ኢያሱ 11:1-23
ኢያሱ 11:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማሮን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ስሚዖን ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥ በመስዕም በተራራማው ሀገር ፥ በከነሬትም ዐዜብ በዓረባ፥ በቆላውም ባለ በፊናዶር ሸለቆ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ በምሥራቃዊ ባሕር ዳርቻ ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞሬዎናዊውም፥ ወደ ኬጤዎናዊውም፥ ወደ ፌርዜዎናዊውም፥ በተራራማውም ሀገር ወዳለው ወደ ኢያቡሴዎናዊው፥ በቆላማውና በመሴፋ ወዳለው ወደ ኤዌዎናዊዉም ላከ። እነርሱ፥ ከእነርሱም ጋር ሠራዊቶቻቸው ሁሉ ብዛታቸው እንደ ባሕር አሸዋ ሆነው ወጡ፤ ፈረሶችና ሰረገሎችም እጅግ ብዙዎች ነበሩ። እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው መጡ፤ እስራኤልንም በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ተያያዙአቸው። እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “በእስራኤል ፊት ይሞቱ ዘንድ ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ” አለው። ኢያሱና ተዋጊዎች ሕዝብም ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጡባቸው፤ በተራራማውም ቦታ ወደቁባቸው። እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፤ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ሞሳሕ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፤ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። በእነዚያም ወራት ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። በእርስዋም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ገደሉ፤ እስትንፋስ ያላቸውንም ሁሉ ሳያስቀሩ ሁሉንም አጠፉአቸው፤ አሶርንም በእሳት አቃጠላት፤ የእግዚአብሔርም አገልጋይ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን መንግሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ንጉሦቻቸውንም ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው። ከአቃጠሏት ከአሶር ብቻ በቀር እስራኤል በየአውራጃቸው የነበሩትን ሌሎች ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም። የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ፥ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አንድም አላስቀሩም። እግዚአብሔርም አገልጋዩን ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፤ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ ፥ ሜዳውንም፥ በምዕራብ በኩል ያለውንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቆላውን ያዘ፤ እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ከኤኬል ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች እስከ ሊባኖስ ሜዳና እስከ በላጋድ ድረስ፤ ንጉሦቻቸውን ሁሉ ይዞ መታቸው፤ ገደላቸውም። ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚሁ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዎናውያን በቀር፤ እስራኤል ያልያዙት ከተማ አልነበረም፥ ሁሉን በጦርነት ያዙ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ እንዳይራሩላቸው ፈጽመው እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ እግዚአብሔር ልባቸውን አጸና። በዚያ ጊዜም ኢያሱ ሄደ፤ በተራራማውም ሀገር የሚኖሩ ኤናቃውያንን ከኬብሮንና ከዳቤር፥ ከአናቦትም፥ ከእስራኤልም ተራራ ሁሉ፥ ከይሁዳም ተራራ ሁሉ አጠፋቸው፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። በጋዛ፥ በጌትም፥ በአዛጦንም ከቀሩት በቀር በእስራኤል መካከል ከኤናቃውያን ማንንም አላስቀረም። እግዚአብሔርም ለሙሴ እንዳዘዘው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸው በየነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከጦርነት ዐረፈች።
ኢያሱ 11:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ማዶን ንጉሥ፣ ወደ ዮባብ ንጉሥ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አዚፍ ንጉሥ ላከ። እንዲሁም በተራራማው አገር ከኪኔሬት ደቡብ በዓረባ፣ በምዕራቡ ቈላ አገርና ከዶር ኰረብታ በስተምዕራብ ወዳሉት ነገሥታት ላከ፤ ደግሞም በምሥራቅና በምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያንና በኰረብታማው አገር ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን፣ እንዲሁም ደግሞ በምጽጳ ምድር በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ወዳሉት ወደ ኤዊያውያን ነገሥታት መልእክት ላከ። እነዚህም ሰራዊታቸውን ሁሉ እጅግ ብዙ ከሆኑ ፈረሶችና ሠረገሎች ጋራ ይዘው ወጡ፤ የሰራዊቱም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሥታት እስራኤልን ለመውጋት ኀይላቸውን አስተባብረው በማሮን ውሃ አጠገብ በአንድነት ሰፈሩ። እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነዚህን ሁሉ ነገ በዚች ሰዓት እንደ ሙት አድርጌ፣ በእስራኤል እጅ አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍራቸው። የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም ታቃጥላለህ” አለው። ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውሃ መጥተው ወጓቸው። እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ስለ ሰጣቸው ድል አደረጓቸው። በታላቂቱ ሲዶና መንገድ መጨረሻ እስከ ማስሮን፣ በስተ ምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዷቸው፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም አቃጠለ። በዚያ ጊዜም ኢያሱ ወደ ኋላ ተመልሶ አሦርን ያዘ፤ ንጉሧንም በሰይፍ ገደለው፤ አሦርም ቀድሞ በእነዚህ ሁሉ መንግሥታት ላይ የበላይነት ነበራት። በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድ እንኳ ሳያስቀሩ ሁሉንም ደመሰሱ፤ ራሷን አሦርንም በእሳት አቃጠሏት። ኢያሱ እነዚህን የነገሥታት ከተሞች በሙሉና ነገሥታታቸውን ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም ስለት ፈጃቸው፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ ደመሰሳቸው። ያም ሆኖ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአሦር በቀር፣ እስራኤላውያን በየተራራው ላይ ያሉትን ከተሞች አላቃጠሉም ነበር። እስራኤላውያን ምርኮውን በሙሉ፣ ከእነዚህም ከተሞች የተገኙትን እንስሳት ለራሳቸው ወሰዱ፤ ሕዝቡን ግን በሙሉ በሰይፍ ስለት ፈጁት፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድም ሰው ሳያስቀር ፈጽመው ደመሰሱት። እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ፣ ሙሴም ኢያሱን አዘዘው፤ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ እርሱ ያልፈጸመው አንዳች ነገር አልነበረም። ኢያሱ ያን ምድር በሙሉ፣ ማለት ተራራማውን አገር፣ ኔጌብን ሁሉ፣ የጎሶምን ምድር በሙሉ፣ የምዕራቡን ቈላ፣ ዓረባን እንዲሁም የእስራኤልን አገር ደጋውንና ቈላውን ጠቅልሎ ያዘ፤ እንዲሁም እስከ ሴይር በሚደርሰው ከሐላቅ ተራራ አንሥቶ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስ ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ያዘ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ ያዘ፤ መትቶም ገደላቸው። ኢያሱ ከእነዚህ ነገሥታት ጋራ ብዙ ዘመን የፈጀ ጦርነት አደረገ። በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር፣ ከእስራኤላውያን ጋራ የሰላም ውል ያደረገ አንድም ከተማ አልነበረም፤ ሁሉንም የያዙት በጦርነት ነው። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ያለ አንዳች ርኅራኄ ፈጽሞ ይደመስሳቸው ዘንድ እስራኤልን እንዲወጉ ልባቸውን ያደነደነው ራሱ እግዚአብሔር ነውና። በዚያ ጊዜ ኢያሱ ሄዶ በተራራማው አገር፣ ማለት በኬብሮን፣ በዳቤርና በዓናብ እንዲሁም በመላው የይሁዳና የእስራኤል ተራራማ አገሮች ያሉትን የዔናቅን ዘሮች ከነከተሞቻቸው በሙሉ ደመሰሳቸው። ከእነዚህም ጥቂቶቹ ብቻ በጋዛ፣ በጋትና በአሽዶድ ሲቀሩ፣ በእስራኤል የቀሩ የዔናቅ ዘሮች ግን አልነበሩም። ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን በሙሉ ያዘ፤ እንደ ነገዳቸው አከፋፈል በመመደብም ርስት አድርጎ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው። ከዚያም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።
ኢያሱ 11:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥ በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞና ሠረገሎች ጋር ወጡ፥ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ። እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፥ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው። ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም። እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፥ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፥ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፥ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፥ አሶርንም በእሳት አቃጠላት። የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። እስራኤልም በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም፥ ነገር ግን እስራኤል አሶርን ብቻ አቃጠሉአት። የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፥ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። እግዚአብሔርም ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፥ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በአልጋድ ድረስ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፥ ሁሉን በሰልፍ ያዙ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ ሞገስንም እንዳያገኙ ፈጽመውም እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፥ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። እግዚአብሔርም ለሙሴ እንደ ነገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፥ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸውና እንደ ነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፥ ምድሪቱም ከሰልፍ ዐረፈች።
ኢያሱ 11:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሐጾር ንጉሥ ያቢን የእስራኤልን ድል አድራጊነት በሰማ ጊዜ፥ ወደ ማዶን ንጉሥ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንና ወደ አክሻፍ ነገሥታት፥ በሰሜን በኩል በኮረብታማው አገር፥ ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ ወደ ነበሩበት ነገሥታት፥ በዮርዳኖስ ሸለቆ፥ በኮረብታዎቹ ግርጌ በስተምዕራብም በፎት ዳር ወደ ነበሩት ነገሥታት ላከ። እንዲሁም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ሒታውያን፥ ወደ ፈሪዛውያንና፥ በኮረብታማው አገር ወደሚገኙት ወደ ኢያቡሳውያን፥ እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሔርሞን ተራራ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሒዋውያን ሁሉ መልእክት ላከ። እነርሱም ከነወታደሮቻቸው ስለ መጡ፥ የሠራዊቱ ብዛት እንደ ባሕር አሸዋ ሆነ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ነበራቸው። እነዚህም ሁሉ ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው እስራኤላውያንን ለመውጋት በሜሮም ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራ፤ ስለ እስራኤል በመዋጋት ነገ ይህን ጊዜ ሁሉንም እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አንተም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ” አለው። ስለዚህም ኢያሱና መላ ሠራዊቱ ዘምተው በሜሮም ድንገተኛ አደጋ ጣሉባቸው። እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በእነርሱ ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረጋቸው፤ እስራኤላውያንም መተው በሰሜን እስከ ሚስረፎትማይምና እስከ ታላቂቱ ሲዶና፥ በምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው እንኳ ሳይተርፍ ሁሉንም ፈጁአቸው። ኢያሱም በእነርሱ ላይ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ይኸውም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። ኢያሱም ወደ ኋላ ተመልሶ ሐጾርን ድል ነሥቶ ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ ሐጾር በዚያን ዘመን ከነበሩት የዘውድ መንግሥታት ሁሉ የሚበልጥ ኀይል ያላት ነበረች። እስራኤላውያን በሐጾር የተገኘውን ሰው ሁሉ ስለ ገደሉ በሕይወት የተረፈ አልነበረም፤ ከተማይቱም በእሳት ተቃጠለች። የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኢያሱ እነዚህን ከተሞችና ንጉሦቻቸውን ሁሉ ማረከ፤ በሰይፍም መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው። ይሁን እንጂ ኢያሱ ካቃጠላት ከሐጾር በቀር እስራኤላውያን በኮረብታ ላይ የተሠሩ ከተሞችን አላቃጠሉም። የእስራኤል ሕዝብ ዋጋ ያለውን ንብረትና ከብቱን ሁሉ ከእነዚህ ከተሞች ወስደው የራሳቸው ንብረት አደረጉት፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ፤ አንድ ሰው እንኳ ሳይቀር ሁሉንም ገደሉ። እግዚአብሔር ትእዛዙን ለአገልጋዩ ለሙሴ ሰጠ፤ ሙሴም ለኢያሱ ሰጠ፤ ኢያሱም ትእዛዞችን ፈጸመ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ሁሉን ነገር አደረገ፤ አንዳችም አላስቀረም። ኢያሱ እነዚያን አገሮች፦ ተራራማውን፥ ኔጌብን፥ የጎሼንን ምድር፥ ቈላማውን፥ የዮርዳኖስን ሸለቆ፥ ቈላማውንና ደጋማውን የእስራኤልን ምድር ሁሉ ያዘ። እርሱም ወደ ኤዶም ከሚያወጣው ከሐላቅ ተራራ ጀምሮ ከሔርሞን ተራራ በታች እስከ ሊባኖስ ሸለቆ እስከ ባዓልጋድ ድረስ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ማርኮ መታቸው፤ ገደላቸውም፤ ኢያሱም ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ስምምነት አድርጋ በሰላም የኖረች አገር ከሒዋውያን ወገን የገባዖን ኑዋሪዎች በቀር ሌላ አልነበረም፤ ሌሎቹ በሙሉ በጦርነት ድል ሆነው የተያዙ ናቸው። እነዚህም ሁሉ ከእስራኤላውያን ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ እግዚአብሔር ልባቸውን እልኸኛ አድርጎ አነሣሣቸው። ስለዚህም በአጠቃላይ እንዲደመሰሱ ተፈርዶባቸው ያለ ምሕረት ተገደሉ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ ይኸው ነበር። በዚህን ጊዜ ዘምቶ ረጃጅሞች የሆኑትን የዐናቅን ዘሮች ደመሰሰ፤ እነርሱም በኮረብታማው አገር በኬብሮን፥ በደቢር፥ በዐናብ፥ በይሁዳና በእስራኤል ኮረብታማ አገሮች የሚኖሩ ነበሩ። ኢያሱ እነዚህን ሕዝቦችና ከተሞቻቸውን ሁሉ ደመሰሰ። ከዐናቅ ዘሮች በእስራኤል ምድር የተረፈ አልነበረም፤ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ በጋዛ፥ በጋትና በአሽዶድ ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ምድሩን ሁሉ በእጁ አደረገ፤ ለእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ድርሻ ርስት አድርጎ በመስጠት ለእስራኤላውያን በሙሉ አከፋፈለ። ስለዚህም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።
ኢያሱ 11:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ፤ የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አክሻፍም ንጉሥ፥ በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ፥ በቍጥር ም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ከሚሆን ብዙ ሕዝብ፥ እጅግም ከሚበዙ ፈረሶችና ሰረገሎች ጋር በመሆን ወጡ። እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ኃይላቸውን አስተባብረው እስራኤልን ለመውጋት መጡ፤ በማሮንም ውኃ አጠገብ በአንድ ላይ ሰፈሩ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ጊዜ እኔ ሁሉንም እንደሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ።” ኢያሱም ከተዋጊዎቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ በእነርሱም ላይ ጥቃት ፈጸመ። ጌታም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ አንድም ሳያስቀሩ መቱአቸው። ኢያሱም ጌታ እንዳዘዘው በእነሱ ላይ አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሦርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሦርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። በእርሷም ያሉትን ሰዎች ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፤ አሦርንም በእሳት አቃጠላት። የጌታም ባርያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። ዳሩ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአሦር ብቻ በቀር እስራኤል በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም። የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። ጌታም ባርያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ ቈላውም እስከ ሴይር ከሚያወጣው ከሐላቅ ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በአልጋድ ድረስ ነበር፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፤ ሁሉንም በጦርነት ድል አድርገው ያዙ። ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ፥ እንዲያጠፉአቸው ምሕረትንም ሳያደርጉ ፈጽመው እንዲፈጅዋቸው፥ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከጌታ ዘንድ ሆነ። በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። ጌታም ለሙሴ እንደ ተናገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደየነገዳቸው ድርሻ ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከጦርነት ዐረፈች።