ኢያሱ 18:1-10
ኢያሱ 18:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፤ በዚያም የምስክሩን ድንኳን ተከሉ፤ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው። ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፥ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር እንዳትወርሱአት እስከ መቼ ድረስ ታቈዩአታላችሁ? ከየነገዳችሁ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎችን አምጡ፥ ተነሥተውም ሀገሪቱን ይዙሩአት፤ ለመክፈልም እንዲያመች ገልጠው ይጻፉአት፤ ወደ እኔም ይመለሳሉ። በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍም ልጆች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ። እናንተም ምድሪቱን በሰባት ክፍል ክፈሏት፤ ወደ እኔም ወዲህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዊ ልጆች በመካከላችሁ እድል ፋንታ የላቸውም፤ ጋድም፥ ሮቤልም፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።” ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን፥ “ሂዱ፤ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፤ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ” ብሎ አዘዛቸው። ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ አዩትም፤ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፤ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ወደ ኢያሱም አመጡ። ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው።
ኢያሱ 18:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መላው የእስራኤላውያን ማኅበር በሴሎ ተሰበሰቡ፣ የመገናኛውንም ድንኳን እዚያው ተከሉ፤ ምድሪቱም ጸጥ ብላ ተገዛችላቸው። ዳሩ ግን ርስት ገና ያልተሰጣቸው ሰባት የእስራኤል ነገዶች ነበሩ። ስለዚህ ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ቸል የምትሉት እስከ መቼ ነው? አሁንም ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰው ምረጡ፤ እኔም ምድሪቱን ተዘዋውረው እንዲያጠኑና እያንዳንዱም ነገድ መውረስ የሚገባውን ድርሻ ዝርዝር መግለጫ ጽፈው እንዲያመጡ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም ወደ እኔ ይመለሳሉ። ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፍሏታል፤ ይሁዳ በደቡብ፣ የዮሴፍ ዘሮች በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን ርስት ይዘው ይኖራሉ። የሰባቱን የመሬት ክፍፍል ዝርዝር መግለጫ ጽፋችሁ ወደ እኔ ታመጡና በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ። ሌዋውያኑ ግን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ርስታቸው ስለ ሆነ በእናንተ መካከል ድርሻ አይኖራቸውም። ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምሥራቅ ዮርዳኖስ የሰጣቸውን ርስት ቀደም አድርገው ወስደዋል።” ሰዎቹ የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናትና ለመመዝገብ ጕዞ ሲጀምሩ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ የምድሪቱን ሁኔታ አጥኑና በዝርዝር ከጻፋችሁ በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም እዚሁ ሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ” አላቸው። ስለዚህም ሰዎቹ ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው አዩ፤ ከነ ከተሞቿም ሰባት ቦታ ከፍለው በጥቅልል ብራና ላይ በዝርዝር ጻፉ፤ ከዚያም በሴሎ ሰፈር ወዳለው ወደ ኢያሱ ተመለሱ። ኢያሱም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ ጣለላቸው፤ ምድሪቱንም እንደየነገዱ ደልድሎ ለእስራኤላውያን አከፋፈላቸው።
ኢያሱ 18:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፥ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው። ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፦ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ እስከ መቼ ለመግባት ቸል ትላላችሁ? ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፥ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይጽፉታል፥ ወደ እኔም ይመለሳሉ። በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፥ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፥ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ። እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወዲህ አምጡልኝ፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ እድል ፈንታ የላቸውም፥ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል። ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፥ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን፦ ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፥ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ ብሎ አዘዛቸው። ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፥ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ። ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው፥ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደ ክፍሎቻቸው ምድሩን ከፈለ።
ኢያሱ 18:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ድል አድርገው ምድሪቱን ከያዙ በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ በሴሎ ተሰብስበው እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳን ተከሉ። ከእስራኤልም ሕዝብ መካከል ገና የርስት ድርሻ ያላገኙ ሰባት ነገዶች ነበሩ፤ ስለዚህም ኢያሱ ለእስራኤላውያን እንዲህ አለ፦ “ገብታችሁ የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ሳትወርሱ የምትቈዩት እስከ መቼ ነው? ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡልኝ፤ እኔም እያንዳንዱ ነገድ ማግኘት የሚገባውን የርስት ድርሻ ለማወቅ የምድሪቱን ሁኔታ አጥንተው እንዲመዘግቡ በመላ አገሪቱ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰው ወደ እኔ ይመጣሉ። እነርሱም የሚያጠኑት ምድር ለሰባቱ ነገድ ይከፋፈላል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል፥ ዮሴፍም በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን የርስት ድርሻ ይዘው ይኖራሉ፤ የእነዚህን ሰባት ክፍያዎች የሚገልጠውንም ማስረጃ በጽሑፍ አድርጋችሁ አምጡልኝ፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ እጥልላችኋለሁ። ይሁን እንጂ የሌዋውያን ድርሻ ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን ማገልገል ስለ ሆነ እነርሱ ከሌሎቻችሁ ጋር የርስት ድርሻ አይኖራቸውም፤ የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት አስቀድመው ወርሰዋል።” ሰዎቹም የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናት ከመሄዳቸው በፊት ኢያሱ፥ “ወደ ምድሪቱ ሁሉ ሂዱ፤ አቀማመጥዋንም አጥንታችሁ መዝግቡ፤ ወደ እኔም ተመልሳችሁ ኑ፤ እኔም በዚህ በሴሎ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ እጥልላችኋለሁ” የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም በአገሪቱ በመላ ተዘዋወሩ፤ ከተሞቹንም ሁሉ መዝግበው ምድሪቱ ለሰባት ነገድ እንዴት እንደምትከፈል በጽሑፍ ገለጡ፤ ከዚህም በኋላ ኢያሱ ወዳለበት ወደ ሴሎ ተመልሰው መጡ፤ ኢያሱም እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ አወጣላቸው፤ ለቀሩትም ለእስራኤል ነገዶች ለእያንዳንዳቸው ተመጣጣኝ የሆነ የርስት ድርሻ ተመደበላቸው።
ኢያሱ 18:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፤ እነርሱም የምድሪቱ ገዢዎች ሆኑ። ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “የአባቶቻችሁ አምላክ ጌታ የሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ እስከ መቼ ቸል ትላላችሁ? ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፤ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይመዘግቡታል፤ ከዚያም በኋላ ወደ እኔ ይመለሳሉ። በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል ባለው ግዛት ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል ባለው ግዛት ውስጥ ይቀመጣሉ። እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወደዚህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በጌታ ፊት በዚህ ዕጣ እጥልላችኋለሁ። ነገር ግን የጌታ ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ ድርሻ የላቸውም፤ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የጌታ ባርያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።” ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ተመልክተው ሊጽፉ የሄዱትን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ እዩና ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በጌታ ፊት ዕጣ እጥልላችኋለሁ።” ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ በከተሞቹም ልክ በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ። ኢያሱም በጌታ ፊት በሴሎ ዕጣ ጣለላቸው፤ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደየድርሻቸው ምድሩን ከፈለ።