ዮናስ 1:11-17
ዮናስ 1:11-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የባሕሩም ማዕበል እጅግ እየበረታ ስለ ሄደ፣ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት። እርሱም፣ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደ መጣባችሁ ዐውቃለሁ፤ አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይላል” አላቸው። ሰዎቹ ግን ባላቸው ኀይል እየቀዘፉ ወደ የብስ ለመጠጋት ሞከሩ፤ ይሁን እንጂ አልቻሉም፤ ባሕሩ የባሰ ይናወጥ ነበርና። “እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ በዚህ ሰው ነፍስ ምክንያት አታጥፋን፤ የዚህ ንጹሕ ሰው ደምም በእኛ ላይ አይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የወደድኸውን አድርገሃልና” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ከዚያም ዮናስን ይዘው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ። ሰዎቹም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ለርሱም ስእለትን ተሳሉ። እግዚአብሔር ግን ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ፤ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ዐደረ።
ዮናስ 1:11-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የባሕሩም ማዕበል እየበረታ በመሄዱ መርከበኞቹ “ይህ ማዕበል ጸጥ እንዲል በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲሉ ጠየቁት። ዮናስም “ይህ ማዕበል በእናንተ ላይ የመጣው በእኔ በደል ምክንያት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔን አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፤ ማዕበሉም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው። መርከበኞቹ ግን ባላቸው ኀይል ሁሉ እየቀዘፉ መርከቢቱን ወደ ዳር ለማድረስ ሞከሩ፤ ሆኖም ማዕበሉ እጅግ በርትቶ ስለ ነበር ይህን ማድረግ አልቻሉም። ስለዚህ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የዚህ ሰው ሕይወት እንዲጠፋ ብናደርግ አታጥፋን፤ አንተ የፈቀድከውን ስላደረግህ ንጹሕ ደም እንዳፈሰስን አድርገህ አትቊጠርብን!” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ከዚህ በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት፤ የባሕሩም ማዕበል ጸጥ አለ። በዚህም ሁኔታ መርከበኞቹ እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈሩ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስእለትንም ተሳሉ። አንድ ትልቅ ዓሣ ዮናስን እንዲውጥ ከእግዚአብሔር ታዘዘ፤ ስለዚህም ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ኖረ።