ኢያሱ 13:1-32
ኢያሱ 13:1-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሱም ሸመገለ፤ ዘመኑም አለፈ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “እነሆ ዘመንህ አለፈ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤ የቀረችውም ምድር ይህች ናት፤ የፍልስጥኤማውያን፥ የጌሴርያውያንና የከነዓናውያን ሀገር ሁሉ፥ በግብፅ ፊት ካለው ምድረ በዳ ጀምሮ ለአምስቱ የፍልስጥኤም ግዛቶች ለጋዛ፥ ለአዛጦን፥ ለአስቀሎና፥ ለጌት፥ ለአቃሮን፥ እንዲሁም ለኤዌዎናውያን በተቈጠረችው በከነዓን ግራ በኩል እስካለችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ ነው፤ ከደቡብ ጀምሮ በጋዛና በሲዶና ፊት ያለውን የከነዓናውያን ምድር ሁሉ እስከ አሞሬዎናውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ በፍልስጥኤም ያለው የጌባላውያን ምድር ሁሉ፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው ጌልገላ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ በተራራማውም ሀገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሬትሜምፎማይም መያያዣ ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፤ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አጠፋቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው። አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ፥ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው። ከዮርዳኖስ ጀምሮ በምዕራብ እስካለው ታላቁ ባሕር ድረስ ትሰጣቸዋለህ፤ ድንበራቸውም ታላቁ ባሕር ይሆናል።” የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴም እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሚሶር ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞሬዎን ንጉሥ የሴዎን ከተሞችን ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ ገለዓድንም፥ የጌሴሪያውያንንና የመከጢያውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ ባሳንንም ሁሉ፥ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን፥ በአስታሮትና በኤንድራይን የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ከረዓይት የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ አወጣቸው፤ ገደላቸውም። የእስራኤል ልጆች ግን ጌሴሪያውያንን፥ መከጢያውያንንና ከነዓናውያንን አላጠፉአቸውም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሴሪና መከጢ በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልተሰጠም፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ርስታቸው ነውና፥ በኢያሪኮ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች እንዳካፈላቸው እንዲሁ ተካፈሉ። ሙሴም ለሮቤል ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ ሜሶርም ሁሉ፥ ሐሴቦን፥ በሜሶርም ያሉት ከተሞች ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበዐል፥ ቤትበአልምዖን፥ ባሳን፥ ቀዲሞት፥ ሜፍዓ፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ ሲራዳት፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ሲዮን፥ ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትሲሞት፥ የሚሶር ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞሬዎናውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቦቅን፥ ሱርን፥ ኡርን፥ ሮቤን በሲዮን የሚኖሩትንም ገደላቸው። ሟርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምንም በአንድነት በሰይፍ ገደሉት። የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በራባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ አራቦት መሴፋ፥ እስከ ቦጣኒም ድረስ፥ ከማኦን ጀምሮ እስከ ዴቦን ዳርቻ ድረስ፥ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትንምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኬኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበረ። የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም፥ መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። በጠላቶቻቸውም ፊት ጀርባቸውን መልሰው ሸሹ፤ መንደሮቻቸውና ከተሞቻቸው በየወገናቸው ሆነዋልና። ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ርስት ሰጣቸው፤ ድንበራቸውም ከመሐናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስጣሮትና ኤድራይን ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፤ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች እኩሌታም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ ርስት ያካፈላቸው እነዚህ ናቸው።
ኢያሱ 13:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢያሱ በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ አርጅተሃል፤ ዕድሜህም ገፍቷል፤ ነገር ግን መያዝ ያለበት እጅግ በጣም ሰፊ ምድር ገና አለ። “የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፤ “እርሱም የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ ነው፤ ከግብጽ በስተምሥራቅ ከሚገኘው ከሺሖር ወንዝ አንሥቶ፣ በሰሜን እስከ አቃሮን ወሰን ያለው አገር፣ ሁሉም እንደ ከነዓናውያን ምድር ይቈጠራል። ይኸውም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣ በአስቀሎና፣ በጋትና በአቃሮን የሚኖሩትን የዐምስቱን የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምድር የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም የኤዋውያን ምድር ነበር። በደቡብ በኩል፤ የከነዓናውያን ምድር ሁሉና የሲዶናውያን ይዞታ ከሆነችው ከመዓራ አንሥቶ እስከ አፌቅ ያለው የአሞራውያን ግዛት፣ የጌባላውያንም ምድር፤ በምሥራቅም ከበኣልጋድ አንሥቶ በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ዐልፎ፣ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው የሊባኖስ ምድር ሁሉ ነው። “ከሊባኖስ እስከ ማስሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል። ይህንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።” ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ እንደየድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ። ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤ እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል። በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል። ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር። እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቍርባን በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና። ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣ ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣ ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣ ቂርያታይምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣ ቤተ ፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣ ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው። በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ሟርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት። የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣ ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጳና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣ በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል። የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ። ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ማለት ለገሚሱ የምናሴ ቤተ ሰብ ዘሮች በየጐሣቸው የሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤ ድንበራቸው ከመሃናይም አንሥቶ ባሳንን በሙሉ ይጨምርና፣ በባሳን ያሉትን ስድሳ የኢያዕር ከተሞች ሁሉ ይዞ የባሳን ንጉሥ የዐግን ግዛት ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣ የገለዓድን እኩሌታ፣ በባሳን የዐግ መንግሥት ዋና ከተማ የሆኑትን አስታሮትንና ኤድራይን ይጨምራል። እነዚህ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ዘሮች የተሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለግማሾቹ የማኪር ልጆች በየጐሣቸው የተሰጡ ናቸው። ሙሴ ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።
ኢያሱ 13:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ፥ እግዚአብሔርም አለው፦ አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፥ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፥ የቀረችውም ምድር ይህች ናት፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ በግብፅ ፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ በደቡብም በኩል የኤዋውያን፥ የከነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ የጌባላውያንም ምድር፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፥ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፥ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው። አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፥ እርሱም ከራፋይም የቀረ ነበረ፥ እነዚህንም ሙሴ መታቸው አወጣቸውም። የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላወጡም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የቀረበው በእሳት የተደረገ መሥዋዕት ርስታቸው ነው፥ እርሱ እንደ ተናገራቸው። ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥ ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥ ቤትባኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥ ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥ ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትየሺሞት፥ የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፥ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን መታቸው። ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት። የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር። የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፥ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ድንበራቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፥ ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የከፈለው ርስት ይህ ነው።
ኢያሱ 13:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነሆ፥ ኢያሱ በዕድሜ እየገፋ ስለ ሄደ አረጀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፤ ዕድሜህም ገፍቶአል፤ ገና ብዙ ያልተያዙ ቦታዎች አሉ። ገና ያልተያዙትም እነዚህ ናቸው፦ የፍልስጥኤምና የገሹር ግዛት በሙሉ፥ እነዚህም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ካለው ከሺሆን ወንዝ ጀምሮ ወደ ሰሜን እስከ ኤክሮን ድንበር ድረስ ያለው ነው። ይህም በአጠቃላይ ከነዓን ተብሎ ይጠራል። እርሱም የአምስቱ የፍልስጥኤም ማለት የጋዛ፥ የአሽዶድ፥ የአስቀሎና፥ የጋትና የኤክሮን ነገሥታት ግዛት ነው። ሌሎች ያልተያዙ ደግሞ በደቡብ በኩል ያለው የአቢብ ግዛት ነው። በሌላም በኩል የሲዶናውያን ይዞታ የሆነው የከነዓን አገር መዓራ ተብሎ የሚጠራውን ሁሉ ጨምሮ በአሞራውያን ጠረፍ እስከ አፌቅ ድረስ የሚገኘው፥ የጌባላውያን ምድርና ከምሥራቅ በአርሞንኤም ተራራ ደቡብ ከሚገኘው ከባዓልጋድ ተነሥቶ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው መላው ሊባኖስ ገና አልተያዘም። ከሊባኖስ እስከ ሚስረፎትማይም ድረስ በተራራማው አገር የሚኖሩ ነዋሪዎች፥ ማለት ሲዶናውያንን ሁሉ፥ እኔ ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አባርራቸዋለሁ፤ አንተ ግን እኔ እንዳዘዝኩህ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ አከፋፍል። ይህንንም ምድር ርስት አድርገህ የምታካፍለው ለዘጠኙ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ነው።” የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በርስትነት የሰጣቸውን ምድር ቀደም ብለው ተረክበዋል። ይህም ምድር የሚገኘው በስተምሥራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ነው። ግዛታቸውም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ከሆነው ከዓሮዔር ተነሥቶ እንዲሁም በሸለቆው መካከል ካለው ከተማ ከሜዴባ ሜዳ እስከ ዲቦን ድረስ ይደርሳል። በሌላም በኩል በሓሴቦን እስከ አሞናውያን ድንበር ድረስ የነገሠውን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል። እርሱም ገለዓድን፥ የገሹርንና የማዕካን አውራጃዎችና የአርሞንኤምን ተራራ በሙሉ እንዲሁም እስከ ሳለካ ድረስ ያለውን ባሳንን ይጨምራል። ከራፋይማውያን ተራፊ የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የባሳንን ንጉሥ የዖግን መንግሥት ሁሉ ይጨምራል። ሙሴም እነዚህን ድል አድርጎ አስወጣቸው። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የገሹርንና የማዕካን ሕዝብ አላስወጡም፤ ነገር ግን እነርሱ እስከ አሁን በእስራኤላውያን መካከል ይኖራሉ። ሙሴ ለሌዊ ነገድ የርስት ድርሻ አልሰጠም፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በመሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ከሚቀርበው መባ የሚያገኙት ድርሻ እንደ ርስት ሆኖ ተመድቦላቸዋል። ሙሴ ለሮቤል ነገድ በየወገናቸው ርስት ሰጣቸው፤ ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ እስከሚገኘው እስከ ዓሮዔርና በዚያም ሸለቆ መካከል እስካለችው ከተማ አልፎ በሜደባ ዙሪያ ያለውን ሜዳማ አገር ሁሉ ያጠቃልላል፤ እንዲሁም ሐሴቦንን፥ በደጋማ አገር ያሉትን ከተሞች፥ ዲቦን፥ ባሞትበዓል፥ ቤትበዓልመዖን፥ ያሀጽ፥ ቀዴሞት፥ ሜፋዓት፥ ቂርያታይም፥ ሲበማ፥ በኮረብታማው ሸለቆ የሚገኘው ጼሬትሻሐር፥ ቤትፐዖር፥ ከፒስጋ ተራራ በታች ያለው ረባዳ ምድርና ቤትየሺሞት ተብለው የሚጠሩትን ሁሉ ይጨምራል። በደጋማው አገር የሚገኙትን ከተሞችና መኖሪያውን በሐሴቦን አድርጎ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖንን ግዛት ሁሉ ይጨምራል። ሙሴም ንጉሥ ሲሖንንና የምድያም መሪዎች የነበሩትን፥ ኤዊን፥ ሬቄምን፥ ጹርን፥ ሑርንና ሬባዕን ድል ነሣ፤ እነዚህ ሁሉ ምድሪቱን የሚያስተዳድሩት የንጉሥ ሲሖን ገባሮች በመሆን ነበር። የእስራኤል ሕዝብ ከገደሉአቸውም መካከል አንዱ ጠንቋይ እየተባለ ይጠራ የነበረው የቢዖር ልጅ በለዓም ነበር። በምዕራብ በኩል የዮርዳኖስም ወንዝ ለሮቤል ነገድ የርስቱ ወሰን ነበር፤ እንግዲህ ለሮቤል ነገድ ቤተሰቦች ርስት ሆነው የተሰጡአቸው ከተሞችና መንደሮች እነዚህ ነበሩ። ሙሴ ለጋድ ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጠ፤ የእነርሱም ግዛት ያዕዜርንና በገለዓድ የሚገኙትን ከተሞች ሁሉ የዐሞንን ምድር እኩሌታ ጨምሮ ከራባ በስተምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ዓሮዔር ይደርሳል። የምድራቸውም ስፋት ከሐሴቦን ተነሥቶ እስከ ራማት ምጽጳና እስከ ቤጦኒም እንዲሁም ከማሕናይም ተነሥቶ እስከ ሎዴባር ድንበር ይደርሳል፤ ከዮርዳኖስ ሸለቆ በተለይ የሐሴቦን ንጉሥ የሲሖን መንግሥት ቅሬታ የሆኑትን ቤትሐራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮትና ጻፎን ተብለው የሚጠሩትን ጭምር ያጠቃልላል፤ በምዕራብ በኩል የሚዋሰናቸውም የዮርዳኖስ ወንዝ ሲሆን፥ በሰሜን እስከ ገሊላ ባሕር ይደርሳል። እንግዲህ ለጋድ ነገድ ቤተሰቦች ርስት ሆነው የተሰጡአቸው ከተሞችና መንደሮች እነዚህ ነበሩ። ሙሴ ለግማሹ የምናሴ ነገድ ርስት ሰጠ፤ የሰጣቸውም እንደየቤተሰባቸው በማከፋፈል ነበር። ግዛታቸውም ማሕናይምንና ባሳንን ሁሉ ያጠቃልላል፤ ይህም ባሳን መላውን የባሳን ንጉሥ የዖግን ግዛት እንዲሁም በባሳን በተለይ ያኢር ተብላ በምትጠራው ስፍራ የሚገኙትን ሥልሳ ከተሞች ሁሉ ይጨምራል፤ እንዲሁም የገለዓድ እኩሌታ፥ አስታሮት እና ኤድራይ እነርሱም በባሳን የንጉሥ ዖግ ከተሞች የነበሩት ይህም ከምናሴ ነገድ ለእኩሌቶቹ የማኪር ልጆች እንደየወገናቸው ተከፋፈሉት። በሞአብ ሜዳ በነበረበት ጊዜ ሙሴ በኢያሪኮና በዮርዳኖስ ምሥራቅ ወንዝ ያለውን ምድር ያከፋፈለው በዚህ ዐይነት ነበር።
ኢያሱ 13:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢያሱም ሸመገለ ዕድሜውም ስለ ገፋ አረጀ፤ ጌታም እንዲህ አለው፦ “አንተ ሸምግለሃል፥ ዕድሜህም ስለ ገፋ አርጅተሃል፤ ያልተወረሰ እጅግ ብዙ ምድር ገና ይቀራል፤ ሳይያዝ የቀረውም ምድር ይህ ነው፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ በግብጽ ፊት ለፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ናቸው፥ የኤዋውያን የሆኑትም እንዲሁ፥ በደቡብም በኩል የነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ የጌባላውያንም ምድር፥ በፀሐይም መውጫ በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፥ እኔ ራሴ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ብቻ ርስት አድርገህ አካፍላቸው። እንግዲህ አሁን ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው።” የጌታ ባርያ ሙሴ እንደሰጣቸው ከሌሎቹ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ብቻ ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አድርጎ አስወጣቸው። የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላስወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ እርሱ እንደ ተናገራቸው እንዲሁ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ርስታቸው ነው። ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥ ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥ ቤትባኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥ ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥ ቤተ ፌጎር፥ የፈስጋ ተዳፋት መሬት፥ ቤትየሺሞት፥ የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም ሴዎንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን ድል ነሣቸው። ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት። የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። ግዛታቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት ለፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥ በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የተቀረውም የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር። የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፤ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ድርሻቸው ይህ ነበረ። ግዛታቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ድርሻቸው ሆነ። ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ ያከፋፈለው ርስት ይህ ነው።