ኢያሱ 15:13-19
ኢያሱ 15:13-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ድርሻውን ሰጠው፤ ኢያሱም የዔናቅ ዋና ከተማ የሆነችውን የአርቦቅን ከተማ ሰጠው። እርስዋም ኬብሮን ናት። የዮፎኒ ልጅ ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሱሲን፥ ተለሚንና አካሚን ከዚያ አጠፋቸው። ከዚያም ካሌብ በዳቤር ሰዎች ላይ ዘመተ፤ የዳቤርም ስም አስቀድሞ “ሀገረ መጻሕፍት” ነበረ። ካሌብም፥ “ሀገረ መጻሕፍትን ለሚመታ፥ ለሚይዛትም ልጄን አክሳን ሚስት ትሆነው ዘንድ እሰጠዋለሁ” አለ። የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁን አክሳንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ “አባቴን እርሻ ልለምነው” ብላ አማከረችው፤ እርስዋም በአህያዋ ላይ ሆና ጮኸች፤ ካሌብም፥ “ምን ሆንሽ?” አላት። እርስዋም፥ “በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ” አለችው። እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት።
ኢያሱ 15:13-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከይሁዳ ድርሻ ላይ ከፍሎ ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጠው፤ አርባቅም የዔናቅ አባት ነበረ። ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ዘሮች ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ከኬብሮን አሳደዳቸው፤ ከዚያም በዳቤር ሕዝብ ላይ ዘመተ፤ ዳቤር ቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር። ካሌብ፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዝ ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ። ስለዚህ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዛት፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት። ዓክሳ ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜም፣ ከአባቷ ላይ የዕርሻ መሬት እንዲለምን አጥብቃ ነገረችው። ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች ካሌብ፣ “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት። እርሷም፣ “እባክህ፤ ባርከኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ጕድጓዶች ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።
ኢያሱ 15:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዳዘዘው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ ድርሻ አድርጎ ሰጠው፥ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ከዚያ አሳደደ። ከዚያም በዳቤር ሰዎች ላይ ወጣ፥ የዳቤርም ስም አስቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበረ። ካሌብም፦ ቂርያትሤፍርን ለሚመታ ለሚይዛትም ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ። የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፥ ልጁንም ዓክሳን አጋባው። እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው፥ እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፥ ካሌብም፦ ምን ፈለግሽ? አላት። እርስዋም፦ በረከትን ስጠኝ፥ በደቡብም በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ አለችው። እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት።
ኢያሱ 15:13-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት ለይፉኔ ልጅ ለካሌብ ከይሁዳ ነገድ ኪርያት ዐርባን ወይም ኬብሮን እርስት አድርጎ ሰጠው። (አርባ የዐናቅ አባት ነበር) ካሌብም የዐናቅን ሦስት ልጆች ሼሻይን፥ አሒማንና ታልማይን አባረረ፤ እነርሱም የዐናቅ ዘሮች ነበሩ። ከዚያም ተነሥቶ በደቢር በሚኖሩት ሕዝብ ላይ አደጋ ለመጣል ሄደ፤ ይህች ከተማ ቀድሞ ቂርያትሴፌር ተብላ ትጠራ ነበር፤ ካሌብም፥ “ቂርያትሴፌርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” ብሎ ተናገረ፤ ስለዚህም የካሌብ ወንድም ከሆነው ከቀናዝ የተወለደው ዖትኒኤል ያችን ከተማ ወግቶ ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት፤ ዖትኒኤልም በሠርጋቸው ቀን ዓክሳን ከአባትዋ የእርሻ መሬት እንድትለምን መከራት፤ እርስዋም ከበቅሎዋ ላይ ወረደች፤ (መሳ 1፥14 ተመልከት) ካሌብም “ምን ትፈልጊአለሽ” ሲል ጠየቃት፤ እርስዋም “የሰጠኸኝ ምድር ደረቅ ስለ ሆነ ጥቂት የውሃ ጒድጓዶች እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ካሌብም ከላይና ከታች በኩል ያሉትን ሁለቱን የውሃ ምንጮች ሰጣት።
ኢያሱ 15:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ኢያሱን እንዳዘዘው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ቂርያት-አርባቅ የምትባለውን ከተማ ድርሻ አድርጎ ሰጠው፤ እርሷም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ከዚያ ስፍራ አሳደደ። እነዚህም የዓናቅ ትውልድ ነበሩ። ከዚያም በዳቤር ሰዎች ላይ ወጣ፤ የዳቤርም ስም አስቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበረ። ካሌብም፦ “ቂርያትሤፍርን ለሚመታ ለሚይዛትም ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ” አለ። የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ስለዚህ ካሌብ ልጁን ዓክሳንን አጋባው። እርሷም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው፤ እርሷም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም፦ “ምን ፈለግሽ?” አላት። እርሷም እንዲህ አለችው፦ “በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብም በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ።” እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት።