ኢያሱ 21:41-45 - Compare All Versions
ኢያሱ 21:41-45 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ካሉ ከመሰማርያዎቻቸው ጋር አርባ ስምንት ከተሞች ነበሩ። እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰማርያቸው ጋር ነበሩ፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። [ኢያሱም በየድንበሮቻቸው ምድርን ማካፈልን ጨረሰ። የእስራኤል ልጆችም ለኢያሱ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ድርሻውን ሰጡት፤ እርሱ የሚፈልጋትን ከተማ በኤፍሬም ተራራ የምትገኘውን ቴምናሴራን ሰጡት፤ ከተማም ሠራባት፤ በውስጧም ተቀመጠ። ኢያሱም በምደረ በዳ በመንገድ የተወለዱትን የገረዘባቸውን የድንጋይ ባልጩቶች ወስዶ በቴምናሴራ አኖራቸው።] እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።
ኢያሱ 21:41-45 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እንግዲህ እስራኤላውያን ርስት አድርገው ከያዙት ምድር ለሌዋውያኑ የተሰጧቸው ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው በአጠቃላይ አርባ ስምንት ነበሩ። እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው መሰማሪያዎች ነበሯቸው፤ መሰማሪያ የሌለው ከተማ አልነበረም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ይሰጣቸው ዘንድ የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ እነርሱም ምድሪቱን ወረሱ፣ መኖሪያቸውም አደረጓት። እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ አንድም ጠላት ሊቋቋማቸው አልቻለም፤ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጥቷቸዋልና። እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሟል።
ኢያሱ 21:41-45 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰምርያቸው ነበሩ። እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰምርያቸው ጋር ነበሩ፥ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸው ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፥ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፥ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፥ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።
ኢያሱ 21:41-45 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
በእስራኤላውያን ይዞታ ሥር የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ከግጦሽ መሬታቸው ጋር አርባ ስምንት ነበሩ። በእነዚህም መሬቶች በእያንዳንዱ ዘሪያ የግጦሽ መሬት ነበራቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ሊሰጣቸው በመሐላ ቃል የገባላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤላውያን ሰጠ። ምድሪቱንም ከወረሱ በኋላ በዚያ ተደላድለው ኖሩ፤ እግዚአብሔርም ለቀድሞ አባቶቻቸው በገባው ቃል መሠረት በአካባቢያቸው ሁሉ ሰላምን ሰጣቸው፤ በጠላቶቻቸው ላይ ብዙ ድልን አቀዳጅቶአቸው ስለ ነበረ ከጠላቶቻቸው አንድ እንኳ በፊታቸው ሊቆም አልቻለም። በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት የገባው ቃል ኪዳን ሁሉ ተፈጸመ እንጂ አንድም የቀረ የለም።
ኢያሱ 21:41-45 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰማሪያቸው ነበሩ። እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው መሰማሪያዎች ነበራቸው፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። ጌታም ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። ጌታም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ማንም ሰው ሊቋቋማቸው አልቻለም፤ ጌታም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ጌታ ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።