እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፥ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፥ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፥ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።
ኢያሱ 6:15-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰባተኛው ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሥተው በዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፤ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩበት ቀን ይህ ብቻ ነበር። በሰባተኛው ዙር ካህናቱ እምቢልታ ሊነፉ በሚዘጋጁበት ጊዜ ኢያሱ ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ከተማይቱን ስለ ሰጣችሁ ጩኹ!” ብሎ አዘዘ። “በከተማይቱና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተረገመ ሆኖ መደምሰስ አለበት፤ ሴትኛ ዐዳሪዋ ግን የላክናቸውን ሰላዮች ደብቃ ስላዳነች መትረፍ የሚገባቸው እርስዋና ከእርስዋ ጋር በቤትዋ ያሉት ብቻ ናቸው። እናንተ ግን በእስራኤል ሰፈር ችግርንና ጥፋትን እንዳታስከትሉ መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች ማናቸውንም ጓጒታችሁ ከመውሰድ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ብርና ወርቅ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን፤ እርሱም በእግዚአብሔር የዕቃ ግምጃ ቤት መቀመጥ አለበት።”
ኢያሱ 6:15-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።”