ኢያሱ 24:11-15
ኢያሱ 24:11-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞሬዎናዊው፥ ፌርዜዎናዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጤዎናዊው፥ ጌርጌሴዎናዊው፥ ኤዌዎናዊው፥ ኢያቡሴዎናዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፤ በሰይፍህም፥ በቀስትህም ሳይሆን ዐሥራ ሁለቱን የአሞሬዎናውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደድኋቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርን ታመልኩ ዘንድ ባትወድዱ ግን፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት፥ ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።”
ኢያሱ 24:11-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
ኢያሱ 24:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፥ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፥ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፥ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።
ኢያሱ 24:11-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ እንዲሁም አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን እናንተን ለመውጋት ተነሡ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋችሁ። በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ እንዳደረግሁት አስቀድሜ ከፊታችሁ ያባረራቸውን ተርብ ሰደድኩባቸው፤ ይህ በእናንተ ሰይፍ ወይም በእናንተ ቀስት የሆነ አይደለም። እናንተ በማረስ ያልደከማችሁበትን የለማ ምድርና ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች መኖሪያ አድርጌ ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፥ አሁን ያልተከላችሁትን የወይን ተክልና ያልደከማችሁበትን የወይራ ዛፍ ፍሬ እየተመገባችሁ ትኖራላችሁ።’ ” ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
ኢያሱ 24:11-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን በፊታችሁም ተርብ ሰድጄ ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።”