ኢያሱ 2:8-11
ኢያሱ 2:8-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን አሳልፎ እንደ ሰጣችሁ ዐወቅሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን መፍራትን በላያችን አምጥትዋልና፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ የተነሣ ቀልጠዋልና። ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት፥ እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን በልባችን ደነገጥን፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእኛ የአንዱም እንኳን ነፍስ አልቀረም።
ኢያሱ 2:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣ እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደ ሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ። ከግብጽ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል። ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና።
ኢያሱ 2:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም።
ኢያሱ 2:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ረዓብም ከመተኛታቸው በፊት ወዳሉበት የቤት ጣራ ወጥታ፥ እንዲህ አለቻቸው፦ “የሀገሪቱ ኗሪዎች በሙሉ በፍርሃት ተውጠው ልባቸው ቀለጠ፤ በሁላችንም ላይ ፍርሀት ስላደረብን እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእናንተ እንደ ሰጠ ዐውቃለሁ፤ ግብጽን ለቃችሁ በወጣችሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ ሰምተናል፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የነበሩትን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን እንዴት እንደ ገደላችሁም ሰምተናል። ስለዚህም ይህን ሁሉ ነገር በሰማን ጊዜ በፍርሃት ልባችን ቀለጠ፤ ወኔአችን ሁሉ ጠፋ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእርግጥ የሰማይና የምድር አምላክ ነው።
ኢያሱ 2:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነርሱም ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ “ጌታ ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ ከእናንተም የተነሣ በፍርሃት መዋጣችንን፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ በፍርሃት እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ጌታ የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ ጌታ አምላካችሁም በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእግዲህ ወዲያ ሰው ሁሉ ሐሞተ ቢስ ሆኖአል።