ኢያሱ 3:1-7
ኢያሱ 3:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ እርሱና እስራኤልም ሁሉ ከሰጢም ተጕዘው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። ከሦስት ቀንም በኋላ ጸሓፊዎች በሰፈሩ መካከል ገቡ። ለሕዝቡም እንዲህ ብለው ዐወጁ፥ “የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ሌዋውያንና ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት። በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፤ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።” ኢያሱም ሕዝቡን፥ “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ራሳችሁን አንጹ” አለ። ኢያሱም ካህናቱን፥ “የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት ሂዱ” ብሎ ተናገራቸው፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ።
ኢያሱ 3:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢያሱም ማልዶ ተነሣ። ከእስራኤላውያንም ሁሉ ጋራ ከሰጢም ወደ ዮርዳኖስ መጥተው ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት በዚያ ሰፈሩ። ከሦስት ቀን በኋላም የጦሩ አለቆች በሰፈር ውስጥ ዐለፉ፤ ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤ ከአሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺሕ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።” ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን፣ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በመካከላችሁ አስደናቂ ነገር ስለሚያደርግ ራሳችሁን ቀድሱ” አላቸው። ኢያሱም ካህናቱን፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ ሕዝቡን ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ። እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋራ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋራ መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ።
ኢያሱ 3:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፥ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ። ሕዝቡን፦ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፥ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ። ኢያሱም ሕዝቡን፦ ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ። ኢያሱም ካህናቱን፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ ብሎ ተናገራቸው፥ የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ሁሉ ዓይን ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ።
ኢያሱ 3:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱ ኢያሱና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፤ የሺጢምን ሰፈር ለቀው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ፤ ከመሻገራቸውም በፊት በዚያ ሰፈሩ፤ ከሦስት ቀን በኋላ የሕዝቡ መሪዎች ወደ ሰፈር ገብተው፥ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጡ፦ “የሌዊ ዘር የሆኑት ካህናት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ሲነሡ በምታዩበት ጊዜ፥ ሰፈሩን ለቃችሁ እነርሱን ተከተሉ። ከዚህ በፊት ይህን ቦታ ስለማታውቁት የምትሄዱበትን መንገድ እነርሱ ያሳዩአችኋል፤ ነገር ግን ወደ ቃል ኪዳኑ ታቦት አትቅረቡ፤ በእናንተና በቃል ኪዳኑ ታቦት መካከል የሚኖረው ርቀት አንድ ኪሎ ሜትር ያኽል ይሁን።” ኢያሱም ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ነገ በመካከላችሁ ተአምራትን ስለሚያደርግ ራሳችሁን አንጹ” አላቸው። የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ከሕዝቡ በመቅደም እፊት እፊት እንዲሄዱ ለካህናቱ ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ። እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርኩ ከአንተም ጋር የምሆን መሆኔን ያውቁ ዘንድ እኔ ዛሬ በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት አንተን ከፍ፥ ከፍ ማድረግ እጀምራለሁ።
ኢያሱ 3:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በማግስቱም ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ። ሕዝቡንም እንዲህ ብለው አዘዙ፦ “የአምላካችሁን የጌታን ቃል ኪዳን ታቦቱንና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ እርሱን በመከተል፥ በዚህ መንገድ በፊት አላለፋችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ ታውቃላችሁ። በእናንተና በታቦቱ መካከል ግን ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።” ኢያሱም ሕዝቡን፦ “ነገ ጌታ በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ” አለ። ኢያሱም ካህናቱን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ፤” እነርሱም የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን እንዲያውቁ በዚህ ቀን አንተን በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ከፍ ከፍ ማድረግ እጀምራለሁ።