ኢያሱ 5:4-6
ኢያሱ 5:4-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ከግብፅ የወጡ ወንዶች ተዋጊዎች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ፤ የወጡትም ወንዶች ሁሉ ተገርዘው ነበር። ነገር ግን ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ፥ በምድረ በዳ የተወለዱ ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበርና፥ ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ገረዛቸው። እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን የማለላቸውን ምድር እንደማያሳያቸው የማለባቸውን፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ተዋጊዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በመድበራ ምድረ በዳ ይዞሩ ነበር።
ኢያሱ 5:4-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ኢያሱ እስራኤላውያንን የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ዕድሜያቸው መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከግብጽ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞቱ። ከዚያ የወጡት ሰዎች ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ከግብጽ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በጕዞ ላይ ሳሉ የተወለዱት ግን በሙሉ አልተገረዙም ነበር። ግብጽን ለቅቀው በወጡ ጊዜ መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፣ እነርሱ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይንከራተቱ ነበር። እግዚአብሔር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን ያችን ማርና ወተት የምታፈስስ ምድር እንደማያዩአት ምሏልና።
ኢያሱ 5:4-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነው፥ ከግብፅ የወጡት ሕዝብ ወንዶች ሰልፈኞች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ። የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፥ ነገር ግን ከግብፅ በወጡበት መንገድ በምድረ በዳ የተወለዱት ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበር። እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር።
ኢያሱ 5:4-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢያሱ እነርሱን የገረዘበት ምክንያት ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች ሁሉ በበረሓው ጒዞ ጊዜ ሞተው ስለ ነበረ ነው። በመጀመሪያ ከግብጽ ምድር የወጡት ወንዶች ሁሉ ተገርዘው የነበሩ ቢሆኑም እንኳ በበረሓው ጒዞ ጊዜ የተወለዱት ወንዶች አልተገረዙም ነበር። ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማታቸው ሁሉም እስኪያልቁ ድረስ እስራኤላውያን በበረሓ ለአርባ ዓመት ተጓዙ። ለልጅ ልጆቻቸው ሊሰጥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ቃል ገብቶ የነበረውን በማርና በወተት የበለጸገውን ምድር በምድረ በዳ ያለቁት ልጆቻቸው እንደማያዩት አረጋግጦ ነበር።
ኢያሱ 5:4-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነበር፤ ከግብጽ ከወጣው ሕዝብ መካከል ወንዶች ተዋጊዎች ሁሉ ከግብጽ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞተው ስለ ነበረ ነው። የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ነገር ግን ከግብጽ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በመንገድ እየተጓዙ ሳሉ የተወለዱት ልጆች ሁሉ አልተገረዙም ነበር። ጌታም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ እንዲሰጠን ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ የጌታንም ቃል ያልሰሙ፥ ሕዝብ ሁሉ፥ ከግብጽ የወጡ ተዋጊዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር።