ኢያሱ 2:1-24
ኢያሱ 2:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የነዌም ልጅ ኢያሱ፥ “ውጡና ምድሪቱን ኢያሪኮን እዩ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ጐልማሶች ሰላዮችን በስውር ላከ። እነዚያም ሁለት ጐልማሶች ሄዱ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሱ፤ ረዓብ ወደሚሉአትም ዘማ ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ። ለኢያሪኮም ንጉሥ፥ “እነሆ፥ ከእስራኤል ልጆች ሰላዮች ሀገራችንን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ” ብለው ነገሩት። የኢያሪኮም ንጉሥ፥ “ሀገራችንን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን በዚችም ሌሊት ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጪ በሉአት” ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፥ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩም ሲዘጋ፥ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ተከተሉአቸው፤ ምንአልባት ታገኙአቸው ይሆናል” አለቻቸው። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በተከመረ እንጨት መካከል በቀርከሃ ጠቅልላ ደብቃቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ ተከተሉአቸው፤ በሩም ተቈለፈ። እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን አሳልፎ እንደ ሰጣችሁ ዐወቅሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን መፍራትን በላያችን አምጥትዋልና፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ የተነሣ ቀልጠዋልና። ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት፥ እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን በልባችን ደነገጥን፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእኛ የአንዱም እንኳን ነፍስ አልቀረም። አሁንም፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ አደረግሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድታደርጉ፥ በእውነት ምልክት ስጡኝ። የአባቴን ቤት፥ እናቴንም፥ ወንድሞቼንና ቤቴንም ሁሉ፥ ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፤ ሰውነታችንንም ከሞት አድኑ።” ሰዎቹም፥ “ሕይወታችንን ስለ እናንተ አሳልፈን ለሞት እንሰጣለን” አሉ፤ እርስዋም አለች፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን በሰጣችሁ ጊዜ ቸርነትንና ጽድቅን ታደርጉልናላችሁ።” ሰዎቹም፥ “ይህን ነገራችንን ባትገልጪ እግዚአብሔር ሀገራችሁን በእውነት አሳልፎ ከሰጠን ከአንቺ ጋር ቸርነትን እናደርጋለን” አሏት። ቤቷም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበርና በመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። እርስዋም፥ “የሚከተሉአችሁ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ የሚከተሉአችሁም እስከሚመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ በኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለቻቸው። ሰዎቹም አሉአት፥ “እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን። እነሆ፥ እኛ ወደ ሀገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም፥ እናትሽንም፥ ወንድሞችሽንም፥ የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ሁሉ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ እኛም ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤትሽ ውስጥ ያለ ቢሞት ደሙ በእኛ ላይ ነው። ነገር ግን ይህን ነገራችንን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን።” እርስዋም፥ “እንደ ቃላችሁ ይሁን” አለች፤ አሰናበተቻቸውም፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። እነርሱም ወጥተው ወደ ተራራው ሄዱ፤ የሚከተሉአቸውና የሚፈልጉአቸውም እስኪመለሱ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ በመንገዱም አላገኙአቸውም። ሁለቱም ጐልማሶች ተመለሱ፤ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፤ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። ኢያሱንም፥ “በእውነት እግዚአብሔር ሀገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ በዚያች ምድር የሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ከእኛ የተነሣ ደነገጡ” አሉት።
ኢያሱ 2:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ ምድሪቱን፣ በተለይም የኢያሪኮን ከተማ ሰልሉ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ፤ ሰዎቹም ሄደው ረዓብ ከተባለች ጋለሞታ ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ። ለኢያሪኮም ንጉሥ፣ “እነሆ፤ ምድሪቱን ሊሰልሉ ጥቂት እስራኤላውያን በሌሊት ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው። የኢያሪኮም ንጉሥ፣ “ወደ አንቺ መጥተው ወደ ቤትሽ የገቡት ሰዎች ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ስለ ሆነ፣ እንድታስወጪአቸው” የሚል መልእክት ወደ ረዓብ ላከ። ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር እንዲህ አለች፤ “በርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም። ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደ ሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።” ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር። ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፤ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደ ሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ። ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣ እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደ ሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ። ከግብጽ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል። ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና። “እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤ የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን እንዲሁም የእነርሱ የሆነውን ነፍስ ሁሉ እንድታተርፉልኝ፤ ከሞትም አድኑን።” ሰዎቹም፣ “የእናንተን ሞት ለእኛ ያድርገው! እኛ የምናደርገውን ሁሉ ካልተናገራችሁ፣ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ፣ በጎነትና ታማኝነት እናሳይሻለን” አሏት። መኖሪያ ቤቷ የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ስለ ነበር፣ ሰዎቹን በመስኮት አሾልካ በገመድ አወረደቻቸው። እርሷም፣ “የሚከታተሏችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ ወደ ኰረብቶቹ ሂዱ፤ እነርሱ እስኪመለሱም ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተሸሸጉ፤ ከዚያ በኋላ መንገዳችሁን ትቀጥላላችሁ” አለቻቸው። ሰዎቹም እንዲህ አሏት፤ “ባማልሽን በዚህ መሐላ የምንያዘው፣ ወደ ምድሪቱ በገባን ጊዜ፣ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽው፣ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፣ ወንድሞችሽንና የአባትሽን ቤተ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ብቻ ነው። ማንም ከቤትሽ ወጥቶ መንገድ ላይ ቢገኝ፣ ደሙ በራሱ ላይ ነው፤ እኛ አንጠየቅበትም፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋራ ቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከተነካ የደሙ ባለዕዳ እኛ እንሆናለን። እኛ የምናደርገውን ብትናገሪ ግን፣ ካስማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።” እርሷም፣ “ይሁን፤ ባላችሁት ተስማምቻለሁ” ስትል መለሰች። ከዚያም ሰደደቻቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀይ ፈትሉንም በመስኮቷ ላይ አንጠለጠለችው። እነርሱም ወጥተው ወደ ኰረብቶቹ ሄዱ፤ የሚከታተሏቸውም ሰዎች በየመንገዱ ሁሉ ላይ ፈልገውና ዐጥተው እስኪመለሱ ድረስ፣ ሦስት ቀን በዚያው ተሸሸጉ። ሁለቱም ሰላዮች ተመለሱ፤ ከኰረብቶቹም ወርደው ወንዙን በመሻገር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጥተው ያጋጠማቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት። ለኢያሱም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሙሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ በዚያ የሚኖረውም ሕዝብ ሁሉ እኛን ከመፍራቱ የተነሣ ልቡ መቅለጡን አይተናል” አሉት።
ኢያሱ 2:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የነዌም ልጅ ኢያሱ፦ ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ። ሄዱም፥ ረዓብም ወደሚሉአት ጋለሞታ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። የኢያሪኮም ንጉሥ፦ እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ ሲባል ወሬ ሰማ። የኢያሪኮም ንጉሥ፦ አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፥ እርስዋም፦ አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደሆኑ ግን አላወቅሁም፥ በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፥ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፥ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ አለች። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፥ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፥ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ። እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም። አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥ አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ። ሰዎቹም፦ ይህን ነገራችንን ባትገልጪ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፥ እግዚአብሔርም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ከአንቺ ጋር ቸርነትንና እውነትን እናደርጋለን አሉአት። ቤትዋም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበረና ከመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። እርስዋም፦ አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፥ ኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለቻቸው። ሰዎቹም አሉአት፦ እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፥ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፥ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። ይህንን ነገራችንን ግን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። እርስዋም፦ እንደ ቃላችሁ ይሁን አለች፥ ሰደደቻቸውም እነርሱም ሄዱ፥ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፥ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፥ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። ኢያሱንም፦ በእውነት እግዚአብሔር አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፥ በአገሩም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፊታችን ይቀልጣሉ አሉት።
ኢያሱ 2:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሺጢም ሰፈር ሁለት ሰላዮችን ላከ፤ እነርሱም የከነዓንን ምድር በተለይም የኢያሪኮን ከተማ በምሥጢር ሰልለው እንዲመለሱ አዘዛቸው፤ ወደ ከተማይቱ በመጡ ጊዜ “ረዓብ” ተብላ ወደምትጠራ ወደ አንዲት ሴትኛ ዐዳሪ ቤት ገብተው ዐደሩ። “አገሪቱን ለመሰለል ከእስራኤላውያን መካከል ዛሬ ማታ ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ለኢያሪኮ ንጉሥ ተነገረው። ከዚህ በኋላ የኢያሪኮ ንጉሥ “ምድሪቱን ሊሰልሉ የመጡ ስለ ሆኑ ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጥተሽ አስረክቢ!” ብሎ ወደ ረዓብ ትእዛዝ ላከ። ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላውቅም፤ ጊዜው መሽቶ በመጨለሙ በሩ ሲዘጋ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ብታሳድዱአቸው ትደርሱባቸዋላችሁ” አለች። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በዚያ በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። የንጉሡም መልእክተኞች ከከተማይቱ ወጥተው ሄዱ፤ የቅጽር በሩም ተዘጋ፤ መልእክተኞቹም ሰላዮችን በመፈለግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ እስከሚያልፈው ስፍራ ድረስ ሄዱ። ረዓብም ከመተኛታቸው በፊት ወዳሉበት የቤት ጣራ ወጥታ፥ እንዲህ አለቻቸው፦ “የሀገሪቱ ኗሪዎች በሙሉ በፍርሃት ተውጠው ልባቸው ቀለጠ፤ በሁላችንም ላይ ፍርሀት ስላደረብን እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእናንተ እንደ ሰጠ ዐውቃለሁ፤ ግብጽን ለቃችሁ በወጣችሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ ሰምተናል፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የነበሩትን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን እንዴት እንደ ገደላችሁም ሰምተናል። ስለዚህም ይህን ሁሉ ነገር በሰማን ጊዜ በፍርሃት ልባችን ቀለጠ፤ ወኔአችን ሁሉ ጠፋ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእርግጥ የሰማይና የምድር አምላክ ነው። አሁንም እኔ ለእናንተ መልካም ነገር እንዳደረግሁላችሁ ሁሉ ቤተሰቤን ከጥፋት በማትረፍ መልካም ነገር ታደርጉልኝ ዘንድ ማሉልኝ፤ ለዚህም መተማመኛ የሚሆን ምልክት ስጡኝ። አባቴንና እናቴን፥ ወንድሞቼን፥ እኅቶቼንና የእነርሱን ቤተሰቦች ሁሉ ከሞት ለማዳን ቃል ግቡልኝ!” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፤ “እኛ በገባንልሽ ቃል መሠረት ባንፈጽም እግዚአብሔር በሞት ይቅጣን! እኛ ያደረግነውን ሁሉ ለማንም ባትነግሪ፥ እግዚአብሔር ይህቺን ምድር ለእኛ አሳልፎ በሚሰጠን ጊዜ ለአንቺ መልካም ነገር ለማድረግ ቃል እንገባለን።” ረዓብ የምትኖርበት ቤት ከከተማይቱ ቅጽር ግንብ ተጠግቶ በውስጥ በኩል የተሠራ ስለ ነበር ሰዎቹ በመስኮት በኩል ቊልቊል በተለቀቀ ገመድ ተንጠልጥለው ወደ ታች እንዲወርዱ አደረገች፤ እንዲህም ስትል መከረቻቸው፤ “ወደ ኮረብታማው አገር ሂዱ፤ ይህ ካልሆነ ግን የንጉሡ መልእክተኞች ሊያገኙአችሁ ይችላሉ፤ በዚያም እነርሱ እስኪመለሱ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ተደብቃችሁ ቈዩ፤ ከዚያን በኋላ ጒዞአችሁን መቀጠል ትችላላችሁ።” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፤ “እኛ ምድሪቱን ለመያዝ በምንመጣበት ጊዜ ይህን ቀይ ገመድ እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል ባታስሪና አባትሽን፥ እናትሽን፥ ወንድሞችሽንና ቤተሰቦችሽን ሁሉ ባትሰበስቢ ካስማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን፤ ማንም ከቤት ወጥቶ ቢገኝና ቢሞት ጥፋቱ የራሱ ይሆናል፤ እኛም በኀላፊነት አንጠየቅም፤ ከአንቺ ጋር በቤት ሳለ ማንም ሰው ጒዳት ቢደርስበት ግን በኀላፊነት ተጠያቂዎች ነን። ይሁን እንጂ ይህን የምናደርገውን ነገር ለማንም ነግረሽ ብትገኚ፥ በጥያቄሽ መሠረት የገባንልሽን ቃል ለመጠበቅ አንገደድም።” እርስዋም በዚህ ተስማምታ ሸኘቻቸው፤ እነርሱም ከሄዱ በኋላ ቀዩን ገመድ በመስኮቱ ላይ አንጠለጠለች። አሳዳጆቻቸው በየመንገዱ ሁሉ ፈልገው ከአጡአቸው በኋላ እስከ ተመለሱ ድረስ ሰዎቹ ወደ ተራራማው አገር ሄደው ለሦስት ቀኖች ተደበቁ። ከዚህም በኋላ ሁለቱ ሰዎች ከተራራው ወረዱ። ዮርዳኖስንም ተሻግረው ወደ ኢያሱ መጥተው ያጋጠማቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት። ለኢያሱም እንዲህ አሉት፦ “የምድሪቱ ነዋሪዎች በሙሉ እኛን በመፍራት ሐሞታቸው ስለ ፈሰሰ በእውነት እግዚአብሔር ምድሪቱን ሁሉ ለእኛ አሳልፎ ሰጥቶአል።”
ኢያሱ 2:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የነዌም ልጅ ኢያሱ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ሄዱ፥ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ።” ሄዱም፤ ረዓብም ወደሚሉአት አመንዝራ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። ለኢያሪኮም ንጉሥ እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ።” የኢያሪኮም ንጉሥ እንዲህ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ፦ “አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ።” ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርሷም እንዲህ አለች፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩ በሚዘጋበት ጊዜ ሲመሻሽ ሰዎቹ ወጥተው ሄደዋል፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ትደርሱባቸዋላችሁ።” እርሷ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ እስከሚወስደው መንገድ ድረስ አሳደዱአቸው፤ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተዘጋ። እነርሱም ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ “ጌታ ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ ከእናንተም የተነሣ በፍርሃት መዋጣችንን፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ በፍርሃት እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ጌታ የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ ጌታ አምላካችሁም በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእግዲህ ወዲያ ሰው ሁሉ ሐሞተ ቢስ ሆኖአል። አሁንም፥ እባካችሁ፥ በጌታ ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት ሥሩ፥ አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፥ ነፍሳችንንም ከሞት ታደጉ።” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፦ “ይህን ነገራችንን ለማንም ባትናገሩ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፤ ጌታም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ለአንቺ ቸርነትንና ታማኝነትን እናደርጋለን።” ቤትዋም የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ነበረና፥ እርሷም በቅጥሩ ውስጥ ተቀምጣ ነበር፤ እነርሱንም በመስኮቱ በኩል በገመድ አወረደቻቸው። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ ከዚያም በኋላ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፦ “እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን ማንም ሰው እጁን ቢጭንበት ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። ይህንን ነገራችንን ግን ብትናገሪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።” እርሷም እንዲህ አለች፦ “እንደ ቃላችሁ ይሁን፤” ከዚያም በኋላ በደኅና አሰናበተቻቸው እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “በእውነት ጌታ አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ ከእኛም የተነሣ በአገሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፍርሃት ቀልጠዋል።”