ኢያሱ 1:5-7
ኢያሱ 1:5-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ። አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል።
ኢያሱ 1:5-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋራ እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋራ እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም። “ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ። አይዞህ፤ ብቻ አንተ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
ኢያሱ 1:5-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፥ ከሙሴ ጋር እንደሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ አልጥልህም፥ አልተውህም። ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፥ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፥ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።
ኢያሱ 1:5-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንተ ኢያሱ፥ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ አንተን ተቋቊሞ ድል የሚነሣህ ማንም አይኖርም፤ እኔ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርኩ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ሁልጊዜም ከአንተ ጋር ነኝ፤ ከቶም አልተውህም፤ አይዞህ፤ በርታ፤ እኔ ለቀድሞ አባቶቻቸው ልሰጣቸው ቃል የገባሁላቸውን ምድር ለማውረስ ለእነዚህ ሕዝብ መሪ ትሆናለህ። አንተ ብቻ አይዞህ፤ በርታ፤ አገልጋዬ ሙሴ ለሰጠህም ሕግ ሁሉ እውነተኛ ታዛዥ ሁን፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ማናቸውም ነገር እንዲሳካልህ ከዚህ ሕግ ከቶ ዝንፍ አትበል፤