ኢያሱ 23:6-16
ኢያሱ 23:6-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ትጠብቁና ታደርጉ ዘንድ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። በእናንተም መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውም ስሞች በእናንተ መካከል አይጠሩ፤ አትማሉባቸውም፤ አታምልኳቸውም፤ አትስገዱላቸውም፤ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ። እርሱ እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኀይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ ያጠፋቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ የተቋቋማችሁ በፊታችሁ ማንም የለም። አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ነገረን ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። አምላካችን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ፥ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በእግራችሁም ችንካር፥ በዐይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያጠፋቸው ራሳችሁ ዕወቁ። “እኔም በምድር እንዳሉት ሰዎች ሁሉ ዛሬ ወደ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም አምላካችን እግዚአብሔር ስለ እኛ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ፥ በነፍሳችሁም ሁሉ ዕወቁ፤ ሁሉ ደርሶናል፤ ከእርሱም ያላገኘነው የለም። አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ብታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።”
ኢያሱ 23:6-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ። በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋራ አትተባበሩ፤ የአማልክታቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ። “እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቷቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት የሚዋጋላችሁ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ አንዱ ሰው ሺሑን ያሳድዳል። ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ። “ነገር ግን ከርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋራ ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና እንቅፋት፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል። “እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሟል። ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል። አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸው የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”
ኢያሱ 23:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፥ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፥ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ እንጂ። እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አስወጥቶአል፥ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በጎናችሁም መግረፊያ፥ በዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ። እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፥ እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፥ ሁሉ ደርሶላችኋል፥ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም። አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።
ኢያሱ 23:6-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህም በኦሪት ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዞች ሁሉ ለመጠበቅ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ከእነርሱም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ አትበሉ። በመካከላችሁ ከቀሩት ሕዝቦች ጋር ከቶ አትተባበሩ፤ የአማልክታቸውንም ስም አትጥሩ፤ በእነርሱም አትማሉ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች አትሁኑ፤ አትስገዱላቸውም። ይልቅስ እስከ አሁን እንዳደረጋችሁት ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ፤ እናንተ ታላላቅና ብርቱዎች የሆኑትን ሕዝቦች እግዚአብሔር ነቃቅሎ አባሮላችኋል፤ እናንተን እስከ ዛሬ ድረስ ሊቋቋማችሁ የቻለ ማንም የለም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ስለ እናንተ ስለሚዋጋ ከእናንተ አንዱ ብቻውን ሆኖ ከእነርሱ ወገን አንዱን ሺህ ማባረር ይችላል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን የምትወዱ መሆን እንደሚገባችሁ በጥንቃቄ አስቡ። እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ርቃችሁ በእናንተ መካከል ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፥ እናንተ የእነርሱን ሴቶች እነርሱ ደግሞ የእናንተን ሴቶች በመጋባት ብትተሳሰሩ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከፊታችሁ ማባረሩን እንደማይቀጥል በእርግጥ ዕወቁ፤ እንዲያውም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስ እነዚህን ሕዝቦች ለጀርባችሁ መግረፊያ፥ ለዐይኖቻችሁ እንደሚወጋ እሾኽ፥ እንዲሁም አደገኛ ወጥመድና መውደቂያ ጒድጓድ ይሆኑባችኋል። “እነሆ እኔ የምሞትበት ጊዜ ደርሶአል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ያደረገላችሁን መልካም ነገር ሁሉ ከእናንተ እያንዳንዱ በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ያውቃል፤ እርሱ ከሰጣችሁ ተስፋ አንድም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል። አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረውን መልካም ነገር ሁሉ እንደ ፈጸመላችሁ፥ እንዲሁም እርሱ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉን ነገር ሁሉ ሊያመጣባችሁ ይችላል። ስለዚህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ቃል ኪዳን በማፍረስ ወደ ሌሎች አማልክት ሄዳችሁ ብታመልኩአቸውና ብትሰግዱላቸው እግዚአብሔርን ታስቈጣላችሁ፤ ከሰጣችሁም መልካም ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”
ኢያሱ 23:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ከእነዚህ አሕዛብ ጋር አትቀላቀሉ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ግን ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ተጠጉ። ጌታ ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አሳድዶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። ጌታ አምላካችሁ እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። ጌታን አምላካችሁንም የምትወድዱ መሆናችሁን እጅግ በጥንቃቄ አስተውሉ። እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ከእነርሱ እነርሱም ከእናንተ ጋር በጋብቻ ቢተሳሰሩ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድና አሽክላ፥ ለጎናችሁም መቅሠፍት፥ ለዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ ጌታ አምላካችሁ ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንደማያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ። “እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም ጌታ ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉም ነገር ተከነናውኖላችኋል፤ ከእርሱም አንድም የቀረ ነገር የለም። ጌታ አምላካችሁ የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ተከናወነላችሁ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ ጌታ እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። ጌታ አምላካችሁ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የጌታ ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።”