ኢያሱ 24:1-33

ኢያሱ 24:1-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢያ​ሱም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴሎ ሰበ​ሰበ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ል​ንም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች፥ አለ​ቆ​ቻ​ቸ​ው​ንም፥ ጸሓ​ፊ​ዎ​ቻ​ቸ​ው​ንም፥ ፈራ​ጆ​ቻ​ቸ​ው​ንም ጠራ​ቸው። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት አቆ​ማ​ቸው። ኢያ​ሱም ለሕ​ዝቡ ሁሉ እን​ዲህ አለ፥ “የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ ‘አባ​ቶ​ቻ​ችሁ፥ የአ​ብ​ር​ሃ​ምና የና​ኮር አባት ታራ፥ አስ​ቀ​ድ​መው በወ​ንዝ ማዶ ተቀ​መጡ፤ ሌሎ​ች​ንም አማ​ል​ክት አመ​ለኩ። አባ​ታ​ች​ሁ​ንም አብ​ር​ሃ​ምን ከወ​ንዝ ማዶ ወስጄ በከ​ነ​ዓን ምድር ሁሉ መራ​ሁት፤ ዘሩ​ንም አበ​ዛሁ፤ ይስ​ሐ​ቅ​ንም ሰጠ​ሁት። ለይ​ስ​ሐ​ቅም ያዕ​ቆ​ብ​ንና ዔሳ​ውን ሰጠ​ሁት፤ ለዔ​ሳ​ውም የሴ​ይ​ርን ተራራ ርስት አድ​ርጌ ሰጠ​ሁት፤ የያ​ዕ​ቆ​ብም ልጆች ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚ​ያም ታላቅ ሕዝብ ሆኑ፤ በዙም፤ በረ​ቱም፤ ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም መከራ አጸ​ኑ​ባ​ቸው። ሙሴ​ንና አሮ​ን​ንም ላክሁ፤ በእ​ነ​ር​ሱም ላይ ስላ​ደ​ረ​ጉት ነገር ግብ​ፃ​ው​ያ​ንን ቀሠ​ፍ​ኋ​ቸው፤ ከዚ​ያም በኋላ አባ​ቶ​ቻ​ች​ሁን ከግ​ብፅ አወ​ጣ​ኋ​ቸው፤ ወደ ባሕ​ሩም ገባ​ችሁ፤ ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም አባ​ቶ​ቻ​ች​ሁን በሰ​ረ​ገ​ሎ​ችና በፈ​ረ​ሶች እስከ ኤር​ትራ ባሕር ድረስ ተከ​ተ​ሉ​አ​ቸው። ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በጮ​ሃ​ችሁ ጊዜ በእ​ና​ን​ተና በግ​ብ​ፃ​ው​ያን መካ​ከል ደመ​ና​ንና ጭጋ​ግን አደ​ረ​ግሁ፤ ባሕ​ሩ​ንም መለ​ስ​ሁ​ባ​ቸው፤ አሰ​ጠ​ማ​ቸ​ውም፤ ዐይ​ኖ​ቻ​ች​ሁም በግ​ብፅ ያደ​ረ​ግ​ሁ​ትን አዩ፤ በም​ድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀ​መ​ጣ​ችሁ። በዮ​ር​ዳ​ኖስ ማዶ ወደ ተቀ​መ​ጡት ወደ አሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያን ምድ​ርም ወሰ​ድ​ኋ​ችሁ፤ ከእ​ና​ን​ተም ጋር ተዋጉ፤ ሙሴም ተዋ​ጋ​ቸው፤ አሳ​ል​ፌም በእ​ጃ​ችሁ ሰጠ​ኋ​ችሁ፤ ምድ​ራ​ቸ​ው​ንም ወረ​ሳ​ችሁ፤ ከፊ​ታ​ች​ሁም አጠ​ፋ​ኋ​ቸው። የሞ​ዓ​ብም ንጉሥ የሴ​ፎር ልጅ ባላቅ ተነ​ሥቶ ከእ​ስ​ራ​ኤል ጋር ተዋጋ፤ እን​ዲ​ረ​ግ​ማ​ች​ሁም የቢ​ዖ​ርን ልጅ በለ​ዓ​ምን ልኮ አስ​ጠ​ራው። እኔ ግን ላጠ​ፋ​ችሁ አል​ወ​ደ​ድ​ሁም፤ መባ​ረ​ክ​ንም ባረ​ክ​ኋ​ችሁ፤ ከእ​ጁም አዳ​ን​ኋ​ችሁ፤ ዮር​ዳ​ኖ​ስ​ንም ተሻ​ገ​ራ​ችሁ፤ ወደ ኢያ​ሪ​ኮም መጣ​ችሁ፤ የኢ​ያ​ሪ​ኮም ሰዎች፥ አሞ​ሬ​ዎ​ና​ዊው፥ ፌር​ዜ​ዎ​ና​ዊው፥ ከነ​ዓ​ና​ዊው፥ ኬጤ​ዎ​ና​ዊው፥ ጌር​ጌ​ሴ​ዎ​ና​ዊው፥ ኤዌ​ዎ​ና​ዊው፥ ኢያ​ቡ​ሴ​ዎ​ና​ዊው ተዋ​ጉ​አ​ችሁ፥ አሳ​ል​ፌም በእ​ጃ​ችሁ ሰጠ​ኋ​ቸው። በፊ​ታ​ች​ሁም ተርብ ሰደ​ድሁ፤ በሰ​ይ​ፍ​ህም፥ በቀ​ስ​ት​ህም ሳይ​ሆን ዐሥራ ሁለ​ቱን የአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን ነገ​ሥ​ታት ከፊ​ታ​ችሁ አሳ​ደ​ድ​ኋ​ቸው። ያል​ደ​ከ​ማ​ች​ሁ​በ​ት​ንም ምድር፥ ያል​ሠ​ራ​ች​ኋ​ቸ​ው​ንም ከተ​ሞች ሰጠ​ኋ​ችሁ፤ ተቀ​መ​ጣ​ች​ሁ​ባ​ቸ​ውም፤ ካል​ተ​ከ​ላ​ች​ኋ​ቸ​ውም ከወ​ይ​ንና ከወ​ይራ በላ​ችሁ።’ “አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፍሩት፤ በእ​ው​ነ​ትና በቅ​ን​ነ​ትም አም​ል​ኩት፤ አባ​ቶ​ቻ​ች​ሁም በወ​ንዝ ማዶ፥ በግ​ብ​ፅም ውስጥ ያመ​ለ​ኩ​አ​ቸ​ውን ሌሎች አማ​ል​ክት ከእ​ና​ንተ አርቁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አም​ልኩ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታመ​ልኩ ዘንድ ባት​ወ​ድዱ ግን፥ አባ​ቶ​ቻ​ችሁ በወ​ንዝ ማዶ ሳሉ ያመ​ለ​ኩ​አ​ቸ​ውን አማ​ል​ክት፥ ወይም በም​ድ​ራ​ቸው ያላ​ች​ሁ​ባ​ቸ​ውን የአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን አማ​ል​ክት ታመ​ልኩ እንደ ሆነ፥ የም​ታ​መ​ል​ኩ​ትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​መ​ል​ካ​ለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።” ሕዝ​ቡም መል​ሰው እን​ዲህ አሉ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ትተን ሌሎች አማ​ል​ክ​ትን ማም​ለክ ከእኛ ይራቅ፤ እኛ​ንና አባ​ቶ​ቻ​ች​ንን ከባ​ር​ነት ቤት ከግ​ብፅ ምድር ያወ​ጣን፥ በዐ​ይ​ና​ች​ንም ፊት እነ​ዚ​ያን ታላ​ላቅ ተአ​ም​ራት ያደ​ረገ፥ በሄ​ድ​ን​ባ​ትም መን​ገድ ሁሉ፥ ባለ​ፍ​ን​ባ​ቸ​ውም አሕ​ዛብ ሁሉ መካ​ከል የጠ​በ​ቀን፥ እርሱ አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነውና። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አሕ​ዛ​ብን ሁሉ፥ በም​ድ​ሪ​ቱም የተ​ቀ​መ​ጡ​ትን አሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን ከፊ​ታ​ችን አሳ​ደደ፤ ስለ​ዚህ እርሱ አም​ላ​ካ​ችን ነውና እኛ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​መ​ል​ካ​ለን።” ኢያ​ሱም ሕዝ​ቡን፥ “እርሱ ቅዱስ አም​ላክ ነውና፥ እር​ሱም ቀና​ተኛ አም​ላክ ነውና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ማም​ለክ አት​ች​ሉም፤ ብታ​ስ​ቀ​ኑት መተ​ላ​ለ​ፋ​ች​ሁ​ንና ኀጢ​አ​ታ​ች​ሁን ይቅር አይ​ልም። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ትታ​ችሁ ሌሎ​ችን አማ​ል​ክት ብታ​መ​ልኩ፥ መል​ካ​ምን ባደ​ረ​ገ​ላ​ችሁ ፋንታ ተመ​ልሶ ክፉ ነገር ያደ​ር​ግ​ባ​ች​ኋል፤ ያጠ​ፋ​ች​ሁ​ማል” አላ​ቸው። ሕዝ​ቡም ኢያ​ሱን፥ “እን​ዲህ አይ​ሁን፤ ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​መ​ል​ካ​ለን” አሉት። ኢያ​ሱም ሕዝ​ቡን፥ “እን​ድ​ታ​መ​ል​ኩት እና​ንተ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እንደ መረ​ጣ​ችሁ በራ​ሳ​ችሁ ላይ ምስ​ክ​ሮች ናችሁ” አላ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም፥ “ምስ​ክ​ሮች ነን” አሉ። እር​ሱም፥ “አሁን እን​ግ​ዲህ በእ​ና​ንተ ዘንድ ያሉ​ትን ሌሎች አማ​ል​ክት አርቁ፤ ልባ​ች​ሁ​ንም ወደ እስ​ራ​ኤል አም​ላክ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አቅኑ” አላ​ቸው። ሕዝ​ቡም ኢያ​ሱን፥ “አም​ላ​ካ​ች​ንን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እና​መ​ል​ካ​ለን፤ ቃሉ​ንም እን​ሰ​ማ​ለን” አሉት። በዚ​ያም ቀን ኢያሱ ከሕ​ዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደ​ረገ፤ በሴ​ሎም በእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ድን​ኳን ፊት ሕግ​ንና ፍር​ድን ሰጣ​ቸው። ኢያ​ሱም ይህን ቃል ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሕግ መጽ​ሐፍ ጻፈው፤ ኢያ​ሱም ታላ​ቁን ድን​ጋይ ወስዶ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በነ​በ​ረ​ችው በአ​ሆማ ዛፍ በታች አቆ​ማት። ኢያ​ሱም ለሕ​ዝቡ ሁሉ፥ “ይህች ድን​ጋይ በእ​ና​ንተ ላይ ምስ​ክር ናት፤ እር​ስዋ፥ ዛሬ እንደ ነገ​ራ​ችሁ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ባ​ለ​ውን ሁሉ ሰም​ታ​ለ​ችና በኋላ ዘመን አም​ላ​ኬን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ብት​ክ​ዱት ይህች ድን​ጋይ ምስ​ክር ትሆ​ን​ባ​ች​ኋ​ለች” አላ​ቸው። ኢያ​ሱም ሕዝ​ቡን አሰ​ና​በተ፤ ሁሉም ወደ​የ​ቦ​ታ​ቸው ገቡ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አገ​ል​ጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድ​ሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆ​ነው ሞተ። በተ​ራ​ራ​ማ​ውም በኤ​ፍ​ሬም ሀገር በገ​ዓስ ተራራ በሰ​ሜን ባለ​ችው በር​ስቱ ዳርቻ በተ​ም​ና​ሴራ ቀበ​ሩት። በዚ​ያም ከግ​ብፅ በወጡ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዳ​ዘ​ዘው የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች በገ​ል​ገላ የገ​ረ​ዘ​ባ​ቸ​ውን የድ​ን​ጋይ ባል​ጩ​ቶ​ችን እር​ሱን በቀ​በ​ሩ​በት መቃ​ብር ከእ​ርሱ ጋር ቀበሩ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። ኢያሱ ባለ​በት ዘመን ሁሉ፥ ከኢ​ያ​ሱም በኋላ በነ​በ​ሩት ለእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ያደ​ረ​ገ​ውን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ ሁሉ ባወ​ቁት በሽ​ማ​ግ​ሌ​ዎች ዘመን ሁሉ፥ እስ​ራ​ኤል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ለኩ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ከግ​ብፅ ያወ​ጡ​ትን የዮ​ሴ​ፍን አፅም ያዕ​ቆብ በሰ​ቂማ ከሚ​ኖሩ ከአ​ሞ​ራ​ው​ያን በመቶ በጎች በገ​ዛው ለዮ​ሴፍ ድርሻ አድ​ርጎ በሰ​ጠው እርሻ በአ​ንዱ ክፍል በሰ​ቂማ ቀበ​ሩት። የአ​ሮ​ንም ልጅ ሊቀ ካህ​ናቱ አል​ዓ​ዛር ሞተ፤ በተ​ራ​ራ​ማ​ውም በኤ​ፍ​ሬም ሀገር ለልጁ ለፊ​ን​ሐስ በተ​ሰ​ጠ​ችው በጊ​ብ​ዓት መሬት ቀበ​ሩት።

ኢያሱ 24:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይሥሐቅንም ሰጠሁት። ለይሥሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብጽ ወረዱ። “ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሠፍት ግብጻውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ። አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ተከታተሏቸው። እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብጻውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ። “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ። “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብጽ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ከዚያም ኢያሱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ መርጣችኋልና በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ምስክሮች ነን” ሲሉ መለሱ። ኢያሱም፣ “እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር መልሱ” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፣ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” አሉት። በዚያ ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ፤ የሚመሩበትንም ደንብና ሥርዐት እዚያው ሴኬም ሰጣቸው። ኢያሱም እነዚህን ቃሎች እግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ በባሉጥ ዛፍ ሥር፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ አጠገብ አቆመው። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣ እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቷል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል” አላቸው። ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደየርስቱ እንዲሄድ አሰናበተ። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው፣ ከገዓስ ተራራ በስተሰሜን ባለችው በራሱ ርስት በተምናሴራ ቀበሩት። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ። እስራኤላውያን ከግብጽ ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም፣ ያዕቆብ ከሰኬም አባት ከኤሞር በመቶ ሰቅል ብር በገዛው በሴኬም ምድር ተቀበረ፤ ይህችም የዮሴፍ ዘሮች ርስት ሆነች። እንዲሁም የአሮን ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በሚገኘው ለልጁ ለፊንሐስ በዕጣ በደረሰው በጊብዓ ምድር ተቀበረ።

ኢያሱ 24:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፥ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፥ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፥ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፥ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፥ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው። አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፥ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፥ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፥ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፥ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፥ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፥ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፥ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፥ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፥ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ እግዚአብሔርን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፥ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፥ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፥ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ አላቸው፥ እነርሱም፦ ምስክሮች ነን አሉ። እርሱም፦ አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፦ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፥ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ፦ እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፥ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል አላቸው። ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ። እንዲህም ሆነ፥ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ። የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በግ በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፥ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፥ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት።

ኢያሱ 24:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም በአንድነት ሰበሰበ፤ ሽማግሌዎችን፥ አለቆቻቸውን፥ ዳኞችንና የእስራኤልን የጦር አዛዦች ሁሉ ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ፤ ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ ‘ከብዙ ዘመናት በፊት የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ይኖሩ ነበር፤ ከነዚያም አባቶች አንዱ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ ነበር፤ ከዚህም በኋላ የቀድሞ አባታችሁን አብርሃምን ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚገኘው ምድር ጠርቼ፥ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት፤ ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁ፤ ለዔሳውም የኤዶምን ኮረብታማ አገር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ነገር ግን ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ወረዱ፤ ከዚያም በኋላ ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ግብጽንም በመቅሠፍት መታሁ፤ በመጨረሻም እናንተን አወጣኋችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ወደ ባሕር ደረሱ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ባሳደዱአቸው ጊዜ፥ እረዳቸው ዘንድ ወደ እኔ ጮኹ፤ እኔም በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረግሁ። ባሕሩም እንዲከነበልባቸው አድርጌ ግብጻውያንን አሰጠምሁ፤ በግብጻውያን ላይ ምን እንዳደረግሁ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ለብዙ ጊዜ በበረሓ ኖራችሁ። ከዚህም በኋላ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ተዋጉአችሁ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋቸው፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ። ከዚህም በኋላ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጲፖር ልጅ ባላቅ ሊወጋችሁ በእናንተ ላይ ተነሣሣ፤ እናንተንም ይረግምለት ዘንድ በለዓም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ቢዖር ልጅ መልእክት ላከ፤ እኔ ግን በለዓምን አልሰማሁትም፤ ስለዚህም በመርገም ፈንታ ባረካችሁ፤ በዚህም ዐይነት ከባላቅ እጅ አዳንኳችሁ፤ እናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ እንዲሁም አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን እናንተን ለመውጋት ተነሡ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋችሁ። በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ እንዳደረግሁት አስቀድሜ ከፊታችሁ ያባረራቸውን ተርብ ሰደድኩባቸው፤ ይህ በእናንተ ሰይፍ ወይም በእናንተ ቀስት የሆነ አይደለም። እናንተ በማረስ ያልደከማችሁበትን የለማ ምድርና ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች መኖሪያ አድርጌ ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፥ አሁን ያልተከላችሁትን የወይን ተክልና ያልደከማችሁበትን የወይራ ዛፍ ፍሬ እየተመገባችሁ ትኖራላችሁ።’ ” ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች ባዕዳን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ! አምላካችን እግዚአብሔር አባቶቻችንንና እኛን ከግብጽ ባርነት አውጥቶናል፤ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተናል፤ ሕዝቦችን ሁሉ አልፈን በመጣንበት ጊዜ በሰላም ጠብቆናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቦችን እንዲሁም በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ሁሉ ከፊታችን አባሮልናል፤ ስለዚህም እርሱ አምላካችን ስለ ሆነ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ቅዱስና ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ፥ እናንተ እርሱን ማገልገል አትችሉም፤ የምትሠሩትን ዐመፅና ኃጢአት ሁሉ ይቅር አይልም፤ እርሱን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ ደግ ያደረገላችሁ ቢሆንም እንኳ ተመልሶ እርሱ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል።” ሕዝቡም ለኢያሱ “ይህ ከቶ አይደረግም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ኢያሱም “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ ስለ መምረጣችሁ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” ሲል ነገራቸው። እነርሱም “አዎ፤ ምስክሮች ነን፤” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ በመካከላችሁ የሚገኙትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አድርጉ” አላቸው። ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ኢያሱን “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ትእዛዞችንም እንፈጽማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ በዚያም በሴኬም የሚመሩበትን ሕግና ሥርዓት ሰጣቸው፤ ኢያሱም እነዚህን ትእዛዞች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ከዚያም በኋላ አንድ ትልቅ ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ በሚገኘው የወርካ ዛፍ ሥር አቆመው፤ ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የነገረንን ቃል ሁሉ ስለ ሰማ ይህ ድንጋይ በእኛ ላይ ምስክር ነው፤ ስለዚህም አምላካችሁን ብትክዱ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆንባችኋል።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ እያንዳንዱም ወደየርስት ይዞታው ተመልሶ ሄደ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በአንድ መቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ። እስራኤላውያንም ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው በኮረብታማይቱ በኤፍሬም አገር የራሱ የኢያሱ ርስት በሆነችው በቲምናትሴራሕ ቀበሩት። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ከእርሱም ሞት በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ በዐይናቸው ያዩት ሽማግሌዎች እስከ ኖሩበት ዘመን ድረስ እርሱኑ በማምለክ ኖሩ። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም በሴኬም ተቀበረ፤ ይህም ምድር ያዕቆብ የሼኬም አባት ከሆነው ከሐሞር ልጆች በአንድ መቶ ጥሬ ብር የገዛው ነበር፤ ምድሩም የሚገኘው በዮሴፍ ዘሮች የርስት ድርሻ ክልል ውስጥ ነው። የአሮን ልጅ አልዓዛርም ሞተ፤ በጊብዓም ተቀበረ፤ እርስዋም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኝና ለልጁ ለፊንሐስ መኖሪያ የተሰጠች ትንሽ ከተማ ናት።

ኢያሱ 24:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምንቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በጌታ ፊት ቆሙ። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብጽ ወረዱ። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብጽን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን አወጣሁ። አባቶቻችሁንም ከግብጽ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። ወደ ጌታም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብጽ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልፈለግሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን በፊታችሁም ተርብ ሰድጄ ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ጌታን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማገልገል ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ ጌታ አምላካችን ነውና። ጌታ አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና ጌታን እናገለግላለን።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና ጌታን ማገልገል አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። ጌታን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን እናገለግላለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እንድታገለግሉት እናንተ ጌታን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ፤” እነርሱም፦ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ አዘንብሉ።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “ጌታ አምላካችንን እናገለግላለን፥ ድምፁንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም እነዚህን ቃላት በጌታ ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በጌታ መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የተናገረንን የጌታን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል።” ኢያሱም እያንዳንዱን ሰው ሕዝቡን ወደ ርስቱ እዲሄድ አደረገ። እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የጌታ ባርያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ግዛት በተምና-ሴራ ቀበሩት። ኢያሱ በኖረበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የጌታን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል ጌታን አገለገሉ። የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ ብር በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፤ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት።