ኢያሱ 1:6-9
ኢያሱ 1:6-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ። አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንብበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። እነሆ አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።”
ኢያሱ 1:6-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ። አይዞህ፤ ብቻ አንተ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤ በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”
ኢያሱ 1:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፥ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፥ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፥ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?
ኢያሱ 1:6-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አይዞህ፤ በርታ፤ እኔ ለቀድሞ አባቶቻቸው ልሰጣቸው ቃል የገባሁላቸውን ምድር ለማውረስ ለእነዚህ ሕዝብ መሪ ትሆናለህ። አንተ ብቻ አይዞህ፤ በርታ፤ አገልጋዬ ሙሴ ለሰጠህም ሕግ ሁሉ እውነተኛ ታዛዥ ሁን፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ማናቸውም ነገር እንዲሳካልህ ከዚህ ሕግ ከቶ ዝንፍ አትበል፤ ይህን የሕግ መጽሐፍ ምን ጊዜም ከማንበብ አትቈጠብ፤ በእርሱ የተጻፈውን ሁሉ መፈጸም ትችል ዘንድ እርሱን ሌሊትና ቀን አሰላስለው፤ ይህንን ብታደርግ፥ ሁሉ ነገር በተቃና ሁኔታ ይሳካልሃል። በምትሄድበት ሁሉ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለምሆን አይዞህ! በርታ! አትፍራ! ብዬ አዝሃለሁ።”
ኢያሱ 1:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግም በርታ፤ ባርያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ከእርሱ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአንደበትህ አይለይ፥ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ እንድትጠብቅና እንድታደርገው በቀንም በሌሊትም አሰላስለው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቃናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ ጌታ አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”